ፐሬዚደንታዊ ምርጫ በአልጀርያ | ኢትዮጵያ | DW | 09.04.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ፐሬዚደንታዊ ምርጫ በአልጀርያ

አልጀርያ ውጥ በዛሬው ዕለት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በመካሄድ ላይ ነው። በህገ መንግስቱ ላይ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ርዕሰ ብሄሩ አብደልአዚዝ ቡቴፍሊካ አሁን ለሶስተኛ ጊዜ በዕጩነት ይወዳደራሉ።

default

ጠንካራ ተፎካካሪ ያልቀረበባቸው ፕሬዚደንት ቡቴፍሊካ በምርጫው ማሸነፋቸው እንደማይቀር ተገምቶዋል፤ ምክንያቱም ጸረ አክራሪ ሙስሊሞች ፖሊሲ የሚከተሉት ፕሬዚደንት ቡቴፍሊካ የሀገሪቱን መረጋጋት ጠብቀው ማቆየት የሚችሉ መሪ ሆነው ነው የሚታዩት። ይሁን እንጂ፡ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ አሌግዛንደር ገብል እንደዘገበው፡ የፖለቲካ ግድየለሽነት እና ቅር የመሰኘቱ ሁኔታ በሚታይባት አልጀሪያ ውስጥ መረጋጋቱን የማረጋገጡ ሂደት ቀላል አይደለም። አርያም ተክሌ

አልጀርያ በአንድ ወቅት « በሜድትሬንያን ባህር የምትገኝ ነጭዋ ሉል » ትባል ነበር። በሀገሪቱ በቅኝ አገዛዝ ዘመን የተገነቡት መልክ የነበራቸው ህንጻዎች ዛሬ አርጅተው በመፈረካከስ ላይ ይገኛሉ። በዋና ከተማይቱ አልዥየ ያሉት ቡና ቤቶች፡ የምግብ ቤቶች፡ ሲኔማ ቤቶች እና የትያትር ቤቶች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። በዚህ ፈንታ ብዙ ፖሊሶች ተሰማርተውባታል። በዚህም የተነሳ የከተማይቱ ጸጥታ ከሞላ ጎደል የተረጋገጠ ነው። በመዲናይቱ የቦምብ ጥቃት የሚጣልበት ሁኔታ በጣም ቀንሶዋል።

« ታያለህ፡ መረጋጋቱ፡ ሰላሙ፡ በአሁኑ ኒዜ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝና አስር ሰዓት ድረስ በከተማይቱ መዘዋወር እንችላለን። ምንም ችግር የለብንም። ከቡቴፍሊካ የስልጣን ዘመን በፊት ግን ቢዘገይ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ በመንገድ የሚታይ ሰው አልነበረም። ዛሬ ግን ሰው ከፈለገ ውጭም ሊያድር ይችላል። »

የአልጀርያ ፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ቡቴፍሊካ ከአስር ዓመት በፊት በሀገሪቱ በግምት እስከ ሁለት መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብን ህይወት ያጠፋው የርስእበርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ነበር የሀገር መሪነቱን ስልጣን የተረከቡት። በዚያን ጊዜ በአልጀርያ እርቀ ሰላም የማውረድ ዓላማ ይዘው የተነሱት ፕሬዚደንት ቡቴፍሊካ በርስበርሱ ጦርነት ጊዜ የግድያ፡ የቁም ስቅል ማሳያና የዕገታ ተግባር ላካሄዱ ሁሉ፡ ለመንግስት ወታደሮችና ለሙስሊሞቹ በጠቅላላ ይቅርታ በማድረግ ምህረት አደረጉ። በሀገራቸው መረጋጋትን ለማረጋገጥና በአክራሪ ሙስሊሞጭ አንጻር ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ ቆርጠው የተነሱት ፕሬዚደንቱ አልጀሪያዊው ፕሬዚደንት ለዚሁ ርምጃቸው ብዙ ወቀሳ ቢፈራረቅባቸውም ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ነበር ግልጽ ያደረጉት። የሰባ ሁለት ዓመቱ አልጀሪያዊ መሪ ዛሬም በድጋሚ የሚሉት ይህንን ነው።

« ሀገሪቱ እንደምትፈልገኝ ከያቅጣጫው ሰምቼአለሁ። በዚሁ ጥሪ ክብር ይሰማኛል። የህዝቡን ፍላጎት በቸልታ ላልፍ አልችልም። እና ለፕሬዚደንትነቱ ስልጣን እንደገና እወዳደራለሁ። »

እንደገናም ፕሬዚደንት ሆነው የሚመረጡበት ዕድል ከፍ ያለ ያለ ነው። አልጀርያ በወቅቱ ከጦር ኃይሉ፡ ከፖለቲከኞችና ከምጣኔ ሀብት ዘርፍ መሪዎች በተውጣጣ በግልጽ በማይታወቅ ቡድን ትመራለች። የተቃውሞው ወገን በህዝብ ዘንድ ያን ያህል ተሰሚነት የሌለው አንዳችም ተጽዕኖ የማያሳርፍ ቡድን ሆኖ ነው የሚታየው። የምርጫው ዘመቻም ቢሆን ትርጉም አልባ ነው። የምርጫውን ዘመቻ በተመለከተ የሀገሪቱ ዜጎች ለራድዮ ፍራንስ ኧንተርናስዮናል ከሰጡት አስተያየት አንዳንዱ፡

« ለምርጫው ዘመቻ ደንታ የለኝም። በዚያ የሚደረጉ ዲስኩሮችን አላዳምጥም፤ ድምጼን ለመስጠትም ወደ ምርጫ ጣቢያ አልሄድም። »

« እኔን በሚመለከት፡ ሁሉም ነገር ድግግሞሽ ነው። ዲስኩሮቹ፡ ፕሮግራሞቹ ሁሉ የተደጋገሙ ናቸው። »

እንደ ብዙኃኑ የአልጀርያ ምክር ቤት እንደራሴዎች ቡቴፍሊካ በስልጣን መቆየት አለባቸው ባዮች ናቸው። በዚህም የተነሳ ነበር ከጥቂት ወራት በፊት ፕሬዚደንቱ ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ እንዲወዳደር አርፎ የነበረውን ዕገዳ ለማንሳት ይቻል ዘንድ በህገ መንግስቱ ላይ ማሻሻያ ያደረጉት። በፓሪስ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ስልት ተቋም የሚሰሩት አልጀሪያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ካደር አብደራሂም ይህንኑ የምክር ቤቱን ውሳኔ ከባድ መዘዘ የሚያስከትል አድርገው ተመልክተውታል።

« ይህ በስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች የፈለጉትን ነው የሚያደርጉት የሚል አስተሳሰብ ባለው ህብረተሰቡ ላይ መጥፎ መዘዝ ይኖረዋል። ምክር ቤቱ የእሺ ባዮች ስብስብ ነው። የፍትሁ አውታር ነጻ አይደለም። ፕሬሱ ክትትል በዝቶበታል። የሚያሳዝነው ገንዘብ ነው ሀገሪቱን የሚገዛው። »

በርግጥ አልጀርያ በቂ ገንዘብ አላት። የሀገሪቱ መንግስት ከነዳጅ ዘይቱና ከጋዝ የተፈጥሮ ሀብት ግዙፍ ገቢ ያገኛል። በዚሁ ገንዘብ ያረጁት የሀሪቱ መንገዶችና የሀዲዶች ዕእደሳ ሊደረግና ለህዝቡ አስፈላጊ የሆኑት መኖሪያ ቤቶች መሰራት ይኖርበታል። ይሁን እንጂ፡ ህዝቡ እስካሁን የዚሁ ገቢ ተጠቃሚ አልሆነም። በተለይ በወጣቱ ትውልድ ዘንድ የስራ አጡ ቁጥር ከፍ ያለ ነው። የስራ ቦታም ሆነ ብሩህ የወደፊት ዕድል የላቸውም። በዚህም የተነሳ ወጣቶቹ ደህና ኑሮ ፍለጋ በጀልባዎች ወደ አውሮጳ መሰደዱን ተያይዘውታል። በሀገራቸው የቀሩት አልጀርያውያን ደግሞ ደህና ቀን መጥቶ በአንድ ወቅት « በሜድትሬንያን ባህር የምትገኝ ነጭዋ ሉል » ትባል የነበረችው ሀገራቸው እንደገና የምታንጸባርቅበትን ዕለት በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

አሌግዛንደር ገብል/አርያም ተክሌ/ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic