ፍልሚያ፦ ለወርቃማው በርጩማ | አፍሪቃ | DW | 15.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ፍልሚያ፦ ለወርቃማው በርጩማ

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መንደርደሪያ ላይ ዛሬ ጋና ብለን በምንጠራት ምድር የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎችን ተፋልመዋል፤ ያ ናና አሣንቴዋ። የእኚህ አፍሪቃዊት ኅልፈተ-ዜና ከተሰማ አንድ ምእተ-ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቢቀረውም ያ አሣንቴዋ ዛሬም ድረስ በጋና እና በአፍሪቃ ልዩ በኾነ መልኩ እጅግ ብርቱ እና ጠንካራ ሴት ተደርገው ይወደሳሉ።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:57

አፍሪቃዊ ሥረ-መሠረት፤ ያ አሣንቴዋ

ዝም ብሎ መናኛ በርጩማ እንዳይመስላችሁ፤ የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በእጃቸው ሊያስገቡት የቋምጡለት በአሻንቲዎች ባሕል ዘንድ እጅግ የተከበረው የወርቅ በርጩማ ነው። ያ ናና አሣንቴዋ ለዚህ ወንበር ለመፋለም የተዘጋጁ ብቸኛዋ ሴት ነበሩ። 

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1840 አሁን ጋና ብለን በምንጠራት ሀገር በያኔዋ የአሻንቲ ግዛት ኤጂሱ ውስጥ ተወለዱ። ያ አሣንቴዋ በለጋ ዕድሜያቸው ተድረው አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል። 

በጋና ጋርደን ሲቲ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ እና ፕሬዚዳንቷ ዶክተር ቪልሔልሚና ዶንኮር የያ አሣንቴዋ የሕይወት ጉዞ ጅማሬን እንዲህ ይቃኛሉ። «ሕይወትን ሀ ብለው የጀመሩት እንደማንኛውም መደበኛ ሰው ነው። የለውዝ ተክል፣ ሽንኩርት እና ሌሎች ለምግብ የሚኾኑተክሎችን የሚያመርቱ ገበሬ ነበሩ።»   

የያ አሣንቴዋ ሕይወት ፍጹም የተቀየረው ወላጆቻቸው ሲሞቱ ነው። የኤጂሱ መሪ የበሩት ወንድማቸው ክዋሲ አፍራኔ እሳቸውን ንግሥት እናት ሲሉ ሰየሟቸው። ኾኖም ክዋሲ አፍራኔ ብዙም ሳይቆዩ በ1894 በሞት ተለዩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ከያ አሣንቴዋ ዐሥር የልጅ ልጆች መካከል አዲስ መሪ የኾኑት አንደኛው በብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ለግዞት ሲዳረጉ ያ አሣንቴዋ ወኪላቸው ኾነው ኤጂሱን አስተዳደሩ።

ይኽ ሥልጣንም በ1900 ከብሪታንያ ተወካዮች ጋር እንዲገናኙ ከተጋበዙት የጎበዝ አለቆች አንዱ እንዲሆኑ ዕድል ሰጣቸው። በስብሰባው ወቅት የብሪታንያ ተወካይ ሠር ፍሬድሪክ ሚቼል ሆድግሰን ወርቃማው በርጩማ ላይ ለመቀመጥ እንዲመጣለት ጠየቀ። ወርቃማው በርጩማ በአሻንቲዎች ዘንድ እጅግ ክብር የሚሰጠው እንጂ ማንም ዝም ብሎ የሚቀመጥበት አይደለም። የአሻንቲ ጎሣ አለቆች ወርቃማውን በርጩማ አሳልፈው ለመስጠት ጫፍ ላይ በደረሱበት ወቅት ያ አሣንቴዋ  አኹንም ድረስ ዝነኛ የኾነውን ንግግር አሠሙ። 

“እናንት የአሳንቴ ወንዶች ወደፊት የማትራመዱ ከኾነ እኛው እንጓዛለን። ለእንስት የሀገሬ ዜጎችም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ነጮችን እንፋለማለን። ከመሀከላችን የመጨረሻዋ እንስት በጦር አውድማው እስክትወድቅ ድረስ እንፋለማለን። እናንት የጎሣ አለቆች የማትዋጉ ከኾነ የአንበሳ ጎፈራችሁን በእኔ ቀሚስ ብትቀይሩ ይሻላችኋል።”

በሀገሪቱ ተቀስቅሶ የነበረው ጦርነት «የወርቃማው በርጩማ ጦርነት» በሚል ይታወቅ ነበር፤ «የ ያ አሣንቴዋ ጦርነት» የሚል ስያሜ የሰጡትም አሉ። ዶክተር ቪልሔልሚና ዶንኮር። «ያ አሣንቴዋ ለምናምንበት ነገር በጽናት እንድንቆም አስተምረውናል። ለጎሣቸውም ኾነ ለሌሎች በጣም የሚጨነቊ ነበሩ። ቢያንስ ለዓለማቸው ለመቆም እጅግ የቆረጡ፤ ለወገኖቻቸውም በጽናት ለመፋለም የተዘጋጁ ነበሩ። ለአሻንቲ ክብር ኹሌም እንደተቆረቆሩ ነበር።»

ያ አሣንቴዋ በብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ላይ ጦርነቱን በማቀጣጠል ብቻ ሳይወሰኑ በጦርነቱ ንቊ ተሳትፎም አድርገዋል። በጦር ግንባሮች ተገኝተው ወታደሮቻቸውን ስለማበረታታታቸው ብሎም ሥንቅ እና ጦር ስለማቀበላቸው ማስረጃዎች አሉ፤ በወቅቱ 60 ዓመታቸው ነበር። የጦርነቱ ግለት መብረድ የጀመረው ልጃቸው በመያዟ እጃቸውን እንዲሰጡ ከተገደዱ በኋላ ነበር። ብሪታንያውያን ያ አሣንቴዋን ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ወደምትገኘው ሲሸልስ አጋዟቸው። እዛም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1921 ሕይወታቸው እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ በግዞት ቆይተዋል።  

በዚህም አለ በዚያ ግን ብሪታንያውያን ወርቃማውን በርጩማ ማግኘት አልቻሉም። ያ አሣንቴዋም በጋናውያን ብቻ ሳይኾን በሌሎችም ዘንድ ክብርና ሞገሥን ተጎናጽፈዋል። ዳንኤል ባከር ግሎቨር ጋናዊ የፊልም ባለሞያ እና የፖለቲካ አነብናቢ (commentator) ነው። ያ አሣንቴዋን የጋና የነጻነት ተጋድሎን ያቀጣጠሉ የነጻነት ፋኖ ሲል ይገልጣቸዋል። «ለአሻንቲዎች በተዘዋዋሪ ደግሞ ለጋናውያን እና ለአፍሪቃውያን ይኽ የገዛ መሬታችን ነው፤ ማንም ከባሕር ማዶ ሠርጎ እየገባ እንዴት መኖር እንዳለብን አይነግረንም ይሉ የነበሩ ናቸው። እና ደግሞ የጦርነቱን የመሪነት ካባ በመደረብ ሴቶች ከወንዶች እኩል ናችሁ፤ ሁለተኛ ዜጋም አይደላችሁም በማለት የሰበኩ ናቸው።» 

ይኽ በእርግጥ አሁንም ድረስ እጅግ ጠቃሚ መልእክት ነው። የያ አሣንቴዋን ውርስ ለማስቀጠል ጋና ውስጥ እጅግ ምርጥ ከሚባሉ የሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች አንደኛው በስማቸው ተሠይሟል። ትውስታቸውም በመጻሕፍት፣ በፊልሞች፣ በሬዲዮ ድራማዎች፣ በዘፈኖች ብሎም በመላው ሀገሬው ልቦና ውስጥ ተቀርጾ ይገኛል።

ፒናዶ አብዱ/ ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ 

 ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

 

Audios and videos on the topic