1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓብሎ ሩይዝ ፒካሶ፤ ከ50 ዓመት በኋላ ሲታወስ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12 2015

ከሀምሳ አመታት በፊት በጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 8 ቀን 1973 ዓ/ም ይችን ምድር የተሰናበተው ስዓሊ እና ቀራፂ ፓብሎ ሩይዝ ፒካሶ በአስደናቂ ስራዎቹ እየታወሰ ነው። ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የባህል ዝግጅቶች የታዋቂው የጥበብ ሰው ህልፈት 50ኛ አመት«ፒካሶ ከ1973-2023» በሚል መሪቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተዘከረ ነው።

https://p.dw.com/p/4PyI9
Frankreich Antibes | Pablo Picasso neben seinem Bild der Friedenstaube
ምስል UPI/dpa/picture alliance

የፒካሶ 50ኛ የሙት ዓመት


ከሀምሳ አመታት በፊት በጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 8 ቀን 1973 ዓ/ም  ይችን ምድር የተሰናበተው ስዓሊ እና ቀራፂ ፓብሎ ሩይዝ  ፒካሶ  በአስደናቂ  ስራዎቹ  እየታወሰ ነው። ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የባህል ዝግጅቶች የታዋቂው የጥበብ ሰው ህልፈት 50ኛ አመት«ፒካሶ ከ1973-2023» በሚል መሪቃል  በተለያዩ ዝግጅቶች እየተዘከረ ነው። ዝግጅቶቹ በትውልድ ሀገሩ  ስፔን፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን እና በአሜሪካ እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ጭምር የሚካሄዱ ናቸው። የዛሬው የባህል መድረክ ዝግጅትም ይህንን የ20ናው ክፍለ ዘመን ስመጥር የጥበብ  ሰው ይዘክራል። 
በደቡባዊ ስፔን ማላጋ በምትባል ከተማ በጎርጎሪያኑ ጥቅምት 25 ቀን 1881 የተወለደው ፒካሶ፤ አባቱ ዶን ጆሴ ሩይዝ ብላስኮ በዚች ከተማ ወፎችን እና እንስሳትን በመሳል የሚተዳደሩ የጥበብ ሰው ነበሩ። ስዕልን ከመተዳደሪያነት ባለፈ አሁን ዓለም የሚካብረውን ልጃቸውን ጨምሮ በርካቶችን አስተምረዋል።
ስፔናዊው ሠዓሊ እና ቀራፂ ፒካሶ ከአባቱ ስዕል መማር የጀመረው ገና በሰባት ዓመቱ ሲሆን፣የመጀመሪያ ስዕሉን የሰራው በዘጠኝ ዓመቱ ነው።ስዕሉም፤ «ትንሹ ተዋጊ በሬ» (The Little Bullfighter) በሚል በሀገሩ ስፔን የሚካሄድ የበሬዎች ፍልሚያን ከተመለከተ በኋላ የሰራው የዘይት ቅብ ስዕል ነበር።
ፒካሶ በ13 አመቱ ደግሞ አባቱ በሚያስተምሩበት ኤስኮላ ዴ ላ ሎትጃ በተባለ የባርሴሎና የስነ ጥበባት ትምህርት ቤት መማር ጀመረ። ከሁለት አመት በኋላም «የመጀመሪያው ቁርባን» የተሰኘውን ትልቅ የዘይት ሥዕል በመሳል  ስራውን በከተማዋ በሚካሄድ አውደ ርዕይ ላይ አቀረበ።
በዚህ ሁኔታ ረጅሙን የ70 ዓመት የጥበብ ጉዞ የጀመረው ፓብሎ ፒካሶ፤ከ140 ዓመታት በፊት ሲወለድ ውስብስብ ችግር አጋጥሞ እንደነበር ይገልፃሉ። በፒካሶ የትውልድ ከተማ በሚገኝ ሙዚየም ሃላፊ የሆኑት  ሆሴ ማሪያ ሉና።
«ቀላል አልነበረም። አጎቱ ሳልቫዶር ሐኪም ነበር። እና ፒካሶ ሲወለድ በአዋላጅነት ይረዳ ነበር።መጀመሪያ ላይ ህፃኑ አይተነፍስም ነበር። ቆዳውም  ሰማያዊ ሆኖ ነበር። አጎቱ ሳልቫዶር ከወሊድ በኋላ  ሲጋራ እያጨስ ነበር እና ሁሉንም ነገር ከሞከረ በኋላ የሲጋራ ጭስ ወደ ልጁ አቅጣጫ ለመልቀቅ ሞከረ። በዚያ ወቅት ታዲያ  አዲስ የተወለደው ህፃን ልጅ  ምላሽ ሰጠ።»
በ 1897 ዓ/ም ማድሪድ ወደሚገኘው ሪል አካዳሚ ዴ ቤላስ አርቴስ ደ ሳን ፈርናንዶ ተዛወረ ፣ነገር ግን በፕራዶ በሚባለው ሙዚየም የሥነጥበብ ስራዎችን ማጥናት መረጠ።በዚያም በዲያጎ ቬላዝኬዝ ፣ ሬምብራንት ፣ ጃን ቨርሜር እና ፍራንሲስኮ ጎያ በተባሉ ታዋቂ ሰዓሊያን የተሰሩ ሥዕሎችን በቅርበት የመመልከት ዕድል አገኘ። በ1990ዎቹ ደግሞ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ አመርቷል።አብዛኛውን የህይወት ዘመኑንም በዚያው አሳልፏል።
የፒካሶ ጥበባዊ ሕይወት በተለያዩ ደረጃዎች የሚከፈል ሲሆን፤የመጀመርያው ምዕራፍ ሰማያዊ ዘመን በመባል የሚታወቅ እና ከ1901 እስከ 1904 ድረስ የቆየ ሲሆን፤ ወዳጁ ስፔናዊው ባለቅኔ ካርልስ ካሳጌማስ ራሱን ማጥፋቱን ተከትሎ የሰራቸው  ስዕሎች ናቸው። በዚህ ወቅትም የመጀመርያ ሥዕሉን በ19901 ዓ/ም የጠለቀ ስሜቱን በሚያሳይ ሰማያዊ ቀለም ያጠላበት  «የካሣጅማስ ሞት» የተባለ ስዕሉን ሰርቷል።
ሁለተኛው የፒካሶ ዘመን የሮዛ ወቅት የሚባለው እና ከ1904-1906 ያለው ጊዜ ሲሆን በዚህ ወቅት  በሮዝ፣ በቀላል ሰማያዊ እና ብርቱካንማ ቀለሞች በመሳል ይታወቃል። «የሀርሊከን ቤተሰብ» እና «ሁለቱ ወንድማማቾች»የተባሉት ስዕሎች ይጠቀሳሉ። በዚያው ዓመት፣ ብዙም ሳይቆይ የአሜሪካዊቷን ፀሀፊ የገርትሩድ ስታይንን ምስል ሰርቶ አጠናቀቀ።

Pablo Picasso | Foto 1904 mit Widmung
ምስል akg-images/picture alliance
BG Gemälde Pablo Picasso
ምስል Peter Barritt/Avalon/picture alliance

ፒካሶ በዚህ ሁኔታ በልጅነቱ ከሚያውቀው  የ1890ዎቹ የአሳሳል ስልት በመውጣት በ1910ቹ የመጀመሪያ አጋማሽ  የ«ሰማያዊ»እና የ«ሮዝ ዘመን» ወደሚባለው ልዩ ስልት ፊቱን አዞረ። በኋላም፤ «ኩብዚም» ወደተባለዉ ከፍተኛ ረቂቅ አሳሳሉ አዘነበለ።
በዚህ መንገድ የተለያዩ ቅርጾችን በአንድ ስዕል ላይ በተዘበራረቀ ሁኔታ ማስቀመጥ ላይ ያተኮረ ኪዩቢዝም የተባለ አዲስ የአሳሳል ዘዴ አብዮት አመጣ። ኪዩቢዝም የተለያዩ ቁሶችን በፈዛዛ ቀለሞች ብዙ ዕይታ ወዳላቸው ቅርፆች በመቀየር የሚሰራ ስዕል ሲሆን በእውነታው ዓለም ግን የማናየው ነው።በዚህ መንገድ «ጊታር» እና «ሶስቱ ወንድማማቾች»የተባሉ ስዕሎቹ ተጠቃሽ ናቸው።
በማላጋ ስፔን በፒካሶ ሙዚየም የባህል እንቅስቃሴ ሀላፊ ማሪያ ጆሴ ቫልቫርዴ እንደሚሉት ይህ የፒካሶ አዲስ የአሳሳል ዘይቬ የህዳሴ ዘመን ልማዶችን ሰብሯል።
«ኩቢዝም የተባለው የአሳሳል ዘዴ ከህዳሴ ዘመን ጀምሮ የነበሩ ወጎችን እና ልምዶችን  እንዲቋረጡ አድርጓል።እነዚህ ሥዕሎች ልክ በመስኮት በኩል እንደሚታዩ የተዋሃደ ዕይታ አላቸው። ፒካሶ ብዙውን ጊዜ በኪዩቢክ የስዕል ሥራዎቹ ውስጥ ጭምር ፤በአንድ ሥዕል ውስጥ የተለያዩ ዕይታዎችን ያሳይ ነበር።»
ኩብዚም፣ በርካታ የዘመኑን የጥበብ ሰዎች የማረከ፣ በዘመናችንም በርካታቶች ላይ ተፅዕኖዉን ያሳረፈ ስልት ነዉ። ሞሪስ ሻፒሮ የተባሉ የፓርክ ዌስት የስዕል ቤተ-መዘክር ኃላፊ ፒካሶን ሲገልፁት፤
«ከፒካሶ በፊት ጥበብ ነበር።ከፒካሶ በኋላም ጥበብ አለ። ግን አንድ ዓይነት አይደለም፣ ሙሉ በሙሉ ተለዉጧል ማለት ተገቢ ይመስለኛል»
ፒካሶ፤የሴቶችን  በተዘበራረቀ ሁኔታ በመሳልም ቀደም ሲል የነበረውን የስዕል  ፅንሰ-ሀሳቦች በመስበር የኩቢዝም ፈር ቀዳጅ ስራ ሆኖ እንዲታይ አድርጓል።በእነዚያ አመታትም ከጆርጅ ብራክ ጋር በመሆን ፒካሶ ኩቢዝምን የበለጠ አሳድጓል። በእነዚህ አወዛጋቢ ስራዎቹም የዘመናዊ ጥበብ ኮከብ በመሆን በዓለም ዙሪያ ታዋቂነትን አትርፏል። ያም ሆኖ በወቅቱ ሴቶችን በስዕሉ ይገልጽበት የነበረበው መንገድ በአሁኑ ወቅት በመብት አቀንቃኞች ዘንድ እየተተቸ ይገኛል።
ፒካሶ፤ጦርነትን በሚቃወሙ ስዕሎቹም ይታወቃል።ከነዚህ ስራዎቹ መካከልም በ1937 የሰራው «ጊርኒካ»የተሰኘው ስዕሉ በስፋት ይታወቃል።ይህ ስዕል የፀረ-ጦርነት መግለጫ ያለው ሲሆን፤በጄኔራል ፍራንኮ ትዕዛዝ በሰሜናዊ ስፔን በባስክ ከተማ ለደረሰው የቦምብ ጥቃት ምላሽ የሰጠ ስዕል ነው።
የማላጋ የቱሪዝም መመሪያ ፍራንሲስ አጊላር  ስዕሉ የተሳለበትን ሁኔታ እንዲህ ያስታውሱታል።«በጎርጎሪያኑ 1937 ዓ/ም በፓሪስ ለተካሄደው ለዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ እንዲሠራ ስፔን ለፒካሶ ሀላፊነት  ሰጠችው። በዚያ ዓመት በእርስ በርስ ጦርነት ስፔን የምትገኘው ገርኒካ ከተማ በቦምብ ተደበደበች። እና ፒካሶ ይህን ጥፋት እንደ በሬ ፍልሚያ ነበር የሚገልጸው።ይህ ድራማ እና ጉልበተኝነት በበርካታ ቦታዎች እና ስፔን ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ ተከናውኗል።»
ሌሎች የፀረ-ጦርነት ስራዎች መካከልም «ዘ ቻርኔል ሃውስ» ከ1944-45 ለተካሄደው የናዚ የዘር ማጥፋትን የተመለከተ እና «እልቂት በኮሪያ» እንዲሁም ልጅነቱ ጀምሮ ይስለው የነበረው የነጻነት ርግቦች ይገኙበታል። የካሳ ናታል ሙዚየም ዳይሬክተር የሆኑት ጆሴ ማሪያ ሉና እንደሚሉት ይህ የርግብ ስዕል የዓለም የሰላም ምልክት ሆኗል።  
«በመሠረቱ የፒካሶ አባት የሰሯቸው  የርግብ ሥዕሎች በማላጋ እና በአካባቢው ገበያ በጣም ተወዳጅ ነበሩ። እና እርግቦች በፒካሶ ስራዎች ውስጥም ይገኛሉ።. ማላጋ የመጣው የፓብሎ ፒካሶ የእርግብ ስዕል በጎርጎሪያኑ 1949 ዓ/ም በፓሪስ በተካሄደው የዓለም የሰላም ጉባኤ ላይ ምልክት ሆኖ  ታየች። እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ  የዓለም የሰላም ተምሳሌት ሆናለች።»
ፒካሶ፤ በ91 አመቱ በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት ጊዜ ስራውን ሲያከናውን የቆየ እና እስከ እርጅና ጊዜው ድረስ ውጤታማ የሆነ የክፍለ ዘመኑ ጥበበኛ ነው። በሚያዝያ 8 ቀን 1973 ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይም  ወደ 150,000 የሚጠጉ የሥዕል፣ የቅርጻ ቅርጽ፣ የሕትመት እና የጽሑፍ ስራዎችን በቅርስነት ትቷል። እነዚህን ስራዎቹን ለመዘርዘር እና ለማደራጄትም ድፍን  ሰባት ዓመታትን ፈጅቷል።በቅርቡም ከፊል ሥራዎቹ  በፓሪስ ፒካሶ ሙዚየም እንዲቀመጥ ተደርጓል።
እነዚህን ዘመን ተሻጋሪ  ስራዎቹን ለመዘከርም ዓመታት በፊት በትውልድ ቦታው ስፔን ማላጋ የመታሰቢያ ሀውልት ቆሞለታል።

Spanien Malaga | Touristen neben Statue von Picasso
ምስል Jesus Merida/ZUMA/picture alliance
BG Gemälde Pablo Picasso
ምስል Lev Radin/Pacific Press/picture alliance
Picasso Gemälde-Detail von Les Demoiselles d'Avignon" 1907
ምስል Peter Barritt/Avalon/picture alliance

ሀውልቱም እስከ አስር አመቱ ቦርቆ ባደገበት የመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ መሆኑን የማላጋ የቱሪዝም መመሪያ ፍራንሲስ አጊላር፣ ይገልፃሉ።
«ፒካሶ እዚህ አቅራቢያ ይኖር ነበር። በህይወቱ የመጀመሪያዎቹን አስር አመታት እዚህ አሳልፏል። እና በዚህ አካባቢ ተጫውቶ ነው ያደገው። አንዳንድ ጎረቤቶች እንኳን እሱ ወለሉ ላይ ስዕል ይስል ነበር ይላሉ።  እነዚህ የመጀመሪያ የጥበብ ስራዎቹ ይሆናሉ ብሎ መናገር ይቻላል።»

 

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ