ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ድጋሚ ተመረጡ | ዓለም | DW | 07.11.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ድጋሚ ተመረጡ

ዩ ኤስ አሜሪካውያን ባራክ ኦባማን ሀገሪቱን ለተጨማሪ አራት ዓመታት በፕሬዚደንትነት እንዲመሩ ድጋሚ መረጡዋቸው። ቀልብ በሳበ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ነበር ዴሞክራቱ ፕሬዚደንት ከባድ የነበረውን ፉክክር ያሸነፉት።

ባራክ ኦባማ በተለይ ድምፃቸውን ለየትኛው ዕጩ እንደሚሰጡ በግልጽ ባልታወቁት እና « ስዊንግ ስቴትስ» በሚባሉት ብዙዎቹ ፌዴራውያን ግዛቶች ቀንቶዋቸዋል። የድምፅ ቆጠራው ሳያበቃ በፊት ኦባማ በምርጫው ለማሸነፍ የሚያስፈልገውን የፌዴራል ግዛቶች ተወካዮችን ድምፅ ማግኘታቸው የተረጋገጠው የኦሀዮ ፌዴራዊ ግዛት ተወካዮችን ድምጽ ባገኙበት ጊዜ ነበር። የፍሎሪዳ ውጤት እስከመጨረሻው አልታወቀም ነበር፤ ምንም እንኳን በውጤቱ ላይ ምንም ለውጥ ባያመጣም።

ድጋሚ የተመረጡት ፕሬዚደንት ኦባማ ውጤቱ በይፋ ከተገለጸ በኋላ ባሰሙት ንግግር፡ በምርጫው የተሳተፉትን የዩኤስ አሜሪካ ዜጎች በጠቅላላ ከልብ አመሥግነዋል።በምርጫው የተሸነፉትን ተፎካካሪያቸውን ሬፓብሊካዊውን ሚት ሮምኒን ለዩኤስ አሜሪካ ጥቅም ሲሉ አብረዋቸው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ሽንፈታቸውን የተቀበሉት ሚት ሮምኒ ለኦባማ ስልክ በመደወል የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። እስካሁን ይፋ በወጣው ውጤት መሠረት፣ ፕሬዚደንት ኦባማ 303፣ ሚት ሮምኒ ደግሞ 206 የፌዴራል ግዛቶች ተወካዮች ድምፅ አግኝተዋል።

ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ ጎን ለጎን በተካሄደው የሕዝብ መምሪያ ምክር ቤት የሬፓብሊካውያኑ ፓርቲ ፡ ለአንድ ሦስተኛው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምርጫ ደግሞ የዴሞክራቶቹ ፓርቲ በድጋሚ አብላጫውን ድምፅ አግኝተዋል። የፕሬዚደንት ኦባማ ተቀናቃኝ ሬፓብሊካዊው ጆን በነር እንደገና የሕግ መምሪያው ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሆነው ተመርጠዋል።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ