ፍርሃትና አልበገርባይነት በካቡል | ዓለም | DW | 17.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ፍርሃትና አልበገርባይነት በካቡል

ታሊባኖች በካቡል መንግሥት ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት በማጠናከራቸዉ አፍጋኒስታን ዛሬም የተረጋጋ ሕይወት አይታይባትም። ዋና ከተማ ካቡል በየቀኑ ጦርነት ታስተናግዳለች። የጥቃት ፍንዳታዉ አላባራም። ዛሬም ከዋና ከተማዋ ብዙም ሳይርቅ ታሊባን እንደመሸገ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:48
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:48 ደቂቃ

ፍርሃትና አልበገርባይነት በካቡል

ባለፈዉ ግንቦት ወር ከባድ ጥቃት የተፈጸመበት የዉጭ ዜጎች የሚያዘወትሩት ሆቴል አሁን ታድሷል፤ በጥይት የተበሳዉ ግድግዳም በተቀባዉ ቀለም ተደፍኗል።

ሆቴሉ አሁን ታድሷል። ጥቃቱ የተዋቸዉ ጠባሳዎችም ከስመዋል። ግድግዳዉን የበሳሳዉ ጥይት ፈለግ አሁን ደብዝዞ ይልቁንም አዲስ በተቀባዉ ቀለም በመድመቁ ባለፈዉ ግንቦት ወር የደረሰዉን ጥቃት ሸፍኖታል። ሃሽማት ሃቢብ የዉጭ ሀገር ዜጎች በሚዘወትሩት የታወቀ ሆቴል ላይ በወቅቱ ጥቃት ሲደርስ በስፍራዉ ነበር።

«ከጥቂት ጓደኞቼ ጋር በሆቴሉ መናፈሻ ስፍራ ከታች ተቀምጬ ነበር። ለምሽቱ ትርኢት ከመጣዉ ዘፋኝ ጋር ሰላምታ እንደተለዋወጥን ተኩስ ሰማሁ። የሚተኮሰዉ ከላይ ነዉ። የጥበቃ ሠራተኞች የአፀፋ ተኩስ ከፈቱ። ሶስቱ ማለትም ጣልያናዊ፣ ካዛኪስታንና አፍጋናዊዉ ግደኞቼ እንደዚያ ከፊት ለፊት ተቀምጠዉ ነበር፤ ሁሉም ተገደሉ።»

ግንቦት 15 ቀን 2007ዓ,ም። ፓርክ ፓላስ ሆቴል በማዕከላዊ ካቡል የሚገኝ ብቻ ሳይሆን የዉጭ ዜጎች የሚያዘወትሩት ስፍራ ነዉ። በመናፈሻ ስፍራዉ በየምሽቱ አንድ ታዋቂ አፍጋናዊ ዘፋኝ ዝግጅቱን ያቀርባል። በዚያች የግንቦት ዕለት ግን የተለመደዉ አልተከናወነም። ሃሽማት ሃቢብ ያን ቀን የሆነዉን ፈፅሞ አይረሳዉም። ሆቴሉ በትልቅ ግንብ ከመታጠሩ በተጨማሪ ጠንክራ ጥበቃ ይደረግለታል። በዚያች ቀን ግን አንድ ሰዉ መሣሪያዉን ሰዉሮ ገብቷል። በመጀመሪያዉ ፎቅ ላይ በመመገቢያ አዳራሹ የሚገኙት ላይ ጥይቱን አዘነበዉ። ቀጠለና እነሃሺም ወደተቀመጡበት መናፈሻ አፈሙዙን አዞረና አርከፈከፈዉ፤ የከበቡት ፖሊሶችም አልቀረላቸዉም። ሃሺም ቀጠለ፤

«ገዳዩ ወደህና ወዲያ እየተዟዟረ ነዉ የሚተኩሰዉ። ሰዓቱ ረዥም ነበር። ምግብ ቤት በተቀመጡት እንግዶች እና በየእቃዉ ላይ ይተኩሳል። መሬት ላይ ተኛን። አንዳንዶች ጀርባቸዉ ላይ ተመትተዋል። ጥይቱ ከአዉቶማቲክ ጠብመንጃ ነዉ የሚወጣዉ። እንዲህ ዓይነቱ መሣሪያ ያለዉ ደግሞ ፖሊስ ብቻ ነዉ።»

ትርምሱ አምስት ሰዓታትን ወስዷል። በጥቃቱም 14 ሰዎች ተገድለዋል። ፓርክ ፓላስ ሆቴል ላይ የደረሰዉ ጥቃት ካቡል ከምታስተናግዳቸዉ በርካታ ፍንዳታዎች አንዱ መሆኑ ነዉ። ጥቃት አድራሾቹ የፍትህ ሚኒስቴር ባልደረቦች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ፤ አስደናቂ የመናፈሻ ስፍራን በፍንዳታ አናዉጠዋል፤ በአፍጋኒስታን ምክር ቤት ላይም ጥቃት አድርሰዋል በተጨማሪም ሙሉዉን ፈንጂ የጫነ ትልቅ ተሽከርካሪ በአየር እስኪንሳፈፍ አንጉደዉታል። የተመድ እንደሚለዉ ከጥር ወር አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት ብቻ ታሊባን 239 ጥቃቶችን በመላዉ አፍጋኒስታን ፈፅሟል። ከዚህ መካከል 12 ከባድ ጥቃቶች የደረሱት ካቡል ዉስጥ ነዉ። በዚህ ላይ ደግሞ ራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን ተጨማሪ በርካት የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶችን ለማድረስ ይፈልጋል። ቡድኑ ባለፉት ጥቂት ወራት አፍጋኒስታን ዉስጥ ራሱን ለማቋቋም ሲሞክር ቆይቷል። ይህ ሁሉ ሃሽማት ሃቢብን ጨምሮ በርካቶችን ግር ያሰኘ ጉዳይ ሆኗል።

«ካቡልና አካባቢዉ የታሊባን ግዛት ነዉ። ወደካንዳር በሚወስደዉ ጎዳና ላይ መሬት አለኝ። ባለፈዉ ዓመት በተደጋጋሚ ወደዚያ ሄጄ ነበር። አሁን ግን መጠንቀቅ ይሻለኛል።»

ወጣቱ ደራሲ ታቂ ባለፈዉ ታህሳስ ወር አንድ የቲያትር ሥራዉን ለማቅረብ በተገኘበት አንድ የፈረንሳይ ትምህርት ቤት ላይ ከደረሰዉ ጥቃት ለጥቂት ተርፏል።

«ፀጥታን በተመለከተ፤ ከዚያ ወዲህ የታየ ለዉጥ የለም፤ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ይደርሳሉ፤ ቦምቦችን መኪናዎች ላይ ያጣብቃሉ፤ በመንገድ ላይ ፈንጂ ያጠምዳሉ፤ ሆኖም ግን ታሊባን አንድም ክፍለ ሃገር በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ አልቻለም። እናም በዚህ ዓመት ፀጥታን በሚመለከት ምንም የተለወጠ ነገር የለም።»

ታቂ የሁለት ልጆች አባት ነዉ። ከነቤተሰቡ በየዕለቱ እንደጦር ሜዳ ተኩስ በማይጠፋበት አካባቢ ይኖራል። በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ወታደሮችን እና በመሣሪያ የተከበቡ አጥሮችን መመልከት፤ ረዥም ሰዓት የሚፈጁ የደህንነት ፍተሻዎችን ጠብቆ ማለፍ እንዲሁም ከርቀት የሚሰሙ የቦምብ ፍንዳታዎችን መስማት ለምደዋል። ያም ሆኖ ግን ታቂ የተዳከመዉ የአፍጋኒስታን የኤኮኖሚ ሁኔታ ሕዝቡን ተስፋ አስቆርጦ ትዕግስቱን እንዳያሳጣዉ ይሰጋል።

«በጣም የሚያሳስበኝ የኤኮኖሚዉ ይዞታ እየከፋ መምጣቱ ነዉ፤ ሕዝቡ ከእንግዲህ ከዚህ በላይ አይታገስም ብዬ እፈራለሁ። ምክንያቱም እንደምታየዉ ቤተሰቡን እንኳ መመገብ አልቻለም። ብዙዎች የሚረዳቸዉ እንዳጡ ማየት ይቻላል።»

ዩርገን ቬበርማን/ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic