ፌርፋክስ በኢትዮጵያ ነዳጅ ማጣሪያ ሊገነባ ነው | ኤኮኖሚ | DW | 17.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ፌርፋክስ በኢትዮጵያ ነዳጅ ማጣሪያ ሊገነባ ነው

በኢትዮጵያ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት ጥናቱን ማጠናቀቁን ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ይፋ አድርጓል፡፡ የነዳጅ ማጣሪያው በቀን 120 ሺህ፤ በዓመት ደግሞ ስድስት ሚሊዮን ቶን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም ይኖረዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:21

የነዳጅ ማጣሪያው ግንባታ በ2011 ዓ.ም ይጀመራል ተብሏል

በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ላይ የሰሩት እና አሁንም በዚያው ዘርፍ የሚንቀሳቀሱት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ስለ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ዕድገት ሽንጣቸውን ገትረው ከሚከራከሩ ሰዎች አንዱ ናቸዉ፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮችም ይህንኑ የሚመሰክሩ ንግግሮች በማቅረብም ይታወቃሉ፡፡ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ አፍሪካ መመንደግ እንዲሁም ስላላቸው ብሩህ ተስፋ ቀልብ ሳቢ በሆነ አቀራረረብ፣ በቁጥር አስደግፈው ሲተትንኑ በሙሉ ኃይል ተሞልተው ነው፡፡ በማህበራዊ መገናኛ የግል ገጻቸውም ይህንኑ የሚያንጸባርቅ አባባል አስቀምጠዋል፡፡ የትዊተር ተጠቃሚዎች ራሳቸውን በአጭሩ በሚያስተዋውቁበት ክፍል “በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ ጉዳይ ምህረት የለኝም” የሚል አንደምታ ጽሁፋቸው ይነበባል፡፡ በራሳቸው አንደበት ደግሞ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ 

“እኔ አንዱ ትልቁ ትኩረቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ዕድል፣ ትልቅ ዕድገት አለ የሚል ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡ እንደምታየው ላለፉት ዘጠኝ አስር ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ ብዙ ሰርተናል፡፡ ምክንያቱም ዕድሉ ስላለ ነው፡፡ በጣም ጥቂት አገሮች ናቸው አፍሪካ ውስጥ በዚህ ደረጃ አቅም ያላቸው፡፡ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ያላቸው፡፡ ይሄን ሁሉ መሰረታዊ እድገቶች እያየን ነው” ይላሉ አቶ ዘመዴነህ፡፡ 

ይህን እምነታቸውን ለ18 ዓመት በኃላፊነት በሰሩበት የአርነስት ኤንድ ያንግ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍም ሆነ ካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ ባሉት ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ድርጅት ወደ ተግባር ሲቀይሩ ቆይተዋል፡፡ ድርጅታቸው ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው በኢትዮጵያ የሚገነባ የነዳጅ ማጣሪያ እቅድም የእዚሁ የቆየ አቋማቸው ውጤት ነው፡፡  ፌርፋክስ ፈንድ የሚያተኩርባቸው ዘርፎች የሚዘረዝሩት አቶ ዘመዴነህ ድርጅታቸው እንዴት ወደ ነዳጅ ማጣሪያ ፊቱን እንዳዞረ ያስረዳሉ፡፡

ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ በጉዳዩ ላይ ጥናት ካደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ለማቋቋም ከውሳኔ ላይ የደረሰበት የነዳጅ ማጣሪያ በቀን 120 ሺህ፤ በዓመት ደግሞ ስድስት ሚሊዮን ቶን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም ይኖረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለው የነዳጅ መጠን ወደፊት ይገነባል የተባለው ነዳጅ ማጣሪያ ያመርተዋል ተብሎ ከታቀደው ግማሹን ያህሉ ብቻ ነው፡፡ መንግስታዊው የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ባለፈው ዓመት ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባው የነዳጅ መጠን 3.3 ሚሊዮን ቶን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ድርጅቱ ለነዳጅ ምርቶቹ 37 ቢሊዮን ብር አውጥቷል፡፡

ይገነባል የተባለው የነዳጅ ማጣሪያ በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ ከሚውለው በላይ ነዳጅ የማምረት አቅም እንዲኖረው መደረጉ የሚያሳስብ ነገር አይደለም ባይ ናቸው አቶ ዘመዴነህ፡፡ ድርጅታቸው የውጭ ገበያን ጭምር ታሳቢ እንዳደረገ የሚናገሩት ሊቀመንበሩ በምስራቅ አፍሪቃ  ያለው ፍላጎት ብቻ ከፍተኛ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ 

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነዳጅ ማጣሪያ ባለቤት ነበረች፡፡ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት 41.5 ሚሊዮን ዶላር ብድር በአሰብ ወደብ የተቋቋመው የነዳጅ ማጣሪያ ኤርትራ እንደ ሀገር ከቆመች በኋላም ለኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሎ ነበር፡፡ የካቲት 1954 ግንባታው የተጀመረው የአሰቡ የነዳጅ ማጣሪያ 500 ሺህ ቶን ነዳጅ በዓመት የማጣራት አቅም እንደነበረው መዛግብት ያመላክታሉ፡፡  የነዳጅ ማጣሪያው አግልግሎት መስጠት በጀመረበት በ1959 ዓ.ም የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍጆታ 300 ሺህ ቶን ገደማ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የነዳጅ ማጣሪያውን ከእነካቴው ያጣችው ኢትዮጵያ የተጣራ ነዳጅ ከውጭ ማስገባቷን እስካሁንም ቀጥላለች፡፡   

ነዳጅ በማታመርተው ኢትዮጵያ ፌርፋክስ ያቀደውን አይነት ግዙፍ የፔትሮ-ኬሚካል ፋብሪካ መገንባት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይሆንም ወይ?” የሚሉ አሉ፡፡ የአዋጪነቱ ጉዳይን የሚጠራጠሩ እንዳሉ ሁሉ ፋብሪካውን ለመገንባት ያስፈልጋል የሚባለው አራት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱም አልጠፉም፡፡ አቶ ዘመዴነህ ለእነዚህ ስጋቶች ምላሽ አላቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፌርፋክስ የመንግስት እና የግል አጋርነት የሚባለውን የትብብር አካሄድ ለመጠቀም አቅዷል፡፡ በድርጅቱ ምክረ ሀሳብ መሰረት የነዳጅ ማጣሪያው በፌርፋክስ ባለቤት እና አስተዳደሪነት ቢያዝም የነዳጅ ውጤቶቹን የሚረከበው የመንግስት ተቋም እንዲሆን ነው፡፡ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ይህን ኃላፊነት እየተወጣ ያለው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነው፡፡ ይህ መንግስታዊ ድርጅት ከማጣሪያው የሚወጣውን ነዳጅ ገዝቶ በብቸኝነት እንዲያከፋፍል አሊያም ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ በእቅድ ደረጃ መቀመጡን አቶ ዘመዴነህ ይናገራሉ፡፡ ማጣሪያውን ለመገንባት የታሰበበት በአፋር ክልል የሚገኘው አዋሽም የሀገሪቱ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎች ያሉበት መሆኑም ትስስሩን ለመፍጠር ያቀለዋል ተብሎ ታስቧል፡፡ 

Symbolbild Benzinpreise Öl

እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ የነዳጅ ማጣሪያውን በአዋሽ ለመገንባት መሬት ተመርተው መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ማጣሪያውን እውን ለማድረግ መጨረስ ያለባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ አልሸሸጉም፡፡ የማጣሪያው እቅድን ለመንግስት በሀሳብ ደረጃ እንደቀረበ የሚያስረዱት አቶ ዘመዴነህ ጥልቅ የሆነ ጥናት እንዲያመጡ በታዘዙት መሰረት እርሱን እያዘጋጁ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በጉዳዩ ላይም ከመንግስት ጋር ድርድር ለመጀመር ገና መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡ በመንግስት በኩል የሚፈለገው ፍቃድ ከተገኘ የነዳጅ ማጣሪያው ግንባታ በ2011 ዓ.ም ይጀመራል ተብሏል፡፡ ግንባታውም በ48 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞለታል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic