10 ኛው የዓለም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ | ዓለም | DW | 20.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

10 ኛው የዓለም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ

«ማንነት እና ብዝኅነት» የዘንድሮው የዶቼቬለ 10 ኛው የዓለም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ መሪ መፈክር ነው።ስብሰባው ከሚነጋገርባቸው ጉዳዮች ውስጥ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ የመገናኛ ብዙኃን ለውጦች ሰብዓዊ መብቶች እና ከጊዜው ጋራ የሚጣጣም ጋዜጠኝነት ይገኙበታል። በዘመናችን ስሜታዊ የፖለቲካ መርህ ላይም ውይይት ይካሄዳል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:46

የቦኑ የዓለም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ

ዓለም አቀፉ የዜና ማሠራጫ ተቋም ዶቼቬለ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የቦኑ የዓለም መገናኛ ብዙሀን መድረክ  ዛሬ ተከፈተ። እስከ ከነገ ወዲያ በሚዘልቀው በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ ጋዜጠኞች ፖለቲከኞች እና የሲቪል ማህበራት ተካፋይ ናቸው። የዶቼቬለ ዋናሥራ አስኪያጅ ፔተር ሊምቡርግ እንዳሉት የዘንድሮ ስብሰባ በዲጂታል ፈጠራዎችም ላይ ያተኩራል።

«ወደ ኋላ የምንመለከት አይመስለኝም። የወደፊቱን እንጂ። ስለዚህ በአሁኑ የዓለም አቀፍ መገናና ብዙኃን መድረክ የዲጂታል ፈጠራዎች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል። »

የመድረኩ ዋና ሀላፊ ፓትሪክ ሎይሽም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ከዚህ ሌላ ስብሰባው የሚያተኩርበት ሌላም መሠረታዊ ችግር አለ።

«በእለት ተእለት ህይወታችን  ስለማይለየው  ስለ ወደፊቱ የዲጂታል ዘመን እንነጋገራለን። ወደፊት እንደ መገናኛ ብዙኃን  እንዴት ሥራችንን እንደምናከናውን፣ እንደተጠቃሚም እንደ ዋትስ አፕ ተጠቃሚ ሁላችንም እንዴት ርስ በርስ ሀሳብ እንደምንለዋወጥ እንነጋገራለን። ጋዜጠኝነት ሁሉም አስተላላፊ እና ተቀባይ የሆነበት ሰፊ ሥራ ነው። ትልቁ ጥያቄ በዚህ ሙያ ውስጥ ተዓማኒ ሆነን እንዴት ልንቆይ እንችላለን ? የሚለው ነው። »

መድረኩ ከሚነጋገርባቸው ጉዳዮች አንዱ ሎይሽ ያነሱት የተዓማኒነት ጉዳይ ነው። የውሸት መስፋፋት ማለት በእውነት ላይ ያልተመሠረተ ጥቆማ ወይም መረጃ እየተጠናከረ በመምጣቱ የተዓማኒነት ጉዳይ በየጊዜው በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ይነሳል። የሁነቶችን እውነትነት በቅጡ ማጣራት ሲያዳግት ወይም ደግሞ የስሜታዊነት አስተሳሰብ እየተጠናከረ ሲመጣ ጉዳዩን ማንሳት አስፈላጊ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ  ከ100 ሀገራት የተጋበዙ በአጠቃላይ 2 ሺህ የሚሆኑ እንግዶች ተገኝተዋል። 40 ያህል የሚደርሱ በግል የሚቀርቡ ዝግጅቶችም በመድረኩ ተካተዋል። በሦስት ቀናቱ መድረክ ከአነስተኛ ዐውደ ጥናቶች አንስቶ በትላልቅ አዳራሾች የሚቀርቡ ዝግጅቶችም አሉ። ከስብሰባው ተካፋዮች መካከል የአውሮፓ ፓርላማ ዋና ፀሀፊ ክላውስ ቤለን፣ የተመ የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በምህጻሩ የዩኔስኮ ምክትል ሃላፊ ፍራንክ ላርዩን ነጋዴ እና የክሬምሊን ተች ሚካኤል ኮዶር ኮቭስኪን እና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሀፊ ሳሊ ሼቲን ይገኙበታል።

የጀርመን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የጥናት እና ምርምር ድርጅቶችም  በፖለቲካው መስክ ለህብረተሰቡ መፍትሄ አመጭ የሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶቻቸውን  ያቀርባሉ። በግል ያካሄዷቸውን ጥናቶች የሚያቀርቡም አሉ። ከቦኑ የዓለም መገናኛ ብዙኃን መድረክ አበይት ክንውኖች አንዱ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ሽልማት ነው። ዶቼቬለ ለሦስተኛ ጊዜ  የሰጠው ይህ ሽልማት ለዋይት ሀውስ ዘጋቢዎች ማህበር ይበርክታል። ማህበሩ ለሽልማቱ የተመረጠበትን ምክንያት የዶቼቬለ ሥራ አስኪያጅ ፔተር ሊምቡርግ ያስረዳሉ።

«ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካኑን ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ጋዜጠኞችን በእጅጉ እያጠቁ ነው። የዋይት ሀውስ ዘጋቢዎችን ክፉኛ እያጠቁ ነው። እናም እንደሚመስለኝ ይህ እንዲሁ የሚታለፍ አይደለም። ከአውሮፓ ወይም ከጀርመን ለዩናይትድ ስቴትስ እንደዚህ ዓይነት መልዕክት እናስተላልፋለን ብለን አስበንም አናውቅ ነበር። ሆኖም እንደማስበው አስፈላጊ ነው ።»

ሊምቡርግፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መገናኛ ብዙኃንን ካወገዙ እና ከሰደቡ ይህ በፕሬስ ነጻነት ላይ እንደተፈፀመ ጥቃት ይቆጠራል ብለን ነው የምናምነው  ብለዋል።  በዓለም ዙሪያ  «ሀሳብን በነጻ መግለጽ» ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች አካል መሆኑንም ሊምቡርግ አሳስበዋል። በአስረኛው የዓለም የመገናና ብዙኃን መድረክ የነገ ውሎው ልዩ ልዩ ጥናታዊ ፊልሞች እና ምርጥ የተባሉ የዶቼቬለ ቴሌዢዥን ዝግጅቶችም ለታዳሚዎች ይቀርባሉ። በመድረኩ የባህል መርሀ ግብር ታዋቂ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ድምጻውያን ይካፈላሉ።  

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic