ፕራምፕ የተገለሉበት የቡድን 7 ጉባኤ | ዓለም | DW | 27.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ፕራምፕ የተገለሉበት የቡድን 7 ጉባኤ

በኢንዱስትሪ የበለፀጉትን የዓለም ቱጃር ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የቡድን ሰባት ጉባኤ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቀነስ በተነደፈዉ ዕቅድ ላይ ሳይስማማ ተበተነ። ከትናንት ጀምሮ ታኦርሚናል-ኢጣሊያ ዉስጥ የተሰበሰቡት የሰባቱ ሐገራት መሪዎች ዛሬ ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ የአየር ንብረት ለዉጥን በተመለከተ አለመግባባታቸዉን አምነዋል።

ከቡድን ሰባት አባል ሐገራት መሪዎች ስድስቱ የዓየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የተነደፈዉን የፓሪስ ዉል የተባለዉን ሥምምነት ገቢር ለማድረግ ሲስማሙ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ሥምምነቱን አልተቀበሉትም። የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስድስት ወይም ሰባት ለአንድ ይሉታል፤ ልዩነቱን።«ሰወስተኛ፤ ሥለ ዓየር ንብረት የተደረገዉ ዉይይት በሙሉ በጣም አስቸጋሪ ነበር።የማያረካ ነበር።ስድስት የአዉሮጳ ሕብረት ከተጨመረ ደግሞ ሰባት ለ አንድ ነን።ይሕ ማለት ዩናይትድ ስቴትስ የፓሪስን ሥምምነት ማክበር አለማክበሯ እስካሁን ግልፅ አይደለም።ሥለዚሕ እኛ ዙሪያ ጥምጥም አልሄድም በግልፅ ነዉ ያስታወቅነዉ።ከቡድን ሰባት አባል መንግስታት እኛ ስድስታችን እና የአዉሮጳ ሕብረት ለዕቅዱ ግብ መምታት የምንሰጠዉን ድጋፍ እንቀጥላለን።»

ከጉባኤዉ በኋላ የወጣዉ የጋራ የአቋም መግለጫ እንደሚለዉ ዩናይትድ ስቴትስ የዓየር ንብረት መርሕዋን በመከለስ ላይ ሥለሆነች በፓሪሱ ሥምምነት ላይ ያላትን አቋም አሁን ማሳወቅ አልፈለገችም። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ስደተኞችን መርዳት፤ማስጠጋት፤ ድጋፍ መስጠት እና የንግድ ልዉዉጥን የሚመለከቱ ሌሎች ሐሳቦችን የተቀበሉት ከብዙ ክርክርና ሙግት በኋላ ነዉ።

ነጋሽ መሀመድ

ልደት አበበ