ፕላስቲክ ያስከተለዉ ብክለት | ጤና እና አካባቢ | DW | 24.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ፕላስቲክ ያስከተለዉ ብክለት

በየዓመቱ እጅግ በርካታ የፕላስቲክ ቆሻሻ ባህር ላይ ይጣላል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2010ዓ,ም ብቻ ከ4,8 እስከ 12,7 ሚሊዮን ቶን ፕላስቲክ ዉቅያኖስ ዉስጥ ተጥሎ መገኘቱን የአዉስትራሊያና ዩናይትድ ስቴትስ ተመራማሪዎች መዝግበዉ ይፋ አድርገዋል።

ለእቃ መያዣና መጠቅለያ፣ ለዉሃ እየተባለ ቢዘረዘር ፕላስቲክ አገልግሎት ላይ የዋለበትን መመገመት ይቻላል። በዉቅያኖስ ላይ እና ከዉኃዉ ሥር በአሁኑ ወቅት ተከማችተዉ የሚገኙት ዉዳቂ ፕላስቲክ ነክ ቆሻሻዎች በአንድ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ አንዳንዶቹም እዚያዉ ባህር ላይ የተወረወሩ ናቸዉ። እነዚህ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በሂደት በተለያዩ መንገዶች ወደከባቢዉ ስነምህዳር እንዲሁም ወደእኛዉ ሊመለሱ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ነዉ በዘርፉ ምርምር ያካሄዱት ባለሙያዎች የሚያመለክቱት።

ከምንም በላይ ከሚጣሉት የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በአማካኝ አብዛኛዉ በየዓመቱ ወደባህር 8,8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚገባዉ ወደዉቅያኖስና ባህር ነዉ። በባህር ዳርቻ በተደረገዉ ቅኝት በፕላስቲክ የእቃ መያዣ የተሞሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ የጥርስ ቡሩሽና የተለያዩ ነገሮች የሚቋጠሩባቸዉ ላስቲኮች አንደኛዉ በሌላዉ ላይ ተደራርበዉ ነዉ የተገኙት። ሁኔታዉን በቅርበት የተመለከቱት ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህን በባህር ዳርቻ አካባቢ በየ30 ሴንቲ ሜትር ርቀቱ ማግኘት የተለመደ ሆኗል። ከዚህ በመነሳትም ተመራማሪዎቹ በየዓመቱ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የፕላስቲክ ቆሻሻ ወደምድራችን የዉኃ አካላት እንደሚገባ በጥናት የተደገፈ ግምታቸዉን አስፍረዋል። ተመራማሪዎቹ የባህር ዳርቻዎች ያሏቸዉን የ192 ሃገራትን ይዞታ ነዉ የተመለከቱት። ከአምስት ዓመት በፊት በጥቅሉ 275 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ ተወግዷል። ከዚህ መካከልም ከ4,8 እስከ12,7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆነዉ ወደባህር ነዉ የገባዉ። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት የአንድ ሀገር የሕዝብ ብዛት እና የቆሻሻ አወጋገድ ስልቱ ወደባህር የሚገባዉን የቆሻሻ መጠን ይወስናል። አርክቲክ ዉቅያኖስ ላይ ዉኃዉን ጠልቀዉ የሚመዘግቡ ካሜራዎችን በማሰማራት ለረዥም ጊዜያት የጀርመኑ አልፍሬድ ቬግነ የምርምር ተቋም ጥናት አካሂዷል።

ካሜራዎቹ ከዉኃዉ ዉስጥ 5,5 ሺህ ሜትር ድረስ ጠልቆ የሚገኘዉን አካባቢ ፎቶ እያነሱ መረጃ ያስተላልፋሉ። የዉኃ ስነሕይወት ተመራማሪዋ ሜላኒ በርግማን እንደሚሉት ካሜራዎቹ በላኳቸዉ ፎቶዎች እንደተረዱት የዉኃዉ ዉስጥ ይበልጥ በቆሻሻዎች የተበከለ ነዉ። ባካሄዱት ምዝገባ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2002 እስከ 2011 ባሉት ጊዜያት በዚያ የሚገኘዉ የቆሻሻ መጠን በእጥፍ መጨመሩን አስተዉለዋል። ለዚህም ዋነኛዉ ምክንያት የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ፣ የባህር ላይ መዝናኛዉ እና ዓሳ በማስገር ሂደት የሚከናወኑ ሌሎች አላስፈላጊ ተግባራት ናቸዉ።

«የዘረጋነዉ መስመር ወደሰሜን እያደር ዘልቆ እየሄደ ነዉ። በሰሜን አርክቲክ የባህር ላይ በረዶ ክምሩ እየቀነሰ ከመሄዱጋ በተገናኘም የንግድ መርከብ እንቅስቃሴዉ፣ የባህር ላይ መዝናኛዉና ለንግድ የሚሰገረዉ ዓሳ መበርከት ወደባህሩ ዉስጥ ከዚህ በፊት ያልነበሩ ነገሮች እንዲገቡ ሳያደርግ አልቀረም።»

ቀደም ሲል የተካሄዱ ተመሳሳይ ጥናቶች ባህር ዉስጥ የፕላስቲክ ቆሻሻ መኖሩንና የት እንደሚገኝ መዝግበዋል። ያም ሆኖ ግን በአብዛኛዉ በዉኃዉ ላይ የሚንሳፈፈዉን ነዉ ለመቁጠር የተቻለዉ። ሁሉም የፕላስቲክ ዉዳቂዎች የሚንሳፈፉ ባለመሆናቸዉ ከዉኃዉ ስር ክምችቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም ነበር። ከሳምንታት በፊት ይፋ የሆነዉ ጥናት ግን በየዓመቱ ወደዉኃዉ ስር እየገባ የሚከማቸዉን የፕላስቲክ ዉዳቂና ስብርባሪ መገመት አስችሏል። ለምሳሌ ፕላስቲክ የዉኃ መያዣን ብንመለከት በፀሐይ ግሎ በማዕበል ተማትቶ፣ አለያም በሻርኮችና ዓሶች ተቆርጥሞም ሆነ በመሳሰሉ የተለያዩ አጋጣሚዎች ሊሰባበር ይችላል። እንዲህ ያለዉ ስብርባሪም ባህር ዉስጥ መከማቸቱ በዉስጡ ለሚኖሩት ፍጥረታት ጠንቅ መሆኑንም ልብ ይሏል።

በዚህ ላይ ምርምር ካካሄዱት ምሁራን አንዱ ማርከስ ኤሪክሰን እንደሚሉት እሳቸዉና የሙያ ባልደረቦቻቸዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2007 እስከ 2013ዓ,ም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ጥናታቸዉን አካሂደዉ ባለፈዉ ታህሳስ ወር ይፋ ባደረጉት የምርምር ዉጤት አንድ ትልቅ የፕላስቲክ ፋብሪካ ሊኖረዉ የሚችለዉን ያህል የፕላስቲክ ስብርባሪ ክምችት በባህር ላይ አግኝተዋል። በዚህ ሁኔታም ከቀጠለም ረዥም የባህር ዳርቻ በታደሉና በተለይ ፈጣን እድገት በማሳየት ላይ ባሉ መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት በቀጣይ ስምንት እና አስር ዓመታት የዚህን አስር እጥፍ ሊሆን እንደሚችልም ስጋታቸዉን ከወዲሁ ገልጸዋል። የባህር ላይ የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ የሚንቀሳቀሰዉ ዘ ፋይፍ ጊርስ የተሰኘዉ ተቋም ተባባሪ መሥራችና ዳይሩክተር የሆኑት ኤሪክሰን፤ በአሁኑ ጊዜ ዉቅያኖሶችና ባህሮች እጅግ መርዘኛ የሆኑ በካይ ቆሻሻዎችን እየተሞሉ እንደሆነም አመልክተዋል።

በተለያየ አካጣሚ ወደባህር እና ዉቅያኖስ የሚገቡ መጠናቸዉ ያልተለካዉ የፕላስቲክ ስብርባሪዎች፣ የሞተር ዘይት ፍሳሽ፣ የፀረ ተባይ መድሃኒቶችና የመሳሰሉትን ዉኃዉ መኖሪያቸዉ የሆነዉ እንስሳት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አብረዉ መመገባቸዉ ግድ ነዉ። ሰዎች ደግሞ ዓሳዎችንም ሆነ ሌሎች የባህር ዉስጥ ፍጥረታትን ይመገባሉ። ለዚህም ነዉ «የጣልነዉን ቆሻሻ በሌላ መልኩ እንመገባለን» ሲሉ ያሳሰቡት ተመራማሪዉ፤ ምክንያቱም ወደባህር የሚጣለዉ ወይም የሚገባዉ ቆሻሻ ዞሮ ዞሮ በሌላ መልኩ ወደእኛ መምጣቱ አይቀርምና። በባህርና አካባቢዉ ከሚኖሩት እንስሳት አብዛኞቹ ያገኙትን ወደሆዳቸዉ ስለሚከቱም ቆሻሻዉ ከባህርና አካባቢዉ እስካልራቀ ድረስ ሁሌም ለችግር የተጋለጡ ናቸዉ። የስነሕይወት ምሁሩ ኒልዝ ጉዘ በአዉሮጳ የምርምር ፕሮጀክት ዉስጥ ተሳታፊ ናቸዉ። ከባህር ላይና ዳርጃ ያገኙትን የሚመገቡት እንስሳት በምድራችን የዉኃ አካል ላይ የተጋረጠዉን አደጋ ያመላክታሉ ነዉ የሚሉት፤

«ዓሶችንና ሌሎች የባህር ዉስጥ እንስሳትንና ተክሎችን እንዲሁም ከዓሳ አስጋሪዎች የሚወዳድቁ ነገሮችን መመገብ ነዉ የለመዱት። ለዓመታት ያን ያህል የሚመገቡትን ለመምረጥ አልተገደዱም ነበር። በባህር ላይ ሲንሳፈፍ ያገኙት ሁሉ ለእነሱ የሚበላ ነዉ። በዚህ ምክንያትም እነሱ እንደሚመገቧቸዉ ሌሎች ነገሮች የሚንሳፈፉትን የፕላስቲክ ዉዳቂዎችን መብላት ጀመሩ ማለት ነዉ።»

በየዓመቱም እሳቸዉና ባልደረቦቻቸዉ ፕላስቲክ ዉዳቂዎችን በመመገብ የሞቱ የባህር እንስሳትን በባህር ዳርቻዎች እያገኙ ወደምርምር ተቋማቸዉ ወስደዉ ሆዳቸዉን ሲከፍቱ የሚያገኙት ይህንኑ የፕላስቲክ ቁርጥራጭ ነዉ። አብዛኞቹም ሆዳቸዉ ዉስጥ በርካታ ፕላስቲክ በመታጨቁ ሌላ ምግብ እንዳይበሉ አግዷቸዉ በረሃብ ነዉ የሚሞቱት። ጉዘ እንደሚሉት ላስቲኩ ብቻ ሳይሆን እሱ ላይ ያለዉ መርዘኛ ንጥረ ነገርም ለመሞታቸዉ ምክንያት ነዉ።

«ከፕላስቲኩ ቆሻሻ የሚገኘዉ መርዘኛዉ ንጥረ ነገር እንደስፖልጅ ዓይነት ባህሪ ይዞ ከፕላስቲኩ የሚገኙ እንደዘይትና የመሳሰሉ በቀላሉ የማይብላሉ ነገሮችን ያከማቻል። በዚህ አጋጣሚም እንስሳቱ ተጨማሪ መመረዝ ያጋጥማቸዋል ማለት ነዉ። በመጀመሪያ እራሱ ፕላስቲኩ ይጎዳቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ ፕላስቲኩ ባህር ዉስጥ እንደመዉደቁ በዚህ በተጠቀሱ ባህሪዉ ምክንያት ከአካባቢዉ የሰባሰበዉን የተበከለ ንጥረነገር ይይዛል።»

Müllkippe Meer

በባህርና ዉቅያኖስ ዉስጥ በሚገኘዉ የፕላስቲክ ዉዳቂ የሚጎዱት ዉስጡ የሚኖሩት ፍጥረታት ብቻም አይደሉም። በተለይ በዉኃዉ ላይ እየበረሩና እየተንሳፈፉ ምግባቸዉን ከዉስጡ የሚፈልጉ የተለያዩ የአዕዋፍ ዘሮች ዓሶችን ለማጥመድ በሚጣሉ የመረቦች ብጥስጣሽ እየተጠለፉ እንደሚሰቃዩና እንደሚሞቱ በዚህም ላይ ምርምር ያካሄዱ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በተለይም በባህርና ዉቅያኖስ ዳርቻ መኖሪያ ጎጆዋቸዉን እየሠሩ የሚኖሩት የአዕዋፍ ዘሮች ለዚህ ዓይነቱ ችግር የተሃለጡ ናቸዉ። ከጀርመን በስተሰሜን በሚገኘዉ የሰሜን ባህር አካባቢ የሚኖሩ አዕዋፍ ጎጇቸዉን ለመሥራት በሚያደርጉት ሙከራ ፕላስቲኮቹ መረቦች ያልጠበቁትን አደጋ እንደሚያስከትሉባቸዉ ስለወፎች የሚያጠኑት ዮሃን ዴርሽከ ይናገራሉ፤

«ባለፈዉ ዓመት በመረብ የተጠለፉትን አሞራዎች ቆጥረን ነበር። በመረቡ ተተብትበዉ ከተያዙት ከ17ቱ 14ቱ ሞተዋል። ከመካከላቸዉ ሶስቱ ብቻ ናቸዉ ከመረቡ እስር ማምለጥ የቻሉት። ከእነሱ ሌላ በአካባቢዉ የሚገኙት ሌሎች የአዕዋፍ ዘሮችም ለዚህ ችግር የተጋለጡ መሆናቸዉን ተመልክተናል። እነሱም በዚሁ መረብ ተሳስረዉ ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ። በአካባቢዉ ቆጠራችንን ስናካሂድ ያጋጠሙን በሙሉ በዚሁ መንገድ ሞተዋል።»

ወፎቹ ጎጇቸዉን የሚሠሩባቸዉ አካባቢዎች ገደላማ በመሆናቸዉ እሳቸዉና ባልደረቦቻቸዉ እዚያ ሲሄዱ በመረቦቹ ተወታትበዉ ቢመለከቷቸዉም አንዳንድ ጊዜ ሊያድኗቸዉ አይችሉም። የተለያዩ ሃገራት ከፕላስቲክ የተሠሩ የእቃ መያዣም ሆነ ሌሎች ነገሮችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲታገሉ ይስተዋላል። ፕላስቲክ የተጠላዉ በቀላሉ ከአፈር ጋ ተዋህዶ ወደሌላ ነገር ስለማይለወጥና ስለማይጠፋ ነዉ። ፕላስቲክን እቃ መያዣን በማገድ አፍሪቃዊቱ ትንሽ ሀገር ሩዋንዳ ተሳክቶላት በምሳሌነት መጠቀስ ከጀመረች ዓመታት እንደዋዛ አልፈዋል። ወደኪጋሊ በአዉሮፕላን የሚጓዙ በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ ይህ ማሳሰቢያ ይሰጣቸዋል። ሩዋንዳ ዉስጥ ፕላስቲክ የእቃ መያዣ አይፈቀድም። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2008ዓ,ም ሌላዉ ዓለም ፌስታል መጠቀምን ለመቀነስ ገና ቀረጥ ስለመጣል ሲግደረደር የምሥራቅ አፍሪቃ ትንሿ ሀገር ሕግ አዉጥታ አገደች። በአየርም ሆነ በምድር ወደሩዋንዳ የሚገባ ማንኛዉም ሀገር ጎብኚ ቅድሚያ የሚጠየቀዉ በጓዙ ዉስጥ የፕላስቲክ እቃ መያዣ እንዳለዉ ነዉ። ይህ ጥንቃቄ ለኪጋሊም ሆነ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጽዳት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ወደዚያ የተጓዙ ሁሉ የሚመሰክሩላት ሀቅ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic