ፖለቲካና የሴቶች ተሳትፎ | ባህል | DW | 01.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ፖለቲካና የሴቶች ተሳትፎ

«ሴቶቻችን ለፍትህ መታገል አለባቸዉ፤ ሰዉ እንዳይሞት መታገል አለባቸዉ። ኢትዮጵያን አንድ ሆና እንድትቀጥል መታገል አለባቸዉ፤ እንጂ የጩኸት ፖለቲካ ሴቶች ላይ መኖር ወይም መታየት የለበትም። ምክንያቱም ሴት ልጅ ጥበበኛ ናትና። ጥበበኛም የምትሆነዉ በማስተዋል በመንቀሳቀስዋ ነዉ።» 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:26

ሴቶቻችን በፖለቲካዉ የሚጠበቀዉን ያህል እየሰሩ አይደለም

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ ሀገራት የሴቶችን ሚና በተመለከተ ያለው አብዛናዉ ባህላዊ እና ልማዳዊ አስተሳሰብ የሴቶችን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶች ለሥነ-ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ 

«ሴቶቻችን ለፍትህ መታገል አለባቸዉ፤ ሰዉ እንዳይሞት መታገል አለባቸዉ። ኢትዮጵያን አንድ ሆና እንድትቀጥል መታገል አለባቸዉ፤ እንጂ የጩኸት ፖለቲካ ሴቶች ላይ መኖር ወይም መታየት የለበትም። ምክንያቱም ሴት ልጅ ጥበበኛ ናትና። ጥበበኛም የምትሆነዉ በማስተዋል በመንቀሳቀስዋ ነዉ።» 

«ስኩዋድ» የሚል ቅጽል መጠርያ የተሰጣቸዉ አራቱ ሴት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ምክር ቤት አባላት እና የዲሞክራት ፓርቲ ተመራጮች ካለፉት ወራቶች ጀምሮ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚያነስዋቸዉን እና የሚሰነዝሩዋቸዉን መጤን የሚያገል አነጋገር እየተጋፈጡ ነዉ። ግራ ዘመም ማለትም የሊበራል አቁዋም ያላቸዉ አራቱ አሜሪካዉያን እንስት ተወካዮች፤ የትራምፕን ዘር ተኮር ጥላቻ አቁዋም ብቻ ሳይሆን በአየር ብክለት ማጽዳትና ክብካቤ በግብር አከፋፈል ስራትና በመሳሰሉት ከወግ አክራሪው የትራምፕ አስተዳደር ይቃረናሉ፡፡ ሴቶች በዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እንዲሁም ብሔራዊ ሕጎች ላይ የተቀመጡ የሰብዓዊ መብቶች እኩል ተጠቃሚ መሆናቸዉ በወረቀት ሰፍሮ ቢታይም፤ በሴቶች ላይ የሚደርስዉ ጥቃት እና አድሎአዊ አሰራር ዓለም አቀፋዊ እውነታ መሆኑ እሙን ነዉ፡፡ በዓለማቀፍም ሆነ በሀገራቀፍ ደረጃ ሴቶች የሰብኣዊ መብቶች ባለቤት መሆን ቢችሉም መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህን አያሳይም። ይሁንና ሴቶች በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰዉን መገለል መድሎ ለመግታት በሚያርጉት ከፍተኛ ጥረት መታፈንን እና ጭቆናን ጥሰዉ የሚወጡ ሴቶች ጥቂት እንዳልሆኑ እሙን ነዉ? የእለቱ ዝግጅታችን የዘር መድሎ አለባቸዉ ተብለዉ ሰሞኑን ስማቸዉ ስለለሚብጠለጠለዉ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጎን ዉጋት የሆኑትን ስለአራቱ የአሜሪካ ምክር ቤት እንስት ተወካዮች እንቅስቃሴን እያየን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዉያን ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ስላላቸዉ ጉልህ ሚና በጥቂቱ ይዳስሳል። 

ሰሜን አሜሪካ ከዓለም ሃገራት የተሰባሰበ ሕዝብ የሚኖርባት በመሰረታዊ ቅርፅዋ የመጤዎች ሃገር ብትሆንም ቅሉ አወዛጋቢዉ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳምንታቶች በፊት ታዋቂ የሆኑ የሴት የምክር ቤት አባላትን በመዝለፋቸዉ በዓለም ዙርያ በሚገኝ የመገናኛ ብዙኃኖች «መጤ ጠል» ተብለዉ ስማቸዉ እየተብጠለጠለ ነዉ። ይሁን ይሁንና የሃያሊትዋ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ «መጤ» ያልዋቸዉን የሴቶች ስራ ዝቅ አድርገዉ ማንኳሰሳቸዉ በሰላም ይሆን? ወይስ ለሚቀጥለዉ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የፖለቲካዊ ቅድመ ዝግጅት። ረዘም ላሉ ዓመታት በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆነችዉ እና በዋሽንግተን በሚገኝ የዲያስፖራ ቢሮ የምክር ስራ አገልግሎት በመስጠትዋ የምትታወቀዉ የዲያስፖራ ሬድዮ ጋዜጠኛ ቅድስት አቤኔዘር፤ ትራምፕ ፕሬዚደንታችን ስለሴቶች አስተያየት ሲሰጡ እጅግ ግድፈት የበዛበት ነዉ ስትል ነዉ የምትገልፃቸዉ።

  

«ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለሴቶች የሚሰጡት አስተያየት እጅግ ግድፈት የበዛበት ጽንፍም የበዛበት ነዉ። ትራምፕ ከሌሎች ሃገራት ፕሬዚዳንቶች ለየት የሚያደርጋቸዉ በጽንፍ ሰዉን በመዝለፍ በመስደብ በመዘርጠጥ ነዉ ወጣ ብለዉ መታየትን የሚፈልጉት። ያን ተከትሎ አራቱ የምክር ቤት አባላት እንስቶች «ነጭ አይደሉም» በአሜሪካን ሃገር ዉስጥ የመብት መከበር ብሎም በተለያዩ ጉዳዮች መንግሥትን በመወትወት ጥሩ የአክቲቪስት ስራ የሚሰሩ ናቸዉ። ስራቸዉን አይተዉ ለምን ግን ወደየሃገሮቻችሁ አትመለሱም፤ ካልተመቻችሁ ለምን አትመለሱም ሲሉ ነበር በይፋ የተናገርዋቸዉ። ይህ የሃያልዋ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አነጋገር የማይጠበቅ ነዉ በአሜሪካ ሁሉም ሰዉ በጥገኝነት የመጣ ነዉ። አልያም በጥገኝነት ከመጡ እዛዉ አሜሪካ ዉስጥ የተወለደ ነዉ። ፕሬዚዳንቱ ይህን በመናገራቸዉ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ሳይቀር ሲተቹ ሰንብተዋል።         

በርግጥ የእንስቶቹ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ በርግጥ ምንድ ነዉ?

« አራቱም እንስቶች በፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ የየራሳቸዉን ነገር በማንሳት ይተቻሉ። ኤላህን ኦማር የሚኒሶታ የምክር ቤት ተወካይ ናት፤ ይህች ሴት ከሶማልያ በሰባት ዓመትዋ ነዉ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጣች ናት። በሚኒሶታ ምክር ቤት ተመርጣ እየሰራች ያለች ሴት ናት። አራቱም ሴቶች ፕሬዚዳንቱ በሚያነስዋቸዉ ነገሮች ላይ መናገር ብቻ ሳይሆን፤ ከሜክሲኮ በኩል በሚገቡት ስደተኞች ላይ የሚደረገዉን ጫና በማንሳት በሞገታቸዉ ይታወቃል»

ትራምፕ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ስደተኞች እንዳይገቡ ሚክሲኮ ድንበር ግንብ አቆማለሁ ማለታቸዉ ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ በተለያዩ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች እየታዩ የነበሩት ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመራቸዉ ፤ እንዲሁም በሃገሪቱ ዉስጥ የስራ ፈጠራ አልያም የከፍተኛ ስራ ቦታ ቢኖርም ትራምፕ አሁንም ስደተኛን ላለመቀበል መወሰናቸዉ ሃገሪቱ ያላትን እሴት እያሳጡ መሆናቸዉን ጋዜጠኛ ቅድስት ተናግራለች።

ወደኛ ሃገር ልዉሰድሽ ወደ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የሴቶች መብት ከሞላ ጎደል መከበሩ በእዉን እየታየ ነዉ የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ሴቶች በሚኒስትር ደረጃ ከፍተኛ የስልጣን ቦታን ተቆናጠዋል ይበል የሚያሰኝ ነዉ ፤ ይሁንና ሴቶች አሁንም ከወንዶች እኩል በፖለቲካዉ በንቃት ሲሳተፉ አይታይም። አሁንም የባህል ተፅኖ አለ፤ ወይስ ወንዶቻችን አሁንም ሴቶችን ይጫናሉ! በርግጥ በድፍረት የሚናገሩ ትችት የሚያቀርቡ በጣት የሚቆጠሩ ሴቶች መኖራቸዉ እንዳለ ሆኖ ማለት ነዉ። ቃለ ምልልሱን የሰጠችንን ጋዜጠኛ ቅድስት አቤኔዘርን በዶቼ ቬለ «DW» በማመስገን ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic