ፍትሕን በደቦ | አፍሪቃ | DW | 07.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ፍትሕን በደቦ

ሌባ በድንጋይ ይወገራል፤ ቤት ሠርሣሪ እስከሞት ድረስ ይደበደባል፤ በአብዛኛው የአፍሪቃ ሃገራት ነዋሪዎች ፍትሕን በእጃቸው ሲያደርጉ ይታያል። በፖሊስ መተማመኑ ሲጠፋ አመፃው ይስፋፋል። ለመሆኑ በአፍሪቃ በርካታ ሰዎች ጥፋተኛን ሕግ ፊት ከማቅረብ ይልቅ ለምንድን ነው ፍትሕን በእራሳቸው መንገድ ለመፈጸም የሚጥሩት?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:54
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:54 ደቂቃ

ፍትሕን በደቦ

የዶይቸ ቬለ ወኪል ኤሪክ ፖንዳ የሚሞት ነበር የመሰለው። ባለፈው ዓመት ከዘገባ ውሎው ወደ ቤቱ በመመለስ ላይ ነበር። ድንገት የተሽከርካሪው ሞተር ቀጥ ይላል። ኤሪክ የመንገዱ ቅያስ ላይ ሊያዞር ሲል ነበር አንድ መንገደኛ ዘው ያለበት። በእርግጥ ተሽከርካሪው የሰውየውን እግር ጨረፍ ነው ያደረገችው። ኤሪክ መኪናዋን ወዲያው ነው ያስቆማት። ሆኖም በቅጽበት ውስጥ ከዚህም ከዚያም የተጠረቃቀመ ግርታ አካባቢውን ሞላው። ጋዜጠኛው ኤሪክ ለሕይወቱ አስጊ የነበረውን ቀን መቼም አይረሳውም። «በጣም ያስፈራ ነበር። እንደውም የምሞት ነበር የመሰለኝ።» ሲል ፍርኃቱን ያስታውሳል።

ከየቤታቸው ግር ብለው የወጡት ሰዎች ያለምንም ጥያቄ ኤሪክን ማዋከብ እና መደብደብ ነው የጀመሩት። አንዳቸውም ኤሪክ ፖንዳን ፍትሕ ፊት ለማቅረብ አልሞከሩም። «ሰዎቹ እጅግ የተቆጡና የተናደዱ ነበሩ» ይላል ኤሪክ። «መኪናዬን ሊያቃጥሏት ምንም አልቀራቸውም ነበር። ከመኪናዬ ውስጥ እየገፈታተሩ በማስወጣት ይቀጠቅጡኝ ጀመር። ንብረቶቼን በመላም ዘርፈው ወሰዱ፤ ገሚሱ እንደውም የዶይቸቬለ መሣሪያዎች ነበሩ» ሲልም አክሏል።

ኬኒያዊው የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛ ኤሪክ ፖንዳ በሚኖርበት የሞምባሳ አካባቢ በዓመት 500 ገደማ ሰዎች ይገደላሉ። ኤሪክ ድንገት ፖሊስ በአካባቢው ሲያልፍ ባያስጥለው ኖሮ ከአምስት መቶዎቹ አንዱ መሆኑ ባልቀረ ነበር። «በዚያ ቀን መቼም ዕድለኛ በመኾኔ ነው የተረፍኩት።» የሚለው ኤሪክ ፖሊስ በዛ በኩል ባያልፍ ኖሮ መኪናውን በእሳት አያይዘው፤ ምናልባትም እሱን ከማቃጠል ወደኋላ የማይሉ ሰዎች አንደነበሩ ገልጧል።

ከዚያች ቀን አንስቶም ኤሪክ መኪናውን ሲያሽከረክር በግማሽ ፍርኃት ተውጦ ነው። «ምን ሊከሰት እንደሚችል አታውቅም» ይላል በሞምባሳ ጎዳናዎች በእየ እለቱ የሚመላለሰው ጋዜጠኛ ስለፍርኃቱ ምንጭ ሲናገር። የደረሰበትን ጥቃት ፖሊስ ዘንድ ቀርቦ ቢያመለክትም ጥፋት አድራሾቹ ላይ ምንም የተደረገ ነገር የለም። «ፖሊስ ጋር ሄጄ አመልክቼ ነበር። ግን ደግሞ ፖሊስ ጋር ስትሄድ ማስረጃ ያስፈልግሀል። ያው ታመለክታለህ ግን ማስረጃ ስለሌለህ ምንም የሚደረግ ነገር የለም።»

የኬንያ ፖሊስ በየዓመቱ ግር ብለው በሚመጡ ሰዎች ምን ያህል ጥቃት እንደሚፈጸም መረጃ ማሰባሰብ ከጀመረ አምስት ዓመታትም አላለፈው። ፖሊስ በዚህ መልኩ የሚፈጸም ወንጀልን በተመለከተ የመጀመሪያውን መረጃ ያሰባሰበው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 ዓመት ነው። እስካሁን 543 ሰዎች ላይ ተመሳሳይ የግርታ ጥቃት መድረሱን ፖሊስ ይገልጣል። በ2014 ዓመት ኡጋንዳ ውስጥ 582 ሰዎች ፍትሕ ዘንድ ሳይቀርቡ በንዴት በተዋጠ ሰዎች ተገድለዋል። ያ ማለት በዚያ መልኩ በየቀኑ ከአንድ ሰው በላይ ይገደላል ማለት ነው።

በደቡብ አፍሪቃ ደግሞ በቁጣ በተዋጡ ሰዎች ግርግር የሚፈጸመውን ተመሳሳይ የደቦ ግድያ ወንጀል ነዋሪዎች «ጎማ ጥፈራ» የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተቆጡ ነዋሪዎች ሰዎችን በተለይም ስደተኞችን ከነሕይወት የማቃጠል ወንጀል በተደጋጋሚ ሲፈጽሙ ያታያል። ወንጀለኞቹ ጥቃት የሚያደርሱበትን ግለሰብ ለማቃጠል ሲፈልጉ በአንገቱ የተሽከርካሪ ጎማ አስገብተው እጆቹን ወደኋላ ከጎማዎቹ ጋር በመጠፈር ቤንዚን ያርከፈክፋሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ዳግም ተቀስቅሶ በነበረው የአፍሪቃውያን ስደተኞች ጥላቻ ሰበብ በርካቶች በጎማ ጥፈራ እሳት ተለኩሶባቸው ተገድለዋል። የግድያው ምክንያት ደግሞ የደቡብ አፍሪቃ የዙሉ ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ ስደተኞችን በተመለከተ «ደቡብ አፍሪቃ ከተባዮች መጽዳት አለባት» ሲሉ ያሠሙት የጥላቻ ንግግር ነበር።
በደቡብ አፍሪቃ የስደተኞች ጥላቻ የቀሰቀሰው ግርግር እና ሁካታ በደቡብ ደርባን ከተማ፤ ኡልማዚ የተባለው ሥፍራ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወንድማማች ስደተኞች በእሳት እንዲቃጠሉ ሰበብ ሆኗል። በወቅቱ ከወንድማማቾቹ አንዱ በቃጠሎው ሕይወቱ ስታልፍ ከፍተኛ ቃጠሎ የደረሰበት ወንድምዬው ሐኪም ቤት እንደገባ ተዘግቦ ነበር።

ቁጣ የቀሰቀሰው የሰዎች ግርታ የጥቃት አድማስ አንዳንድ ጊዜ ዳፋው በፖለቲከኞች ላይም ሲደርስ ይታያል። በቅርቡ እንኳን በሚያዝያ ወር መግቢያ የናይጄሪያ የምክር ቤት አባል የሆኑት ቡኮላ ሳራኪ ላይ የደረሰው የሚታወስ ነው። የተቆጡ ሰዎች የምክር ቤት አባሉን በናይጀሪያ መዲና አቡጃ የገበያ ሥፍራ ውስጥ ልብሳቸውን በመግፈፍ ጸያፍ ጽሑፎችን ገላቸው ላይ ጽፈው ተሳልቀዋል።

ጥቃት አድራሾቹ የምክር ቤት አባሉ ገላ ላይ የጻፉት መቼም ታጥቦ እንዳይለቅ በማሰብ ነው። የሰዎቹ የጥቃት ሰበብም ፖለቲከኛው ያለአግባብ በልጽገዋል፣ በሙስናም ተጨማልቀዋል የሚል ነው። ፖለቲኛውን የሚወነጅሉ ጽሑፎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በተሰራጩበት ቅጽበት ቁጣው ገንፍሎ ወደ ጥቃት ተቀይሯል። መደበኛ የእለት ተእለት ኑሮ የሚገፋ ነዋሪ ድንገት የግድያ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፈው ለምንድን ነው? የብዙዎች ጥያቄ ነው። ጌይል ሱፐር ካፕሽታድት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የወንጀል ድርጊት ተመራማሪ ናቸው። በግርታ የሚፈጸም የደቦ ፍትሕ ሰበብን ሲያብራሩ «ሰዎች በጋራ ጥቃት ሲፈጽሙ የሚሰማቸው የጋራ ጉድኝት ላይ ማተኮሩ ወሳኝ ነው።» ይላሉ። «እንዲህ አይነቱ በግርግር የሚፈጸም የደቦ ፍትሕ ማኅበረሰቡ ለአንዳች ጉዳይ ትእግስት እንደሌለው ማሳያ ነው። በጉስቁልና በተዋጡ ማኅበረሰቦች ዘንድ ስርቆት መዘዙ እጅግ የከፋ ነው። እናም ማኅበረሰቡ ሰራቂውን መቀጣጫ ማድረግ ነው የሚሻው።»ሲሉም ድርጊቱ የቆየ መሆኑን አብራርተዋል።

በአፍሪቃ በርካታ ነዋሪዎች ራሳቸውን በፖሊስ ቦታ በመመደብ ወንጀልን ለመከላከል በሚል የደቦ ፍትሕን ሲፈጽሙ ይታያል። በእርግጥ በብዙዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት የሕግ አስከባሪ አካላት እጥረት ይስተዋላል። ለአብነት ያህል በናይጀሪያ የኒጀር ግዛት ውስጥ ያሉት ፖሊሶች ከ8000 እንደሚያንሱ የናይጀሪያ ፖሊስ አዛዥ ሶሎሞን አራሴ በቅርቡ ለመገናኛ አውታሮች ገልጠዋል። ያ ማለት በግዛቲቱ የሚገኝ አንድ ፖሊስ የሚመደበው ለ494 ሰዎች ነው።

ከዚያ በተጨማሪ በአፍሪቃ በርካታ ሃገራት ፖሊሶች ራሳቸው በሙስና የተዘፈቁ ከመሆናቸው ባሻገር ወንጀልን የመታገል ጥልቅ ፍላጎት አይታይባቸውም። በደቡብ አፍሪቃ የደኅንነት ጥናት ተቋም ውስጥ «ወንጀል እና ፍትሕ» የተሰኘው የጥናት ቡድንን የሚመሩት ሊዜቴ ሌንካስተር «የደቦ አለያም በግርግር ውስጥ ሰዎች ፍትሕን በእጃቸው በማስገባት የሚፈጽሙት ሕገ-ወጥ አሠራር ወንጀለኞችን ወይንም ደግሞ በሀገር ውስጥ የሚከሰት ከፍተኛ የወንጀል ድርጊትን በመቃወም በማኅበረሰቦች ዘንድ የሚፈጸም» የቆየ ባሕላዊ ድርጊት መሆኑን አብራርተዋል። «የወንጀል ችግሮቹን ፖሊስ መፍታት ይችላል የሚለው እምነት ከማኅበረሰቡ ውስጥ ሲጠፋ ያ ይከሰታል» ሲሉም አክለዋል።

ከመደበኛው የፍትሕ ስርዐት ውጪ በተቆጡ ሰዎች በጋራ የሚፈጸም የደቦ ፍትሕን በተለይ በከተሞች ውስጥ መቆጣጠሩ ከበድ ብሎ ያታያል። ከፈጣን የከተሞች መስፋፋት ጋር የሰዎች ፍልሰት መጨመር እና የወጣቶች ሥራ አጥነት የችግሩ ተጨማሪ ሰበብ ተደርጎ ይወሰዳል። በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሕግ አስፈፃሚው አቅም እና ተግባር ሲያንስ ራሳቸውን የፍትሕ አስፈጻሚ እና ስርአት አስከባሪ አድርገው ይሾማሉ።

«ብዙውን ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ፖሊስ በፍጥነት አይደርስም። ፖሊስ የሚደርሰው አስክሬኑ በግለሰቦች አለያም በበርካታ ሰዎች ከተገኘ እና ፖሊስ ከተጠራ በኋላ ነው። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ድርጊቱ ሲከሰት አያዩም»
የዶይቸ ቬለ ወኪል ኤሪክ ፖንዳ ከደረሰበት የደቦ ድብደባ ፖሊስ ድንግት ደርሶ ቢያስጥለውም እምነቱ ግን ተሸርሽሯል። ፖሊስ በወቅቱ በቦታው ደርሶ የሰውን ግርግር ቢበትንም ከዚያ ባሻገር ያደረገለት አንዳችም ነገር አልነበረም። ክስ ቢመሠርትም ክሱ ዋጋ እንዳጣ ነው የሚናገረው።

«ሁሉንም ነገር ታጣና ያከትምልህ ይሆናል። በስተመጨረሻ በክስ ሒደቱ ሳይቀናህ፤ ሐብት ንብረትህ ወድሞ ሕይወትህንም ታጣ ይሆናል። ማሸነፍ ባለመቻልህም ምንም የሚፈጠር ነገር አይኖርም።»

መኪናው ሰው በመጭረፉ በተቆጡ ሰዎች ከተደበደበበት ከዚያች አስደንጋጭ እና አደገኛ ክስተት በኋላ ኤሪክ ፖንዳ በሞምባሳ ጎዳናዎች መኪናውን ሲያሽከረክር ፍርኃት ውስጡን እያናወጠው ነው። ግር ብለው የሚመጡ የተቆጡ ሰዎች የሚፈጥሩት አይታወቅምና።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic