“ፎጋሪው” ማነው? | ባህል | DW | 08.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

“ፎጋሪው” ማነው?

“ፎጋሪው”ን ማስተዋወቅ ያስቸግራል፡፡ “ፉገራ ዜና” በተሰኘው ዝግጅቱ ለተመልካች በአካል ቀርቦ ዜና እያነበበ እንኳ መልኩ አይታይም፡፡ ፊቱ ተከልሏል፡፡ ሊያውም እንደ ቤተሰባችን አባል በምናውቀው ምስል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:37

ስላቅ፣ ሽሙጥ፣ ተረብ እና ቀልድ

ፎጋሪው በአንድ ብር ላይ የፊት ምስሉ የታተመውን ሰው ግልባጭ አሰርቶ፣ ለዓይኑ ብቻ ቀዳዳ ቢጤ አበጅቶ፣ እንደ ጭምብል በማጥለቅ ከካሜራ ፊት ይቆማል፡፡ ጣቶቹ እንኳ እንዳይታዩ ጓንት ያጠልቃል፡፡ ራሱን መደበቅ የፈለገበትን ምክንያት ጠየቅሁት፡፡ ዓይናፋርነት፣ ፍርሃት ፣ ወይስ …?፡፡ በዝግጅቶቹ ላይ እንዳስለመደው ቀልድ እና ቁም ነገር እያደባለቀ፣ ከባልደረባው አለማየሁ ገመዳ ቃል እየተበደረ መለሰልኝ፡፡

“ፎገራ ኒውስ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለ ሰው አይደለም፡፡ የኖርንበት ያደግንበት ጨዋታ ነው፤ የጨዋታ ዘዬ ነው፡፡ እዚያ ላይ የሚወጣው ሰው እንደ አንድ ብሩ ሰው ተራ፣ መደበኛ ሰው መሆኑ ደስ ይለናል፡፡ እኛም ስለራሳችን እንዲያ ነን ብለን እናምናለን፡፡ ጨዋታችን በዚያ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የግድ አቅራቢ መሆን የለብህም፡፡ ዋናው ሱፍ የለበሰ ሰው ቲቪ ፊት ቀርቦ መናገር ነው አይደለ? እኛ ደግሞ [እየቀለድንበት] ያለው መድረክ ያ ነው፡፡ ሱፍ የለበሰ ሰው ማይክራፎን አንጋግቶ ዝም ብሎ [ውሸት] ነው የሚነዛው፡፡ በእኛ በኩል ፉገራችንን ሱፍ ለብሰን እንነዛዋለን” ይላል፡፡

እንዲህ እንደ ፎጋሪው ፊትን ሸፍኖ ለህዝብ የሚደርስ ነገር ማቅረብ በሌሎች ሀገራት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ ጥበባዊ ስራዎች በሚያቀርቡት ዘንድ ይበረታታል፡፡ ሲያ የተሰኘችው አውስትራሊያዊት የሙዚቃ ዘፋኝ ለዚህ ተጠቃሽ ነች፡፡ በሙዚቃ ቪዲዩዎቿ ላይ አትታይም፡፡ ወደ 1.5 ቢሊዮን ተመልካች በዩ-ቲዩብ ያየው “ሻንድሊየር” የተሰኘው ዘፈኗ ለምሳሌ አንዲት ታዳጊ ዳንሰኛ ብቻዋን ስትወዛወዝ የሚያሳይ ነው፡፡ ሲያ በመድረክ ዝግጅቶቿ ሳይቀር ወይ በረጅም የዊግ ጸጉር ፊቷን ተሸፍናለች፣ አሊያም ጀርባውን ለተመልካች ሰጥታ ተዘፍናለች፡፡

ፎጋሪውን  ልዩ የሚያደርገው ራሱን በጭምብል መደበቁ ብቻ አይደለም፡፡ የዝግጅት አቀራረቡም ያልተለመደ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ የኢትዮ-ቲዩብ ድረ-ገጽ አንድ አካል ሆኖ መቅረብ ከጀመረ አራት አመትን ያሳለፈው “ፉገራ ዜና” በቴሌቭዥን ዜና አቀራረብ ለተመልካች የሚደርስ ነው፡፡ ዜናዎቹ እውነተኛ ክስተቶችን እንደመንደርደሪያ ቢጠቀሙም በቀልድ የተዋዙ ናቸው፡፡ ““ፉገራ ዜና” ራሱን የሚያስተዋውቅበት አጭር መግለጫ ስለምንነቱ ይበልጥ ጠቋሚ ነው፡፡ “ፉገራ ዜና” የሚተማመኑበት ያልታመነ የዜና አገልግሎት ነው” ይላል በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈው ማስተዋወቂያ፡፡

የ“ፉገራ ዜና” አቀራረብ በበርካታ ሀገራት ከተለመዱት የ“ስላቅ ዜናዎች ” ፕሮግራም ጋር ይመሳሰላል፡፡ ዝግጅቱ ኮሜዲ ሴንትራል በተሰኘው የአሜሪካ የቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ የሚቀርበውን “ዴይሊ ሾው” ፕሮግራም አካሄድ የሚከተል ይመስላል፡፡ እንዲህ አይነት መሰናዶዎች እውነተኛ የዜና ዝግጅቶችን በግብዓትነት ይጠቀማሉ፡፡ ፎቶዎች ለእነርሱ በሚስማማቸው መልኩ አስተካክለው እና ታሪካቸውን እንዲናገሩላቸው አድርገው ይጠቀማሉ፡፡ ልክ እንደ “ዴይሊ ሾዎቹ” ጆን ስትዋርት እና ትሬቨር ኖሃ ሁሉ የዝግጅቱ ቁልፍ ሰው ዜናውን የሚያቀርበው ፎጋሪው ነው፡፡ እነርሱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ተባባሪ ዘጋቢዎችን በፕሮግራሙ ጣልቃ ያሳትፍ ነበር፡፡ እንደ እነርሱ በመደበኛነትም ባይሆን አልፎ አልፎም እንግዳዎችን በአካልም በስልክም እየጋበዘ ያነጋግራል፡፡  

ጥያቄ ለፎጋሪው፡፡ ዝግጅቱ በየትኛው ምድብ ውስጥ ይፈረጃል? ስላቅ፣ ሽሙጥ፣ ነቆራ ወይስ ቀልድ?

“ሁሉም መልስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የጠቀስካቸው ሁሉም አሉበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ዋናው ኢትዮጵያ የምንከታተለው ነገር ይሄ ነው፤ እኛም እየተከታተልነው ነው [ለማለት ነው]፡፡ ቀልዱም እንዳለ ነው፡፡ የእኛ አመለካከት ‘ነገሮችን ማካበድ ይደብራል’ የሚል ነው፡፡ ረጋ ባለ ሁኔታ እንድንነጋገርበት የተደረገ ሴራ ነው” ሲል ቀልድ አዘል ምላሹን ይሰጣል፡፡ 

በእርግጥም የፎጋሪውን ዝግጅቶች ለጥቂት ደቂቃ የተመለከተ ነገሮችን ቀለል አድርጎ የመመልከት አካሄዱን ወዲያውኑ ይረዳል፡፡ ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችን፣ በሀገሪቱ ፖለቲካም ሆነ ሌላው ዘርፍ አንቱ የተባሉ ግለሰቦችን እና ክስተቶችን የከተማ ወጣቶች ሰፈራቸው ውስጥ በሚያወሩበት ቋንቋ አቅርቦ ያብጠለጥላቸዋል፡፡ የትችት ዶፍ ያወርድባቸዋል፡፡ አሳማኝ እና ምክንያታዊ ያልሆኑትን በፈርጅ በፍርጃቸው እየተነተነ ይሳለቅባቸዋል፡፡ የመንግስት ባለስልጣን ይሁን ተቃዋሚ፣ ዝነኛ ይሁን ባለሀብት፣ የመብት ተሟጋች ይሁን የአገዛዙ ደጋፊ ሁሉንም አይምርም፡፡ 

ፎጋሪው ፖለቲካ ጉዳዮች ይመስጡታል፡፡ እስካሁን ለተመልካች በቀረቡ 20 ክፍሎች ሰፊውን ሽፋን ያገኙትም ፖለቲካ ቀመስ ጉዳዩች ናቸው፡፡ በአማካይ የግማሽ ሰዓት ርዝመት ለሚኖረው ዝግጅቱ የሚሆኑ ጉዳዩችን የሚመርጠው ከኢትዮ-ቲዩብ ባልደረቦቹ ጋር በመነጋገር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የወቅቱን ዜናዎች እና በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ አነጋጋሪ የነበሩ ጉዳዮችን በትኩረት እንደሚከታታሉና ለዝግጅታቸው ይሆናል የሚሉትን ከዚያ ተነስተው እንደሚመርጡ ያስረዳል፡፡

USA -Fugera News Satireprogramm von EthioTube: Alemayehu Gemeda, co-founder von EthioTube

አለማየሁ ገመዳ ከኢትዮ-ቲዩብ መስራቾች አንዱ

በተመረጡት ጉዳዩች ላይ ያለውን ዕውነታ ለማረጋገጥ እና ለማጣራት ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስዱ ይናገራል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አባባሎችን ለማረጋገጥ እንደሄዱበት ርቀት ሁሉ ብዙዎቹ ዜናዎቻቸው ወደ ሀቅ ማጣራት (fact-checking) እያዘነበሉ የመምጣት አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ ፎጋሪውም ይህን ይቀበላል፡፡ ሀሳቡ የኢትዮ-ቲዩብ መስራቾች የሆኑት አለማየሁ ገመዳ እና ሙክታር መሐመድን ከተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ እንደሆነ ይናገራል፡  

“እንደተዋወቅኳቸው ስንነጋገር አንዱ አላማቸው [ሀቅ ማጣራት] መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ‘ምን ማድረግ እንችላለን፣ ምን ሊደረግ ይችላል?’ እያልን ስንወያየ የምንኖርበት ስምንተኛው ሺህ የተለያየ የመረጃ መንገድ አለ፡፡ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ባትሄድም የጋዜጠኝነትን መርህ ከተከተልክ አንዳንድ ነገሮቹ ሊጣሩ የሚችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነርሱ የተለያዩ ክሊፖችን እየሰበሰሰቡ ያመጡ ነበር፡፡ ከተሰበሰቡ መረጃዎች ውስጥ ደግሞ ጊዜ ወስደህ ካየህና [መርሆዎችን] ከተከልክ ምንጠራ ወይም ጉርጎራ ይከሰታሉ ማለቴ ነው፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ከኢትየ-ቲዩብ ጋር ስለምሰራና የተለያዩ መረጃዎች ስለምናገኝ ያንን በመግፋት ነው ” ይላል እውነታዎችን የሚያጣሩበትን አካሄድ ሲያብራራ፡፡

“ፉገራ ዜና” ሀቅ የማጣራቱን ጉዳይ በዛ እንዳደረገው ሁሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቀልድ ከተዋዛ አቀራረቡ መረር፤ ኮስተር ወደ ማለት የተሻገረ ይመስላል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ክፍሎች በየዜናዎቹ መካከል ይቀርቡ የነበሩት የፈጠራ ማስታወቂያዎች ቀርተዋል፡፡ ያለፉትን ሁለት ክፍሎች የተመለከተ ፉገራ ሙሉ ለሙሉ በቁም ነገር መሞላቱን ይታዘባል፡፡ የኢትዮ-ቲዩቡ አለማየሁ ለዚህ ምላሽ አለው፡፡

“ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ነገር ብዙ ነገሩን [ይወስነዋል፡፡] ፉገራ የሚወጣበትን የጊዜ ርቀቱን፣ ይዘቱን፣ አቅጣጫውን እንደገና ደግሞ የአንዱ ክፍል ርዝመት ይሄ ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄደውም ነገር ላይ ይወሰናል፡፡ ምናልባት ጠጠር ያሉ፣ ቀልዶቹ አነስ እያሉ ቁም ነገሮቹ እየሰፉ ከመጡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነገሮች ቆምጨጭ እያሉ መምጣታቸውን የሚያሳይ ነገር ነው” ይላል አለማየሁ፡፡   

ፎጋሪውም ተመሳሳይ አስተያየት ይሰጣል፡፡

“እንዴት መሰለህ ነገሮች መረሩ፡፡ ሰው እየተደበደበ፣ እየተገደለ በኢንተርኔት እያየህ ትንሽ መቀለድ ይከብዳል ግን እንደዛም ሆኖ ግን መቀለድ ማቆም የለብንም ብዬ አምናለሁ፡፡ እስር ቤትም ሆነህ መቀለድ አለ፡፡ እና ያው መቀለዳችንን አናቆምም፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው፡፡ ሁሌም ደግሞ በነገሮች አማርሮ መኖር ይደብራል ስለዚህ አንዳንዴ ቀልድ ፈታ ፈታ ያለ ነገር ደስ ይላል፡፡ ግን ድግሞ እንደዚያ ዓይነት ነገር እየተካሄደ በጣም ልቅ የሆነ ወይም ከዚህ ጋር የማይጣጣም የፈጠራ ማስታወቂያ መስራት ትንሽ ከነገሮች ጋር [አይሄድም]” ሲል ያክላል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መምረር ከመጀመራቸውም በፊት ግን ፎጋሪው ሀገሪቱን የሚመለከቱ አሳዛኝም አስደንጋጭም ሁነቶች ሲከሰቱ ሽፋን ከመስጠት አልቦዘነም፡፡ አቋሙንም በግልጽ ከማቅረብ አላመነታም፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ሲባረሩ እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ድርጊቱን ተቃውሟል፡፡ በሊቢያ በረሃ እና በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን በግፍ ሲገደሉ እና ጥቃት ሲፈጸምባቸው ሀዘኑን ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ተጋርቷል፡፡ 

ፎጋሪው ዝግጅቶቹን የሚያቀርበው ጉራማይሌ ቋንቋ ተጠቅሞ ቢሆንም፣ የአራዳ የሚባለውን ዘዬ ቢከተልም በየቤቱ፣ ከጓደኞች ጋር አሊያም በየቡና ቤቱ የሚቀለዱ ቀልዶች ይመስጡታል፡፡ ራሱን እንደ ተራ የአዲስ አበባ ልጅ የሚቆጥረው ፎጋሪው እየሰማቸው ላደጋቸው ቀልዶች ልዩ ቦታ ይሰጣል፡፡ “የእንግሊዘኛ ቀልድ እንደ አማርኛ ቀልድ አያስቀኝም” የሚለው ፎጋሪው “ኢትዮጵያውያን ቀልድ ያውቃሉ” የሚል እምነት አለው፡፡

የእርሱ ዝግጅቶች ለዕይታ ከበቁ በኋላ ከቪዲዮዎቹ በታች የሚሰጡ አብዛኞቹ አስተያየቶች ግን እንዲህ ዓይነት በስላቅ የታጀበ አቀራረብን የመረዳት ችግር የሚንጸባረቅባቸው ናቸው፡፡ ፎጋሪው ግን እርሱ እንደሚያዘጋጃቸው ዓይነት ዝግጅቶች ባህል የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል ባይ ነው፡፡ 

“የገባው ይገባዋል፡፡ ደስ የሚልህ እሱ ነው፡፡ የገባው የምትናገረውን ያውቀዋል፡፡ ከአንተ ጋር በአንድ ምት ላይ ናችሁ ያላችሁት፡፡ ለሌላው ግን ምጸቱ ይሁን አነጋገሩ ትንሽ ሊምታቱ ይችላሉ፡፡ ግን ያን አይነት ነገር ከተለመደ፤ አንዱን አይቶ ካልገባው ምናልባት በሁለተኛው ወይም ሶስተኛው ሊገባው ይችላል፡፡ በሆነ ትውልድ የተወሰኑ ነገሮች ባህል ይሆናሉ፡፡ በደርግ ጊዜ ወይም በ70ዎቹ ወይ በ80ዎቹ የሆኑ ነገሮች በዚያ ወቅት፣ በዚያ ትውልድ ባህል የሆኑበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ በእኔ አስተያየት እነዚህ ነገሮች ዛሬ ባይሆንም የዛሬ 10 ዓመት አንዱ የባህላችን ገጽታ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ” ሲል ያጠቃልላል፡፡ 

  

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic