ፓኪስታን እና የአሸባሪዎች ጥቃት | ዓለም | DW | 09.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ፓኪስታን እና የአሸባሪዎች ጥቃት

በፓኪስታን የካራቺ ከተማ በሚገኘው የጂና ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የታሊባን ሚሊሺያዎች ትናንት በጣሉት ጥቃት እና ጥቃቱን ለማብቃት የአየር ማረፊያው ፀጥታ ኃይላት በወሰዱት አፀፋ ርምጃ ቢያንስ 28 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

የፀጥታ ኃይላቱ መሪ ሜጀር ጀነራል ሪዝዋን አክታር እንደገለጹት ፣ ከተገደሉት 28 መካከል አስሩ የታሊባን ሚሊሺያዎች ናቸው።

« አስሩ አሸባሪዎች አምስት አምስት በመሆን ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች ነበር ወደ አየር ማረፊያው የገቡት፣ በአንፃራቸው አፀፋ ርምጃ መውሰድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ሰባት የፀጥታ ኃይላት ተሠውተውብናል። በጥቃቱ አንድም አይሮፕላን አልተጎዳም። ጥቃቱ የተጣለው የዕቃ መጫኛ እና ማራገፊያ አካባቢ ነው። አሸባሪዎቹ የዕቃ ማከማቺያውን መጋዘን በእሳት አጋይተውታል። አሸባሪዎቹ የተገደሉትም እዚሁ መጋዘን አካባቢ ነው። »

በተያያዘ ዜናም፣ ከኢራን ጋ በሚያዋስነው የፓኪስታን ድንበር ላይ ትናንት ማምሻውን ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች ራሳቸውን በቦምብ ባነጎዱበት ጥቃት ቢያንስ 24 ሰዎች መገደላቸውን ያካባቢ መገናኛ ብዙኃን አስታወቁ። ከሟቾቹ መካከል አስር ሴቶች ሕይወታቸውን ያጡበት ጥቃት የተጣለው በምዕራብ ባሉቺስታን ግዛት የታፍታን ከተማ የሺአ ምዕመናን ባረፉበት አንድ ሆቴል ነው።

ፓኪስታናውያኑ ምዕመናን በኢራን ቅዱስ ቦታዎችን ጎብኝተው የተመለሱ ነበሩ። ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ባይኖርም፣ ያካባቢው ባለሥልጣናት ፅንፈኛ ሱኒዎችን እንደሚጠረጥሩ ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ