ፓሪስ፤ የሽብር ጥቃቱ አቀነባባሪ ተገደለ | ዓለም | DW | 19.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ፓሪስ፤ የሽብር ጥቃቱ አቀነባባሪ ተገደለ

ባለፈዉ ዓርብ ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ የደረሰዉን የሽብር ጥቃት በማቀነባበር የሚጠረጠረዉ አብደልሀሚድ አባዑድ መገደሉን ፖሊስ ዛሬ አረጋገጠ። የፈረንሳይ ፖሊስ ትናንት በሰሜን ፓሪስ አካባቢ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ላይ ባካሄደዉ ከበባ በነበረዉ የተኩስ ልዉዉጥ ነዉ ተፈላጊዉ የተገደለዉ።

ትዉልዱ ከሞሮኮ የሆነዉ ይህ ግለሰብ ሶርያ ዉስጥ ሰልጥኖ እንደመጣ እና ባለፈዉ ዓመት ጥር ወር የቤልጅየም ፖሊስን ሊገድል ሞክሮ እንደከሸፈበትም ተገልጿል። በወቅቱ አንዲት ሴት አጥፍቶ ጠፊ የታጠቀችዉን የፈንጂ ቀበቶ ካነጎደች እና ሰባት ሰዓት ከፈጀዉ የተኩስ ልዉዉጥ በኋላም ቢያንስ ሁለት አስከሬን በስፍራዉ መገኘቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። የእጅ አሻራን የሚመረምሩ ባለሙያዎች ከሟቾቹ አንዱ ተፈላጊዉ የቤልጂየም ዜጋ መሆኑን መለየታቸዉንም አመልክቷል።

Frankreich Premierminister Valls Rede im Parlament

ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ቫልስ

ትናንት ከተካሄደ ከበባዉና የተኩስ ልዉዉጥ በኋላ የሀገሪቱ የምክር ቤት አባላት ዛሬ በፈረንሳይ የተደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እንዲራዘም ወስኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፖሊሶች እና የፀጥታ ኃይሎች መሣሪያቸዉን ከሥራ ሰዓት ዉጭም ይዘዉ እንዲንቀሳቀሱ እና የፈረንሳይ መንግሥትም የኢንተርኔት እና የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ግንኙነቶችን እንዲዘጋም ይፈቅዳል። ምክር ቤቱ አዋጁን ሲያራዝም ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ቫልስ አሁንም ፈረንሳይ ምናልባትም የኬሚካል ጦርመሳሪያ አደጋ እንደሚያሰጋት አሳስበዋል።

«አሁንም የኬሚካል ወይም ባዮሎጆካል ጦር መሣሪያ እንደሚያሰጋን እናዉቃለን። ድንበር አልፎ ሊሄድ የሚችል አዲስ የጦርነት ዓይነት እያየን ነዉ። በእስላማዊ መንግሥት ወይም በአልቃይዳ የግንኙነት ሰንሰለት አማካኝነት ከረዥም ርቀት የሚካሄድ ጦርነት። በዚህ አማካኝነት ተዋጊዎች ይመለመላሉ፤ ይሰለጥናሉ፤ ንጥረነገሮች ይቀመሙና ትዕዛዝ ይተላለፋል። በአንድ ትዕዛዝ ብቻም ትርምሱ ተደራጅቶ ይጀመራል።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ