1 ሺህ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድምቀት ተከበረ | ኢትዮጵያ | DW | 04.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

1 ሺህ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድምቀት ተከበረ

1 ሺህ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በመላዉ ኢትዮጵያ በድምቀት ተከበረ። በተለይም መዲና አዲስ አበባ ስቴዲዮም ዉስጥና ዙርያዉን ከማለዳው ጀምሮ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት የእምነቱ ተከታዮች፣ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሮአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:09

ኢድ አልፈጥር አዲስ አበባ ስቴዲዮም ዉስጥና ዙርያ ላይ በድምቀት ተከብሮአል

1,440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በመላዉ ኢትዮጵያ በድምቀት ተከበረ። በተለይም መዲና አዲስ አበባ ስቴዲዮም ውስጥና ዙርያዉን ከማለዳው ጀምሮ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት የእምነቱ ተከታዮች፣ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሮአል። በበዓሉ በአዲስ አበባ ከተማም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተገኝተዉ ንግግር አድርገዋል።

በበዓሉ ተቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት የዘንድሮዉ የኢድ አልፈጥር በዓል ሰላምና አንድነት የታየበት መሆኑን ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የኢድ ሶላት መስገጃ ቦታን ለህዝበ ሙስሊሙ በማፅዳት ላሳዩት ቀና ትብብር አመስግነዋል። 1,440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ህዝበ ሙስሊሙ በአዲስ አበባ ከተማ በሚከናወኑ የፅዳት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የችግኝ ተከላ ሥራዎች እንዲሳተፍ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሸገር እና አንበሳ የከተማ አውቶቡሶች ከተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች የኢድ ሶላት ወደ ሚደረግበት የአዲስ አበባ ስቴዲየም የደርሶ መልስ የነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በትናንትናዉ ዕለት በፌስ ቡክ ገፁ ገልፀዉ ነበር።

የኢድ አል ፈጥር በዓል አከባበር በባህር ዳር

በባሕር ዳር ኢድ አል ፈጥር በዓል ሲከበር ወንድማማችነት የታየበት እንደነበር ምዕመናን አመለከቱ፣ በዓሉ ሲከበር የተቸገሩትን መርዳት እንደሚገባም ተናግረዋል። 1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በባሕር ዳር ሲከበር ወንድማማችነት የታየበት ነበር ሲሉም ምዕመናኑ አመልክተዋል፡፡ ክርስቲያን ወንድሞች መስገጃ ቦታዎችን በማፅዳት ያሳዩት ወንድማዊነት የቆየውን ወንድማማችነት የሚያመለክት እንደሆነም ተናግሮዋል።

በደቡብ ክልል የኢድ አልፍጥር በዓል አከባበር

አንድ ሺህ አራት መቶ አርባኛው የኢድ አልፍጥር በዓል በደቡብ ክልል በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች በዛሬው ዕለት ተከብሮ ውሏል። በተለይም በሀዋሳ ከተማው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተክቢራ  (የውዳሴ መዝሙር ) በማሰማት  በሀዋሳ መስቀል አደባባይ የተሰባሰቡት የእምነቱ ተከታዮች የጋራ ጸሎት በማድረግ ለፈጣሪያቸው ምስጋና አቅርበዋል። ዶቼ ቨለ ( DW ) ያነጋገራቸው የጸሎቱ ተሳታፊዎች በዓሉን ከቤተሰብና  ከወዳጅ ዘመድ ጋር በመሰባሰብና በየአካባቢያቸው  የተቸገሩ ሰዎችን በማብላት እያከበሩ እንደሚገኙ  ገልጸዋል።

የኢድ አልፍጥር በዓል አከባበር በድሬደዋ

የዘንድሮ 1,440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬደዋ የተከበረበት መንገድ ድሬደዋ ቀድሞ የምትታወቅበትን መልካም ገፅታ ያመላከተ እንጂ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ ግበዓት የሚጠቀሙበትን ዓይነት ገፅታ ብቻ የታየበት አልነበረም ፤ በልዩነት ተዋዶ የመኖር እሴቱን ያንፀባረቀበት ጭምር ነበር፡፡ ራስ ተነሳሽነት በከተማዋ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካረዎች በአብዛኛው የበዓሉ ዋነኛ ስነስርዓት የሆነው የኢድ ሰላት በሚካሄድበት ቦታ ህዝበ ሙስሊሙ ሊያጋጥመው የሚችል የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት  ተሽከርካረዎች የነፃ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ትልቅ ሥራ ሢሠሩ ማርፈዳቸውን ተመልከተናል ፡፡

በድሬደዋ በዛሬው ዕለት ከነበረው የአከባበር ሁኔታ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን ለ«DW» የሰጡት አቶ ሱልጣን በድሬደዋ ዛሬ የተከበረው በዓል «ስንናፍቀው የነበረ በራሳችን ጊዜ ከቀልባችን ጋር ሳንሆን ጥለነው የነበረውን ማንነታችንን ነው ዘንድሮ ያገኘነው» ብለዋል ።

የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ኡስታዝ አዩብ ሀሰን በበኩላቸው ወጣቱ እንዲሁም ሙሰሊም አንድነቱን በመጠበቅ እና ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር በጋራ የመስራት ጥሩ ባህላችንን ይዘን ድሬደዋ ከድህነት ወጥታ በእድገት ጎዳና እንድትጓዝ ለማድረግ  በጋራ መስራት ይገባናል ብለዋል ፡፡

የበአሉ ታዳሚዎች የዘንድሮውን የረመዳን ወቅት ሙስሊሙ ከሌሎች እህት ወንድሞች ጋር በመሆን ሰላማዊና በጣም በጥሩ ሁኔታ በፆም በጸሎት ማሳለፉንና የዛሬወም ሁኔታ ደስታው እጥፍ ድርብ ነው ብለዋል ፡፡

በዓሉን የተቸገሩ ወገኞችን በመርዳትና በጋራ በማክበር እንደሚያሳልፉ የገለፁ አስተያየት ሰጭዎች የረመዳን ወርንም ሆነ በዓሉን የተለየ የሚያደርገው ይኸው መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓልን በማስመልከት በከተማው ተፈናቅለው በመጠሌ ለሚገኙ ዜጎች እንዲሁም ድጋፍ ለሚያፈልጋቸው ወገኖች የተለያዩ ድጋፎች በተለያዩ አካላት ተደርገዋል ፡፡ ሰላማዊነቱ ዋንኛ ትኩረት ሆኖ የሚካሄደው የኢድ በዓል በአስተዳደሩ ሰላማዊ እና የተሻለ ድባብ ኖሮት በመካሄድ ላይ ይገኛል ፡፡ በዓሉ በተመሳሳይ በሀረሪ እና ሶማሌ ክልላዊ መስተዳድሮች በጥሩ ሁኔታ መከበሩን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ፡፡

ወኪሎቻችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የበዓሉን አከባበር የቃኙበትን ዘገባ የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ! 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic