ፑንትላንድን የመታዉ ማዕበል | አፍሪቃ | DW | 13.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ፑንትላንድን የመታዉ ማዕበል

የሶማሊያዋ ራስ ገዝ ግዛት ፑንትላንድን በሳምንቱ መጨረሻ በመታዉ ኃይለኛ ማዕበል የሞቱት ሰዎች ቁጥር 300 መቶ ሊደርስ ይችላል ሲል መንግስት ስጋቱን እየገለጸ ነዉ። መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን በማዕበሉ ለተጎዱ አካባቢዎችም ዓለም ዓቀፍ ርዳታ ጠይቋል።

በምስራቅ አፍሪቃ በዚህ ወቅት ያልተለመደ የአየር ንብረት መኖሩ ነዉ የሚገለጸዉ። ፑንትላንድን በመታዉ ማዕበል የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት የተንቀሳቀሰዉ ዓለም ዓቀፉ የቀይ መስቀል ባልደረባ እንደሚሉትም በአንዳንድ አካባቢ እንደዉም የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች ወርዷል። የመሬት መናድን ያስከተለዉ ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ ፑንትላንድን የመታዉ ይህ ማዕበል ያጠፋዉ የሰዉ ህይወትም ሶስት መቶ ሊደርስ ይችላል ሲል መንግስት ስጋቱን እየገለጸ ነዉ። ከሰዉ ህይወት በተጨማሪም ከብቶችና ቤቶችንም ጠራርጎ ከባህር መጨመሩ የተነገረለት ማዕበል፤ ባልተለመደ ከባድ ዉሽንፍር የታጀበ መሆኑም ተመልክቷል። በሶማሊያ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት FAO ጽህፈት ቤት እንደሚለዉም በቀጣይም ከባድ ዝናብ ሊጥል ይችላል።

እናም ነፍሳቸዉ ለተረፈዉ ወገኖች የአስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልግ ነዉ FAO ያመለከተዉ።

የዓለም ዓቀፍ ቀይ መስቀል የኬንያ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፋጡማ አብደላ በበስፍራዉ የሚገኙ የድርጅታቸዉ ባልደረቦች በማዕበል ወደተመቱት አካባቢዎች ለመድረስ መቸገራቸዉን ይናገራሉ።

«አብዛኞቹ መንገዶች በማጥና በጎርፍ በመሸፈናቸዉ ምክንያት ለመጓጓዝ አዳጋች ሆነዋል። ክፉኛ የተጎዳዉ አካባቢ ሶስት ጎንዮሽ በሆነዉ በሰሜን በባንደርቤይላ እና ወደደቡብ የባህር ዳርቻ የሚገኘዉ ኤይል ከተማ መካከል በግምት 400 ስኩየር ኪሎሜትር ገደማ ነዉ። በቀርዶና ገረዌ መከካል የሚገኘዉ ዱንገየሮ ከተማም እንዲሁ ተጎድቷል።»

የሟቾቹ ቁጥር አሁን 140 መድረሱን ያረጋገጡት የፑንትላንድ የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር አብዱላሂ አህመድም እንዲሁ ወደተጎጂዎቹ ለመድረስ የሚቻልበት ብቸኛዉ መንገድ የአየር በረራ ብቻ እንደሆነ ነዉ የተናገሩት። እናም ጉዳት ለደረሰባቸዉ ወገኖች የንፁህ ዉሃ፣ በቀላሉ የማይበላሽ ምግብ፤ መድሃኒት፤ ብርድ ልብስና ለመጠለያ የሚሆን ቁሳቁስ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። ቀይመስቀል በበኩሉ በትክክል ለተጎጂዎቹ የሚፈለገዉን የሚያጠና ቡድን መላኩን ነዉ የገለፀዉ፤

«ዓለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ለድረሱልን ጥሪዉ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነዉ፤ ሆኖም ያንን የሚያደርገዉ እዚያ ሁኔታዉን ለማጥናት የላክነዉ ቡድን በሚያቀርብልን መረጃ መሠረት ይሆናል። እናም የአደጋዉን መጠን አስቀድመን ማወቁ ለእኛ አስፈላጊ ነዉ። ከዚህም ምን እየተካሄደ እንደሆነ በመረዳት ተገቢዉን ምላሽ ለመስጠት እንችላለን።»

የዓለም ዓቀፍ ቀይ መስቀል የኬንያ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፋጡማ አብደላ ይህን ቢሉም ግን ባፋጣኝ ሊቀርቡ የሚችሉ ተፈላጊ ነገሮች ዝግጁ መሆናቸዉንም አመልክተዋል።

«ለጊዜዉ ጥቂት ምግብ፤ አስፈላጊ የሆኑ የቤት ቁሳቁሶች፤ ማለትም እንደመመገቢያ እቃዎች እና የመሳሰሉት እንዲሁም ልብሶች ተዘጋጅተዋል። ቡድናችንም ለማከፋፈል ይህ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል፤ የአደጋዉ መጠን በትክክል የሚያመለክተዉ መረጃ እንደደረሰንም ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ ኃይል እናሰማራለን።»

ፑንትላንድ ባለፈዉ ነሐሴ ወር ስልጣንና የዉጭ ርዳታ አያጋራኝም በሚል ከመቃዲሾ መንግስት ጋ የነበራትን ግንኙነት ማቋረጧን አስታዉቃለች። እንዲያም ሆኖ ከሃማ ዓመታት በላይ የወረደባት ጦርነት ያደቀቃት ሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼኽ ሞሐመድ ሀገራቸዉ በማዕበሉ ለተጎዱ አካባቢዎች አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደምትለግስ አስታዉቀዋል።

በባህር ማዕበል የተረዳዉ ኃያል ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍ መቶ ሺህ ገደማ ከብቶችንና የዓሣ ማስገሪያ ጀልባዎችን ጠራርጎ ህንድ ዉቅያኖስ ከቷል። FAO ከሶማሊያ ህዝብ 65 በመቶዉ ከብት በማርባት እንደሚተዳደር ያመለክታል። የዘርፉ እንቅስቃሴም በተለይም የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት ከሶማሊያ ከብቶችን ላለማስገባት ለዘጠኝ ዓመታት የጣሉትን ማዕቀብ ካነሱ ወዲህ ጥሩ እድገት እያሳየ እንደነበር ተገልጿል። ወደእነዚህ ሃገራት ከሚላከዉ ግማሽ ያህሉም በቦሳሶና ፑንትላንድ ወደብ የሚሻገር ነዉ። ድርቅና ርሃብ ላለፉት ሶስት ዓመታት አካባቢዉን ክፉኛ ጎድተዉ ቆይተዋል። የሰሞኑ ማዕበልና ከባድ ዝናብም ተጨማሪ ጫና ይዞባቸዉ እንደመጣ ነዉ FAO ያመለከተዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic