1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያን በሕክምና የዕውቀት ሽግግር ለማገዝ የሚጥረው «ፒፕል ቱ ፒፕል»

ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2017

ኢትዮጵያን በሕክምና የዕውቀት ሽግግር ለማገዝ የሚጥረው ዮናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው «ፒፕል ቱ ፒፕል» የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ከሰሞኑ 25ኛ ዓመቱን አከበረ።

https://p.dw.com/p/4m9Uk
ፒፕል ቱ ፒፕል
ዮናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው «ፒፕል ቱ ፒፕል» የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን የጤና ጥበቃ አገልግሎት በሰው ሠራሽ አስተውሎትና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ለማሻሻል፣ በዕውቀት ሽግግር እያገዘ እንደሚገኝ አስታውቋል።ምስል David Herrarez/Zoonar/picture alliance

ፒትፕ ቱ ፒፕል

ዮናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው «ፒፕል ቱ ፒፕል» የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን የጤና ጥበቃ አገልግሎት በሰው ሠራሽ አስተውሎትና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ለማሻሻል፣ በዕውቀት ሽግግር እያገዘ እንደሚገኝ አስታወቀ። ድርጅቱ 16ኛ መደበኛ ጉባኤውን ሰሞኑን ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘውና አርሊንግተን በተባለችው ከተማ ውስጥ አካሄዷል። 

የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ በእውቀት ሽግግር ለመደገፍ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተቋቁመው «ፒፕል ቱ ፒፕል»፣ 16 ኛ ዓመት ጉባኤውን እና 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ቅዳሜ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 2017 ዓ.ም አካሄዷል።

ጉባኤው፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይንም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል፣ በዋናነት በበቂ የዳታ (መረጃ) ማዕከላት አስፈላጊነት ላይ መምከሩን፣ የድርጅቱ መስራችና ፕሬዚዳንት ዶክተር እናውጋው ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል።

የዳታ ማዕከላት አስፈላጊነት

«ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረት ልማት በጣም ወሳኝ ነው። መሠረተ ልማቱ ብቻ ደግሞ ሳይሆን ዳታን ማንበብ ይህም ራሱን የቻለ በጣም አስፈላጊ የሆነ ቦታ ነው፤ ለሂደቱ ተገቢ የሆነ ጉዳይ ነው።»

ጉባዔው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የህክምና አገልግሎት፣ ቅልጥፍናንና፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ህክምና ለማዳረስ በሚኖረው አስተዋጽዖ ላይም መክሯል። የቦርድ ሊቀመንበሩ ዶክተር አንተነህ ሃብቴ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን አፍሪቃ ውስጥ በጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የተካሄደውን ዉይይት በተመለከተ ሲያስረዱ፤ «ባለፈው በዲጂታል ጊዜ ወደኋላ እንደቀረነው፣ አሁን በዚህም ወደኋላ መቅረት የለብንም፣ ምክንያቱም መምጣቱ የማይቀር ነው። ስለዚህ ለእኛ እንደሚሠራ አድርገን እንዴት ነው መጠቀም የምንችለው የሚለው ጥያቄ ላይ ነው ብዙ ያተኮርነው።»

 የጤና ትምህርት ዕውቅና በኢትዮጵያ

ፒፕል ቱ ፒፕል፤ በኢትዮጵያ የህክምና ደረጃዎችን ከፍ ለማድረግ እንዲቻል፣ በህክምና ትምህርት ዕውቅና አሰጣጥ ላይም ትኩረት መስጠቱን ፕሬዝደንቱ ዶክተር እናውጋው ያስረዳሉ።

«በክሪዲቴሽን(እውቅና )በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች፣ ወርልድ ሜዲካል ፌዴሬሽን የሚባለው ከእሱ እውቅና የሚያገኙበት አካሄድ፣ ፒፕል ቱ ፒፕል ከጤና ጥበቃ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሃኪሞች ማኀበር ጋር በመተባበር ወደፊት እውቅና ከሌለው የኢትዮጵያ የህክምና ትምህርት ቤቶች የሚጨርሱት ልጆች፣ እዚህ አሜሪካ መጥተው መፈተን ስለማይቻል እንዲቻል ለማድረግ እያገዘ ነው ፒፕል ቱ ፒፕል።»

ፒፕል ቱ ፒፕል፣ የሚሰጠው እገዛ

ድርጅቱ ባለፉት 25 ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ውስጥ የጤናውን ዘርፍ ለማገዝ እያደረገ ያለውን ትብብር በተመለከተ፣ የቦርድ ሊቀመንበሩ ዶክተር አንተነህ ሲያስረዱ፤ «በርከት ካሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የህክምና ተቋማት ጋር በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሠርተናል። ይህንንም ስንሠራ እኛና አባሎቻችን ከእኛ ጋር የሚሠሩ ኢትዮጵያን የሚወዱ የውጭ ሃገር ሰዎች ጨምርን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያሉትን ጨምረን ነው ኢትዮጵያ በመሄድ የቴክኖሎጂ ልውውጥ በማድረግ፣ እዚያ ያሉትም እዚህ እንዲመጡ በማድረግ አንድ ላይ ስንሠራ ቆይተናል።»ብለዋል።

የዕውቅና ሽልማት

ድርጅቱ በጤናው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰባት ሰዎች እውቅና ሰጥቷል። የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማ ሲንጋ ለጉባዔተኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለፒፕል ቱ ፒፕል የ25 ዓመታት ውጤታማ ሥራ እንዲሁም በጤና አጠባበቅና በህክምና ትምህርት የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ግለሰቦች የምስጋና እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ