«ፍትሕ ለኅሊና እስረኞች» በይነ-መረብ ዘመቻ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 29.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

«ፍትሕ ለኅሊና እስረኞች» በይነ-መረብ ዘመቻ

«ፍትሕ ለኅሊና እስረኞች» በሚል ርእስ የተኪያሄደው በይነ-መረብ ዘመቻ የቆየው ለአንድ ቀን ነው። በዘመቻው ወቅት የተገለጡት ቊጥር ሥፍር የሌላቸው የእስር ቤት ሰቆቃዎች ታሪክ ግን እስከ መቼም ከአዕምሮ የሚጠፉ አይደሉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:45

የእስር ቤት ሰቆቃዎች ታሪክ ግን እስከ መቼም ከአዕምሮ የሚጠፉ አይደሉም

«ፍትሕ ለኅሊና እስረኞች» በሚል ርእስ የተኪያሄደው በይነ-መረብ ዘመቻ የቆየው ለአንድ ቀን ነው። በዘመቻው ወቅት የተገለጡት ቊጥር ሥፍር የሌላቸው የእስር ቤት ሰቆቃዎች ታሪክ ግን እስከ መቼም ከአዕምሮ የሚጠፉ አይደሉም። ብልታቸው ላይ በውኃ የተሞላ ጠርሙስ ተንጠልጥሎባቸው ስለተሰቃዩ ሰዎች መስማት በርካቶችን አሰቅቋል፤ አስቆጥቷል። ጉልበታቸው ሚስማር በተቸነከረበት ዱላ የተደበደቡ፤ ሰብእናቸውም በብርቱ የተብጠለጠለባቸው ሰዎች ጥቂት አለመኾናቸው በዘመቻው ወቅት ተጽፏል። የዘመቻው ተሳታፊዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጻፏቸውን አስተያየቶች አሰባስበናል።  

ረቡዕ ታኅሣሥ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የትዊተር አለያም የፌስቡክ ገጹን የከፈተ ሰው «ኹሉም የኅሊና እስረኞች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ!» የሚለው መፈክርን በተደጋጋሚ ማንበቡ አይቀርም። «በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ለሚገኙ ሁሉም ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች ፍትሕ እንሻለን!» የሚለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው መፈክርም በእለቱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በጉልህ ካስተጋቡ መልእክቶች ዋነኛው ነበር።

በርካቶች የትዊተር እና የፌስቡክ ገጽ ፎቶዋቸውን የወንድ እና የሴት እስረኞችን ለመከወል በካርቱን በተሰናዱ የፊት ገጽ ስዕሎች ተክተው ቆይተዋል።  የጽሑፍ መልእክቶቹም ሆኑ የካርቱን ስዕሎቹ በዕለቱ ጎልተው የመታየታቸው ምክንያት «ፍትሕ ለኅሊና እስረኞች» በሚል ርእስ የተኪያሄደው የበይነ-መረብ ዘመቻ ነው።

ከዚህ በይነ-መረብ ዘመቻ አዘጋጆች መካከል አንዱ የኾነው የዞን ዘጠኝ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፦«የኅሊና እስረኞችን ጉዳይ በአፅንዖት ልንከታተልባቸው የሚያስገድዱን 3 ዐበይት ምክንያቶች» በሚል ርእስ ቀጣዩን መልእክት በፌስቡክ ገፁ አስነብቧል።

«1ኛ የአንድ ስርዓት ፍትሐዊነት የሚፈተሸው የታሰሩ ዜጎችን ሰብኣዊ መብቶች እና ክብሮችን በመጠበቅ እና በማስጠበቅ ዐቅሙ እና ፈቃደኝነቱ ልክ ስለሆነ፣ 2ኛ የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ ለፍትሕ፣ ርትዕና ነጻነት እንዲሁም ለዴሞክራሲ ዕድገት አስፈላጊ በመሆኑ በቸልተኝነት ልናልፈው ስለማይገባ፣ 3ኛ የኅሊና እስረኞች በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ በጋዜጠኝነት ሥራቸው፣ የመንግሥትን እና ባለሥልጣናቱን ስህተት በመንቀፋቸው ወይም በማጋለጣቸው፣ እንዲሁም ለሕዝባቸው የሚበጅ በመሥራታቸው አሊያም ለሕዝብ የማይበጅ አልሠራም በማለታቸው የታሰሩ በመሆናቸው እና ይህ በአገራችንም ሆነ በየትኛውም ዓለም ላይ፣ መቼም መፈፀም ስለሌለበት» የሚል ጽሑፍ አስፍሯል።  ጽሑፉንም «ፍትሕ ለሕሊና እስረኞች» በሚል መፈክር ቋጭቷል።

«በሽብር ክስ እስር ላይ የሚገኙ የግፍ እስረኞች ስም ዝርዝር ሳትሰለቹ አንብቡ!» በሚል ርእስ የጻፈው ደግሞ ሬቮሉሺን ሱን ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ነው። ገጹ በእስር ላይ የሚገኙ ያላቸውን 570 ሰዎች ስም ዝርዝር አስፍሯል። «ከዚህ በላይ የምታዩት በግፍ የታሰሩ የፓርቲ አባላት እና አመራሮች ነፃነት ታጋዮች ጋዜጠኞች ፣ተቋማት የዩንቨርቲ ተማሪዋችና መምህር የመንግስት ሠራተኞች የስም ዝርዝር ነው። ሲታሰሩ እየጨመርኩኝ ሲፈቱ እየቀነስኩኝ ዛሬ ላይ ስብስቡ ይኽን ይመስላል። ይኽ ማለት የታሰሩ ወገኖቻችን 570 ብቻ ናቸው ማለት አይደለም እነዚህ በስም እና በፎቶ የሚታወቁ ብቻ ናቸው በብዙ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በእስር እየተሰቃዩ እንደሆነ ፍጹም አንዘነጋም ።» የሚል መልእክት «የኅሊና እስረኞች ይፈቱ» ከሚል መፈክር እና በይነ-መረቡ የካርቱን ፎቶዎች ጋር አያይዟል። በዚሁ ገጽ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል የሺመቤት አበባው  «እግዚአብሔር ከአረመኔ እጅ ነፃ ያውጣችሁ...» ብላለች።

ትእግስት ኤም በትዊተር ገጿ «የኅሊና እስረኞችን ለማስታወስ» ከሚል የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ጋር ያያያዘችው ቪዲዮ የበርካታ እስረኞች ስም ዝርዝር በተከታታይ ብቅ ሲል ይታይበታል። ትእግስት ከዘረዘረቻቸው እስረኞች መካከል፦ ታዋቂ ጋዜጠኞች ፤ ጸሐፍት፣ ፖለቲከኞች እና ምሁራን ይገኙበታል።

ሊያና ቢ ተፈሪ ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ያቀረበችው ጽሑፍ «መነኮሣት፣ ቀሳውስት፣ አዛውንቶች፣ ወንዶች፣ ሴቶች» ሲል ይንደረደራል። ኹሉም «ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው» ሊያና «አሸባሪ» ያለችው «መንግሥት ሰለቦች ናቸው» ብላለች። «ለመንገላታት እና እስር ቤት ለመወርወር የሕወሓት የጭቆና ስልቶች የኾኑትን በገፍ መጋዝን፣ መገደልን፣ ጎሠኝነትን ብሎም ጭቆናን ብቻ መቃወም ነው የሚያስፈልጋቸው» በማለት ከመልእክቷ ጋር ፎቶግራፍ አያይዛለች። ፎቶግራፉ ላይ አዛውንቶች እና በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ቢጫ የእስር ቤት ልብስ እንደለበሱ ይታያሉ። 

«ማሰር፣ መደብደብ፣ ማሰቃየት፣ ማዋረድ፣ አንገት ማስደፉት፣ ሰው የመሆን ክብርን መግፈፍ… ይህ ሁሉ እየሆነባቸው ያለው በማሰባቸው እና ሀሳባቸውን በመግለፃቸው ነው። ማሰብ ክልክል ነው። መናገር ክልክል ነው።» ያለችው ሲያኔ አንለይ ናት በትዊተር ገጿ።«የኅሊና እስረኞች ይፈቱ» የሚል መልእክትም አያይዛለች።

ሰለሞን መንገሻ፦ «እንደዜጋ ከሚያሸማቅቁኝ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ዓስራ ሦስት ነገሮች ውስጥ ቀዳሚው፤ በዚህች ሀገር እስር ቤቶች ውስጥ ይሄ ሁላ ግፍ እየተፈፀመ ምንም እንዳልተፈጠረ አይነት ኑሮ መኖሬ ነው ።» ሲል በፌስቡክ ጽፏል። «የኅሊናና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ»ም ብሏል።

ሲቲና ኑሪ ትዊተር ላይ ፎቶግራፎችን አያይዛ በእንግሊዝኛ የሚከተለውን ጽፋለች። «የታሰራችሁበት እግረ-ሙቅ ምንጊዜም ታሪካችሁን ይነግረናል። ሰውነታችሁ ላይ ያረፈው የሰቆቃ ምልክት የነጻነት ንቅሳት ነው። ኹላችሁም ከነዚያ የእስር ቤት የጨለማ ቤቶች በክብር የምትወጡበት ጊዜ አለ፤  መቼም አትረሱም።» ይላል የሲቲና ጽሑፍ።

«ፍትሕ ለኅሊና እስረኞች» ከተሰኘው ዘመቻ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው፦ «የኅሊና እስረኞችን ለማስታወስ በተደረገው የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ የተሳተፋችሁትን ሁሉ በእስረኞቹ ሥም እናመሰግናለን።» ሲል ፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል። «እስረኞችን የማስታወስ ግዴታችን ሁልጊዜም የሚቀጥል ቢሆንም በተቀናጀ ሁኔታ ለማስታወስ ግን በሌላ ዘመቻ ሌላ ጊዜ እንገናኛለን።» ብሏል። «ማንም በአመለካከት ልዩነቱ ወይም በማንነቱ ሊታሰር እና ሊንገላታ አይገባም!» የሚል መልእክትም በፌስቡክ ገጹ አስተላልፏል።

ከዚሁ ከእስረኞች ርእሰ ጉዳይ ሳንወጣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ምስክሮችን የተመለከተው ጉዳይም ሌላኛው በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተነሳ ነጥብ ነበር። የገዢው ኢሕአዴግ አባል ድርጅት የኾነው የኦሮሞ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራር ባልተለመደ መልኩ ለአቶ በቀለ ገርባ ለመመስከር ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው የሚለው ዜና የመገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ኾኖ ነበር።

የአቶ በቀለ ገርባ መከላከያ ኾነው ሐሙስ እለት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ የተባሉት የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፦ «በአስቸኳይ ሀገራዊ ስብሰባ ምክንያት መመስከር ስለማይችሉ» ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠየቁ የተባለበት ደብዳቤም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ብዙዎች ተቀባብለውታል። 

በርካቶችን ያስገረመው የመንግሥት ከፍተኛ አመራር እስር ላይ ለሚገኝ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ለመመስከር ይቀርባሉ መባሉ ነበር።  የባለሥልጣናቱን ፎቶግራፍ አያይዞ ስለ አቶ በቀለ ገርባ ምስክሮች የዘገበው የአዲስ ስታንዳርድ ጽሁፍን በመጥቀስ አወል አሎ በትዊተር ገጹ  እንዲህ ብሏል። «ይኽ የአዲስ ስታንዳርድ ዘገባ እውነት ከኾነ በኢትዮጵያ ለፍትሕ በሚደረገው ትግል ታላቅ ርምጃ ነው» ብሏል። «መቼስ ነው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት  የተከሳሽ ምስክር ለመኾን ፍርድ ቤት ለመጨረሻ ጊዜ የቀረቡት?» ሲልም ጠይቋል።

ለነ ጉርሜሳ አያኖ ፍርድ ቤት ቀርበው ይመሰክራሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የኦህዴድ ባለስልጣናትን የጠቀሰው አበበ ቶላ ፈይሳ፦ «አቶ ለማ መገርሳ፣ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ ዶክተር አብይ አህመድ እና አቶ አባዱላ ገመዳ በድርጅታቸው ስም ለፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው መጠየቃችውን አይተናል። ይሄ የሚበረታታ ጅምር ነው» ብሏል። «በተለዋጩ ቀጠሮ ተገኝታችሁ ምስክርነታችሁን እንደምትሰጡ ተስፋ እያደረኩ በበኩሌ ገለቶማ! ብያለሁ!» ብሏል።

ብርካን ፋንታ ትዊተር ላይ «ለማ መገርሳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ምስክርነት ሰጠ አልሰጠ፣ በነገር ሁሉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አለ አላለ በእጁ ያለው ደም በአፉም ሆነ በማንም አጫፋሪነት አይታጠብም ፍትሕ ትርፍና ከሲራ ላይ አይሠራም » የሚል ጽሑፍ አስነብቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች