ፌስታ እና ቁም ነገር | ዓለም | DW | 26.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ፌስታ እና ቁም ነገር

የዓየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት ፓሪስ ላይ የፈረመዉን ዉል ትራምፕ እንዲቀበሉት ማክሮን ማሳመን አልቻሉም።የፈረንሳይ ጦር የአሜሪካን ጦር ተክትሎ ሶሪያን እንዲደበድብ ትራምፕ ሲጠይቁ ማክሮ ለአዎንታ መልስ አላመነቱም።ሶሪያ የሸመቁ አሸባሪዎችን እንዲዋጋ የዘመተዉ የአሜሪካ ጦር እዚያዉ እንዲቆይ ማክሮ የሰነዘሩትን ሐሳብ ግን ትራምፕ አልተቀበሉትም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:19

 የትራምፕ፤ የማክሮ ወዳጅነት እና ልዩነት

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከየትኛዉም የዓለም መሪ የበለጠ የፈረንሳዩን አቻቸዉን ኢማንኤል ማክሮን እንደሚያቀርቡ ለማክሮ ያደረጉት ልዩ ግብዣ እና መስተንግዶ እንደመረጃ እየተጠቀሰ ነዉ።ትራምፕ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ በክብር እንግድነት የጋበዟቸዉ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንትም ለአስተናጋጃቸዉ ልዩ ክብር እንዳላቸዉ አልሸሸጉም።ይሁን እና የሁለቱ መሪዎች ጥብቅ ወዳጅነት በኢራን የኑክሌር ስምምነት፤ በተፈጥሮ ጥበቃ፤ በሶሪያ ጦርነት እና በብረት ንግድ ልዉዉጥ ላይ ያላቸዉን ልዩነት ለማቀራረብ የተከረዉ ነገር የለም።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

እሳቸዉ የዩናይትድ ስቴትስን የፕሬዝደትነት ሥልጣን በመያዝ ሽማግሌዉ ፖለቲካኛ ናቸዉ (እንደ እዉነቱ ፖለቲከኛ ሳይሆኑ ነጋዴ ናቸዉ።) ሰኔ ላይ ሰባ ሁለት ዓመታቸዉን ይደፍናሉ።ዶናልድ ትራምፕ።እኝሕኛዉ በፈረንሳይ ታሪክ የመጀመሪያዉ ወጣት ፕሬዝደንት ናቸዉ።ኢማኑኤል ማክሮ።40 ዓመታቸዉ።
በሰላሳ ሁለት ዓመት ይበላለጣሉ።የሩቅ ለሩቅ ትዉልዶች።
የትራምፕ ባለቤት ሜላኒያ ዛሬ 48ኛ ዓመታቸዉን ደፈኑ።ከባለቤታቸዉ በ24 ዓመት ያንሳሉ። የማክሮ ባለቤት ብሪዢት ከባለቤታቸዉ

በ25 ዓመት ይበልጣሉ። 65 ዓመታቸዉ።
ሽማግሌዉ ቱጃር ፕሬዝደንት አምና ሞዴል ባለቤታቸዉን አስከትለዉ ፓሪስ የገቡት፤ አሜሪካንን አስቀድማለሁ እያሉ ወዳጅ ከጠላት ሳይለዩ ሁሉንም በመናደፋቸዉ፤ ሁሉም ገሸሽ- ገለል ባደረጋቸዉ ወቅት ነበር።ኃምሌ።
ወጣቱ ፕሬዝደንት እና ጠና ያሉት ባለቤታቸዉ አትላንቲክን  አቋርጠዉ የመጡ እንግዶቻቸዉን በቅጡ ለማስተናገድ ያለደረጉት የለም።ድካማቸዉ ከንቱ አልቀረም።የአባጩን ሽማግሌ ቀልብ ማረኩ።
በእድሜ-በልምድ፤ በትዳር- በሐብት የሚቃረኑት ፈረንሳይ-አሜሪካኖች በዚያች ግብዣ ተወዳጁ።ቱጃሩ ፖለቲከኛም ዉለታ አልረሱም።እነ ማክሮንን የመጀመሪያዉ የክብር እንግዳቸዉ አድርገዉ ጋበዟቸዉ።
ዋሽግተን ሰኞ እና ማክሰኞ ።ከጆርጅ ዋሽግተን መኖሪያ ቤት እስከ ሐዉልታቸዉ፤ ከዋሽግተን ተራራማ መናፈሻ እስከ መታሰቢያ ሥፍራ ጉብኝቱ ተቀለጣጠፈ። የክብር መድፍ-ተንደቀደቀ፤ ሙዚቃ መዝሙሩ ተስረቀረቀ።
                             
መሞጋገስ፤ በቆለጳጳሱ ደመቀ።እራቱም ቀጠለ።«ሥለዚሕ ዛሬ ማታ ለፕሬዝደንት ማክሮ፤ለብሪዢት ፤ ለፈረንሳይ ልዑካን፤ ለመላዉ የፈረንሳይ ሕዝብ፤ ወዳጅነታቸን ከዚሕም የበለጠ ጥልቅ እንዲሆን ፅዋችንን እናንሳ።»
ብርጭቆዉ ተጋጨ።ሹካ፤ማንካ፤ ቢላ፤ ሳሕኑ ተቅጨለጨለ።ሻፓኝ ወይኑ ተንቆረቆረ።ፌስታ።በፌስታዉ የታየዉ የመወዳጀታቸዉ ጥብቀት በቁም ነገሩ የመለያየታቸዉን ርቀትን ማጥበብ አለመቻሉ ነዉ ድንቁ።
የዓየር ንብረት

ለዉጥን ለመግታት ድፍን ዓለም ፓሪስ ላይ የፈረመዉን ዉል ትራምፕ እንዲቀበሉት ማክሮን ማሳመን አልቻሉም።የፈረንሳይ ጦር የአሜሪካን ጦር ተክትሎ ሶሪያን እንዲደበድብ ትራምፕ ሲጠይቁ ማክሮ ለአዎንታ መልስ አላመነቱም።
ሶሪያ የሸመቁ አሸባሪዎችን እንዲዋጋ የዘመተዉ የአሜሪካ ጦር እዚያዉ እንዲቆይ ማክሮ የሰነዘሩትን ሐሳብ ግን ትራምፕ አልተቀበሉትም
                         
«መዉጣት እፈልጋለሁ።እኒያ ጀግና ተዋጊዎቻችንን ወደ ሐገራቸዉ መመለስ እወዳለሁ።ታላቅ ምግባር ፈፅመዋል።»
ከሰሜን ኮሪያን ጋር ይደረጋል በተባለዉ ድርድር ላይ የሚለያዩበት ምክንያት የለም።በሌለ ነገር የሚስማማም የሚለያይም የለም።የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር ለማስቆም ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገዉ ስምምነት ግን አላግባባቸዉም።ትራምፕ ስምምነቱ መፍረስ አለበት ይላሉ።ማክሮን ግን ይቆይ ባይ ናቸዉ።
                            
«በ2015 የተደረገዉ የኢራን ስምምነት መጥፎ ነዉ ብለዋል።እኔም ለወራት ስምምነቱ አጥጋቢ ስምምነት አይደለም ሥል ነበር።ግን እስከ 2025 ድረስ (የኢራኖችን) የኑክሌር እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያስችለናል።»
ኤማኑኤል ማክሮ።ሮብም ለዩናያትድ ስቴትስ ጥምር ምክር ቤት ያደረጉት ንግግርም ከትራም መርሕ ጋር የሚጣጣም አይደለም።ማክሮ የትራምፕ የመጀመሪያዉ የክብር እንግዳ ሆነዉ ዋሽግተን ሔዱ። በሉ፤ ጠጡ፤ አወሩ ወደ ፓሪስ ተመለሱ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች