ፓሪስ፤ ጥቃት አክሻፊዎች በክብር ተሸለሙ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ፓሪስ፤ ጥቃት አክሻፊዎች በክብር ተሸለሙ

ባለፈዉ ሳምንት ከአምስተርዳም ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ይጓዝ የነበረ ፈጣን ባቡር ላይ ካላሽኒኮቭ የታጠቀ ግለሰብ ሊያደርስ የነበረን ጥቃት ያከሸፉ ሶስት አሜሪካዉያንና አንድ እንግሊዛዊ ለፈፀሙት ድፍረት የተሞላዉ ተግባር የፈረንሳይን ከፍተኛ ማዕረግን አገኙ።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦሎንድ ለጥቃት አክሻፊዎቹ የከፍተኛ ማዕረግ ሜዳልያ የሸለሙት በፓሪሱ የኤሊዜ ቤተ-መንግሥት ዉስጥ ነዉ። አንድ ማንነቱ እንዲታወቅ ያልፈለገ የ 28 ዓመት ፈረንሳዊም የፈረንሳይን ከፍተኛ የክብር ሜዳልያ መቀበሉ ተመልክቶአል። ከአራቱ ተሸላሚዎች ሁለቱ የአሜሪካ ወታደሮች እንደሆኑም ታዉቋል። ጥቃት አክሻፊዎቹ ስለራሳቸዉ ሕይወት መጥፋት ሳያስቡ የንፁሃን ደም ከመፍሰስ ማትረፋቸዉን ፕሬዚዳንት ኦሎንድ በሥነ-ስርዓቱ ላይ አወድሰዋል። አራቱ ተሸላሚዎች አዩ ኧሊ ካዛኒ የተባለዉ ሞሮኮዋዊ ያቀደዉን ጥቃት ነዉ ያከሸፉት።

ከፈረንሳይ ፓሪስ፥ሆላንድ አምስተርዳም ተመላላሽ ባቡር ላይ ክላሽንኮቭ፣ የእጅ ሽጉጥና ቢላዋ የታጠቀ የ26 አመት ሞሮኳዊ የከፈተው ጥቃት በመንገደኞች ከሸፈ። ፈጣኑ ባቡር ዓርብ ነሐሴ 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. ማምሻውን ከቤልጂየም ድንበር ወደ ፈረንሳይ እንደገባ ነበር ጥቃቱ የተሰነዘረው።

ፓሪስ አቅራቢያ በጸረ-ሽብር ኃይል ቁጥጥር ስር የሚገኘው የ26 አመቱ ሞሮኳዊ በባቡሩ ላይ ተኩስ በከፈተበት ቅጽበት በሦስት አሜሪካውያን ትግል ተይዟል ተብሏል። የወጣቱን ጥቃት ካከሸፉት አሜሪካውያን ኹለቱ ከግዳጅ ውጪ የነበሩ ወታደሮች መኾናቸውም ተዘግቦ ነበር።

ከአምስተርዳም ወደ ፓሪስ በመጓዝ ላይ በነበረው ፈጣን ባቡር ላይ የተያዘው ተጠርጣሪ ወደ ሶርያ ተጉዞ እንደነበርና በፈረንሳይና ስፔን የጸጥታ ተቆጣጣሪዎች ክትትል ውስጥ እንደነበረም ተጠቅሷል። የስፔን የስለላ ድርጅት ወጣቱ 'የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ አባል በመሆኑ ክትትል እንዲደረግበት ለፈረንሳይ አቻዎቻቸው ጠቁመው እንደነበር የፈረንሳይ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከተጠርጣሪው በተተኮሰ ጥይት የቆሰሉት ስፔንሰር ስቶን የተባለ የአሜሪካ አየር ኃይል ባልደረባና አንድ ሌላ መንገደኛ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ተጠርጣሪው 554 መንገደኞች የጫነው ባቡር ከሰሜናዊ የፈረንሳይ ከተማ አራስ ደርሶ ሲቆም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎዋል። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ሊደርስ የሚችለውን አሰቃቂ ጥቃት ያከሸፉትን ወጣቶች አመስግነዋል። በሚቀጥሉት ቀናትም ጀብድ የፈፀሙትን ወጣቶች በቤተመንግስታቸው አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ተዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተዛማጅ ዘገባዎች