1፣ የማሊ ሰላም ድርድር፣ 2፣ የናዲን ጎርዲሜር ስራ እና ሕይወት | አፍሪቃ | DW | 19.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

1፣ የማሊ ሰላም ድርድር፣ 2፣ የናዲን ጎርዲሜር ስራ እና ሕይወት

የማሊ መንግሥት እና የቱዋሬግ ዓማፅያን በአልጀሪያ የሰላም ድርድር ጀምረዋል። ማሊ ውስጥ እኢአ በ 2012 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ እና በሀገሪቱ ሰሜናዊ ከፊል የሚንቀሳቀሱት ለዘብተኛ እና አክራሪ የቱዋሬግ ዓማፅያንም በመንግሥቱ አንፃር ትግላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ማሊ መረጋጋት አልቻለችም።

ያኔ ሰሜናዊውን አካባቢ የተቆጣጠሩት የቱዋሬግ አማጽያን ወደ መዲናይቱ ባማኮ መገሥገሥ ሲጀምሩ ነበር ፈረንሳይ ጣልቃ በመግባት ዓማፅያኑን ግሥገሣ ያስቆመችው። ለዘብተኞቹ ዓማፅያኑ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር የማስገኘት ዓላማ ቢኖራቸውም፣ ብዙዎች አዛዋድ የሚል መጠሪያ የሚኖረው የራሳቸውን መንግሥት ለማቋቋም ያላቸው ፍላጎት ውዝግቡ እልባት እንዳያገኘ ድርሻ አበርክቶዋል።

የማሊ መንግሥትና ዓማፅያኑ የሰላም ውል ለመድረስ ካለፈው ረቡዕ ጀምረው በአልጀሪያ መዲና አልዥየ የሰላም ድርድር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። በዚሁ የአልዥየ ዝግ ስብሰባ ላይ ስድስት ያማፅያን ቡድኖች ተሳታፊዎች ቢሆኑም፣ ስድስቱም በአንድ ላይ መደራደሩን አለመፈለጋቸው ተሰምቶዋል። በመሆኑም የሀገሪቱ መንግሥት የልዑካን ቡድን ባለፈው ሰኔ ወር የአልዥየን መግለጫ ከፈረሙት ሦስት ያማፅያን ቡድኖች ተወካዮች እና ከሌሎቹ ሦስት ቡድኖች ጋ በየተራ እየተደራደረ ነው። የአዛዋድ ነፃ አውጪ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ በምሕፃሩ « ኤም ኤን ኤል ኤ» ፣ የአዛዋድ ዐረባዊ ንቅናቄ፤ «ኤም ኤ ኤ » የአዛዋድ አንድነት ምክር ቤት ፣ ይገኙባቸዋል። ከአል ቃይዳ ጋ የቅርብ ግንኙነት አለው የሚባለው አንሳር ዲን በድርድሩ አይሳተፍም።

ለማሊ አንድነት የቆመው መንግሥታቸው ባፋጣኝ ሰላም ለማውረድ ቆርጦ መነሳቱን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላይ ዲዮፕ በድርድሩ መክፈቻ ላይ አስታውቀዋል።

« ወደ አልዥየ ቀና መንፈሥ እና ቁርጠኘነትን ይዘን የመጣነው በሰሜን ማሊ ከሚንቀሳቀሱት የቱዋሬግ ወንድሞቻችን ጋ ዘላቂ እና የሚፀና የሰላም ውል ሊደረስበት የሚቻልበትን መንገድ ሁሉ ለመፈተሽ ነው። »

በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሱት የቱዋሬግ ዓማፅያን ባለፈው ግንቦት 2014 ዓም በኪዳል አካባቢ ግዙፍ ጥቃት ከጀመሩ ወዲህ አንድ አራተኛው የሀገሪቱ አካባቢ እንደገና በዓማፅያኑ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ የመገናኛ ብዙኃን አመልክተዋል። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አልጀሪያዊ ዲፕሎማት እንዳስታወቁት፣ ዓማፅያኑ በድርድሩ የገቡት ተጠናክረው ነው። ፈረንሳዊው የፖለቲካ ተንታኝ እና የማሊ አዋቂ ሚሼል ጋሊም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰነዘሩት።

እነዚሁ የዓማፅያኑ ንቅናቄዎች ባንዳንድ ኪዳልን በመሳሰሉ አካባቢዎች የራሳቸውን አስተዳደር አቋቁመዋል። በሚገባ የተጠና ዕቅድ የሌለው የማሊ መንግሥት ኪዳልን መልሶ ለመቆጣጠር በዚሁ የቱዋሬግ ርምጃ አንፃር ያደረገው ሙከራ ከሽፎዋል። እና ሁለቱን ስናወዳድር ለነፃ መንግሥት ምሥረታ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ጠንካራ ሆኖ እናየዋለን። »

የተመ በማሊ በጀመረው በምህፃሩ « ሚኑስማ » በተባለው ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ እና በፈረንሳይ ወታደሮች የሚረዳው የማሊ መንግሥት በሀገሩ ሰሜናዊ ከፊል በወቅቱ ብዙም ማድረግ አልቻለም። ባለፈው ሰኞ እንኳን አንድ የፈረንሳይ ወታደር በዚሁ አካባቢ በአንድ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ተገድሎዋል፤ ባለፉት ቀናትም በዚሁ አካባቢ፣ በተለይ፣ ከኪዳል በስተደቡብ 100 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው አኔፊስ በ «ኤም ኤን ኤል ኤ » እና በ«ኤም ኤ ኤ » መካከል ግጭት እንደነበር ተሰምቶዋል። ሁለቱ ቡድኖች ተጋጩ መባሉን የ « ኤም ኤን ኤል ኤ » ቃል አቀባይ ሙሳ አግ አሳሪድ አስተባብለዋል።

« አኔፊስ በ «ኤም ኤን ኤል ኤ » እና በ«ኤም ኤ ኤ » መካከል ውጊያ አልተካሄደም። ሁለቱ ቡድኖች በመተባበር ወደ አልዥየ አንድ የጋራ የልዑካን ቡድን ይዘው ነው ወደ አልዥየ የተጓዙት። በአኔፊስ ለታየው ግጭት ተጠያቂዎቹ አንዱን ሠፈራችንን ያጠቁት የማሊ ጦር አባላት ናቸው። »

የማሊ መንግሥት በዚሁ ወቀሳ አኳያ ለዶይቸ ቬለ አስተያየት ከመስጠት የተቆጠበው የማሊ መንግሥት በወቅቱ ትኩረቱን የአልዥየው የሰላም ድርድር ፍሬያማ ውጤት በሚያስገኝበት ጥረት ላይ ማድረግ መምረጡን አስረድቶዋል። በዚሁ መሠረትም፣ ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች የሰላም ውይይት ከመጀመራቸው በፊት ባለፈው ማክሰኞ የእሥረኞች ልውውጥ በማድረግ፣ መንግሥት በሰሜን ማሊ ተይዘው የነበሩ 41 የቱዋሬግ አማጽያንን ፣ ዓማፅያኑ 45 የማሊ ወታደሮች ለቀዋል።

-----------------

የናዲን ጎርዲሜር ስራ እና ሕይወትን

በሕይወት ዘመናቸው ሳሉ ትልቅ ዝና እና አክብሮት ያተረፉ ግለሰብ ነበሩ። ደቡብ አፍሪቃዊቱ የኖቤል የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ ናዲን ጎርዲሜር ባለፈው እሁድ በ90 ዓመታቸው አርፈዋል።

ዝርያቸው ከሊትዌንያ ከሆኑ አይሁዳዊ ሰዓት ሰሪ አባት እና ከእንግሊዛዊት እናት የተወለዱት ናዲን ጎርዲሜር « በርገርስ ዶውተር » « ኧ ሀውስ ኦፍ ስትሬንጀርስ» « ዘ ሀውስ ጋን» በመሳሰሉት መጻሕፋቸው ነበር ዝና ያተረፉት። ስራዎቻቸው ስለ አፓርታይድ ዘመን እና ስላስከተለው ጥፋት ነው የሚያወሱት። ደራሲዋ ጎርዲሜር እአአ በ1991 ዓም « በርገርስ ዶተር » ለሚለው መጽሓፋቸው ነበር የኖቤል ሰላም ሽልማት ያገኙት። ጎርዲሜር ለሥነ ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ያገኙ ሰባተኛዋ ሴት ሲሆኑ፣ በአፍሪቃ ሽልማቱን ካገኙት አራት ደራስያን መካከል ጎርዲሜር የመጀመሪያዋ ሴት ደራሲ ሆነዋል። እስከዛሬ የሥነ ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ያገኙት ሴቶች ቁጥር 13 ደርሶዋል። ደቡብ አፍሪቃ ታዋቂ ደራሲዋን በማጣቷ አዝናለች። ብዙዎች ጥልቅ ሐዘን ተሰምቷቸዋል። ባለፉት ጊዚያት ናዲን ጎርዲሜር ራሳቸው በጥብቅ ሲነቅፉዋቸው የነበሩት የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ እንኳን ጎርዲሜር የተጫወቱት ሚና እጅግ ከፍ ሀገራቸው በጎርዲሜር ሞት ትልቅ ሀገር ወዳድ እና ዝነኛ ደራሲ ማጣቷን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

Süsafrika Jacob Zuma nach der Wahl

አባል የነበሩበት የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ፣ በምሕፃሩ « ኤ ኤን ሲ »ም ኪነት፣ ሙዚቃ እና ሥነ ጽሑፍ በፀረ አፓርታይድ ሥርዓት አንፃር በቀላሉ የማይገመት ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ባሳዩት በጎርዲሜር ሞት ደቡብ አፍሪቃ ከታዋቂዎቹ የላቀ የሥነ ጽሑፍ ችሎታ የነበራቸውን ደራሲዋን አጥታለች ሲል ነበር አድናቆቱን እና አክብሮቱን የገለጸው። ሁሌ መልካም ስብዕናን ለማጉላት የጣሩትን የእኒህኑ ደራሲ ስራ እንደ መስታወታቸው ይመለከቱት እንደነበር የ«ኤ ኤን ሲ » ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ ተቋምም የእኩልነት እና የዴሞክራሲ ድምፅ » በማለት ነበር ደራሲዋን ያሞገሣቸው። ታህሳስ አምሥት፣ 2013 ዓም የሞቱት እና ከጎርዲሜር ጋ ወዳጃዊ ግንኙነት የነበራቸው ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ስለለዘብተኛ ነጮች አመለካከት ከጎርዲሜር መጽሓፍት ብዙ ሊማሩ መቻላቸውን ስለሕይወት ታሪካቸው በጻፉት መጽሓፋቸው ላይ ጠቅሰዋል።

እንደ አንድ ነጭ ደቡብ አፍሪቃዊት የውሁዳኑን ነጮች አገዛዝ፣ አፓርታይድን በተቃወሙበት ርምጃቸው በሀገሪቱ ፀረ አፓርታይድ ትግል ላይ ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ ጋዜጠኛዋ እና ደራሲዋ ሩት ቫይስ አስታውቀዋል። የብሔራዊ ሶሻሊስት፣ የናዚ ሥርዓት/ዘመንን በመሸሽ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሄዱት እና እአአ እስከ 1960 ዓም በዚያ የኖሩት ቫይስ የጎርዲሜር የቅርብ ጓደኛ ነበሩ።

« በሁለታችን መካከል የነበረው ልዩነት እሷ የተወለደችው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ መሆኑ ነው። ይህም በፖለቲካዊ አመለካከቷ እና በሀገሪቱ በነበረው የዘር አድልዎ ሥርዓትን በተቃወመችበት አቋሟ ፀንታ ለመቆየት ጠንክራ ሰርታለች። ይህን ውሳኔ መውሰድ ነበረባት። እንዲያውም፣ እንዲህ መኖር አልፈልግም፣ ይህን (ሥርዓት)በፍፁም አልቀበልም፤ ነበር የምትለው። »

በውሁዳኑ የነጮች አገዛዝ አንፃር የታገሌት ጎርዲሜር «ኤ ኤን ሲ »ን የተቀላቀሉት በሕገ ታግዶ በነበረበት በአፓርታይድ ሥርዓት ነበር። የአፓርታይድ ሥርዓት ተገርስሶ እአአ በ1994 ሥልጣን የያዘው «ኤ ኤን ሲ» ባለፉት ዓመታት ያሳየውን ወይም የተከተለውን አሰራር ጎርዲሜር በግልጽ መንቀፋቸውን ደቡብ አፍሪቃዊው የመገናኛ ብዙኃን ጠቢብ አንጀሎ ፊክ ያስታውሳሉ።

« ጎርዲሜር ጠንካራ ትችት ማቅረባቸውን፣ ሁኔታዎችን ነቅተው መጠበቃቸውን ፣ ጉዳዮችን ጠለቅ ብለው መመርመራቸውን፣ እና በዓለም የሚካሄደውን ሁሉ በጥሞና መከታተላቸውን ቀጠሉ። በዚሁ ርምጃቸው ሂደቶችን ለመረዳት ብቻ ሳይሆን ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚፈፀሙ ስህተቶችም ለመንቀፍም ጭምር ነበር የፈለጉት። ሰፊው ሕዝብ እንዲያደንቃቸው ፍላጎት ኖሯቸው አያውቅም። »

ጎርዲሜር ከማንም ተፅዕኖ ነፃ እንደነበሩ ጋዜጠኛዋ ሩት ቫይስም ይናገራሉ።

« ጎርዲሜር በስራዎቻቸው ላይ ስለ ጥቁሮቹ ደቡብ አፍሪቃውያን ጉዳይ ስለሚያነሱ የ«ኤ ኤን ሲ » አመራር ለርሳቸው ትልቅ አመለካከት እንዳላቸው ያውቁ ነበር። ያም ቢሆን ግን ከ1994 ዓም በኋላ «ኤ ኤን ሲ» እንደ ፖለቲከኛ አድርጎ ሊያቀርባቸው ያደረገውን ሙከራ አልተቀበሉትም። ደራሲ ነበሩ። »

እርግጥ ፣ እንደ አንድ ነጭ ለዘብተኛ ከዘር አድልዎ አገዛዝ ነፃ በሆነች ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ያን ያህል ትኩረት አላገኙም፤ ግን፤ አዲሱን የደብብ አፍሪቃ አመራር በግልጽ በተቹበት « ኖ ታይም ላይክ ዘ ፕሬዘንት » በሚለው መጽሓፋቸው ነጮቹ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያንም ዘንድ የበለጠ ተቀባይነትን አግኝተዋል። ለፀረ አፓርታይድ ታጋይ ሞራካቤ ራክስ ሲኮሃ፣ ነጭዋ ደቡብ አፍሪቃዊት ደራሲ ናዲን ጎርዲሜር የሕይወት ዘመናቸውን ለብዙዎቹ ችግር ላይ ለነበሩት ጥቁሮቹ የሀገራቸው ዜጎች ሲሟገቱ ያሳለፉ ትልቅ አድናቆት የሚገባቸው ግለሰብ ነበሩ።

ሂልከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic