ፍርድ ቤት እና የአቶ ሃብታሙ የጤና ሁኔታ | ኢትዮጵያ | DW | 01.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ፍርድ ቤት እና የአቶ ሃብታሙ የጤና ሁኔታ

በቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው በመታመማቸው ከአገር እንዳይወጡ የተጣለባቸው እገዳ ተነስቶ በውጭ መታከም እንዲችሉ የቀረበለትን አቤቱታ ዛሬ የተመለከተው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ተጨማሪ ማስረጃዎች እንዲቀርቡለት በመጠየቅ ውሳኔውን ወደ ሚቀጥለው ሳምንት አስተላልፎታል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:09

የአቶ ሃብታሙ የጤና ሁኔታ

የአቶ ሃብታሙ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት እገዳውን ለማንሳት በቂ ማስረጃ አልቀረበም ያለው ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም በእነ አቶ ሀብታሙ ጉዳይ ላይ አቃቤ ህግ ላቀረበው ይግባኝ በመጪው ማክሰኞ ይሰጣል ተብሎ ከሚጠበቀው ውሳኔ በኋላ ሌሎች አማራጭ መፍትሄዎች ሊታዩ እንደሚችሉ አስታውቋል ።
አቶ ሃብታሙ አያሌው በ2006 ዓም በሽብር ወንጀል ተከሰው አንድ ዓመት ተኩል ከታሰሩ በኋላ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ነበር ከእሥር የተፈቱት ።አቶ ሃብታሙ ያኔ በነፃ ቢለቀቁም አቃቤ ህግ ባቀረበው ይግባኝ ምክንያት ከሃገር እንዳይወጡ ታግደዋል ። አቶ ሃብታሙን በቅርብ የሚያውቋቸው እንደተናገሩት በእሥር እያሉ እና ከእሥር ከተፈቱም በኋላ በተለያዩ የጤና ችግሮች ይሰቃዩ ነበር ። አቶ ሃብታሙ ከተኙበት ሆስፒታል በስልክ ያነጋገርኩት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እንዳለው በአሁኑ ጊዜ በግል ሆሲፒታል ተኝተው በመታከም ላያ ያሉት የአቶ ሃብታሙ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ።
አቶ ሃብታሙን በቅርብ የሚያውቋቸው እንደሚሉት አሁን የጠናባቸው የጤና ችግር የጀመራቸው በእሥር ላይ እያሉ ነበር ። ይህን ከሚሉት አንዱ ከአቶ ሃብታሙ ጋር ታስረው የነበሩት አቶ ዳንኤል ሽበሺ የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የድርጅት ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ ናቸው ።


አቶ ሃብታሙ ቀደም ሲል ለህክምና በሄዱባቸው ሁለት ሆስፒታሎች ሊረዱ አለመቻላቸውን የገለፁት ጠበቃቸው አቶ አም ሃ መኮንን እንደሚሉት አሁን በተኙበት ሦስተኛ ሆስፒታልም የስቃይ ማስታገሻ ብቻ እየተሰጣቸው ነው ። ህክምናው ውስብስብ እና ከፍተኛ ስቃይ የሚያስከትል መሆኑ ከሐኪሞች የተነገራቸው አቶ ሐብታሙ ወደ ውጭ ሃገር ሄደው የመታከም ፍላጎት ቢኖራቸውም ፍርድ ቤት በጣለባቸው እገዳ ምክንያት አልቻሉም። ይኽው እገዳ እንዲነሳ አቤቱታ የቀረበለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ተጨማሪ ማስረጃ እንዲቀርብለት ዛሬ መጠየቁን አቶ አምሃ ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።
አቶ አምሃ እንደተናገሩት የተጠየቀውን ማስረጃ ማቅረብ ካልተቻለም ፍርድ ቤቱ ሌሎች አማራጭ መፍትሄዎችን ሰጥቷል ።
በእነ አቶ ሃብታሙ መዝገብ የተከሰሱትን ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት በነፃ አሰናብቷቸው ነበር ። ይሁንና አቃቤ ህግ ይግባን በመጠየቁ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፊታችን ማክሰኞ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic