ፊሊፒንስ የአውሎንፋስ ተጎጂዎችና ርዳታዉ | ዓለም | DW | 11.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ፊሊፒንስ የአውሎንፋስ ተጎጂዎችና ርዳታዉ

ሃኢያን የተሰኘው ከባድ አዉሎነፋስ የፊሊፒንስን ምሥራቃዊ የባህር ዳርቻን ከመታ ዛሬ አራተኛ ቀን ተቆጠረ። የፈራረሱ ቤቶች መተላለፊያ መንገዶችን ዘግተዋል። የስልክ እና የመብራት መስመሮች ተቋርጠዋል።

ሃኢያን አዉሎነፋስ በፊሊፒንስ እስካሁን ከተከሰቱ የአዉሎነፋስ አደጋዎች እጅግ ከባዱ እንደሆነ ተነግሮለታል። ካለፈው ዓርብ ጀምሮ የሌይቴ አውራጃ የሆነችው ታክሎባን ከተማ ከጥቅም ውጪ ሆናለች። እንደ ፊሊፒንስ መንግሥት ከሆነ 9 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ በአውሎንፋሱ ምክንያት ተጎጂ ሆኗል። ሁሉም ማለት ይቻላል ከህይወት ጋር ትግሉን ተያይዟል።

ሁሉ ነገር ወድሟል። ምንም የቀረኝ ነገር የለም። ያለኝ ነገር የለበስኩት ልብስ እና የያዝኩት ልጄ ነው» በህይወት የተረፈ እና አቅም ያለው ምግብ እና መጠጥ ካለበት እየዘረፈም ቢሆን ይወስዳል። ይህ አንዳንድ ስልክ ከሚሰራበት አካባቢ የሚመጡ መረጃዎች ናቸው። አሁን ድረስ አንዳንድ የባህር ዳርቻ ላይ ያሉ ቦታዎች ከማንኛውም ርዳታም ይሁን ግንኙነት ተነጥለው ይገኛሉ። ከመዲና ማኒላ እና ከውጭው ሀገራት ፤ የመጠጥ ውሃ፣ መድሀኒት፣ ብርድ ልብስ እና ድንኳን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች በርዳታ መልክ ቀርበዋል። ይሁን እንጂ አሁን ድረስ ትልቅ ፈተና የሆነው ፤የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ አቀባይ አስተባባሪ ዴቪድ ካርደን እንደሚሉት የመንገድ ችግር ነው።

« ለምሳሌ 6 ሰዓት ያህል ይፈጃል፤ ከአየር ማረፊያው 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ከተማ ለመድረስ።» በየቀኑ አስክሬኖች ይሰበሰባሉ። ከወደሙት ቤቶች ስር በህይወት ያሉ ሰዎችን የማግኘት እድሉ ቀናት በተቆጠሩ ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። ፍለጋው ግን እንደቀጠለ ነው። እንደ ጀርመን ያሉ የውጭ ሀገራት የቁሳቁስ ድገፋ ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይልም ወደ አካባቢው እየላኩ ይገኛሉ። «ቴሽኒሸ ሂልፍስቬርክ» የተሰኘው የጀርመን የሲቪል እና የአደጋ ጊዜ ደራሽ ድርጅት፤ መርማሪ ቡድኑን ማኒላ ካደረሰ ድርጅት አንዱ እንደሆነ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ኒኮላስ ሄፍነር ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። እሳቸው እንደሚሉት ከሀገሪቱ መስሪያ ቤቶች ጋ በመተባበር የርዳታ ስርጭቱን ማቀድ አስፈላጊ ነው።

« የአስተባባሪነቱን ዋና ኃላፊነት የሚወስዱት ፊሊፒያኖቹ ናቸው። ማኒላ የአውሎንፋሱ ተጎጂ ባለመሆኗ የአደጋ ጊዜ ደራሽ መስሪያ ቤቶቹ በሙሉ አገልግሎት በመስጠት አቅም ላይ ነው ያሉት። እንደሰማሁት ብዙ ወታደሮች እና ፖሊሶች አደጋው ወደደረሰባቸው አካባቢዎች ተልከዋል። ስለዚህ ብቻችንን ሆነን መወሰን ያለብን ርምጃ የለም። »

በሚመጡት ቀናት ማንኛውም የርዳታ አይነቶች ወሳኝ ናቸው ይላሉ። የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ አቀባይ አስተባባሪ ካርደን፤ የአውሮፓ ኮሚሽን 3 ሚሊዮን ዮሮ ርዳታ መፍቀዱን ተናግሯል። የዮናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ 75000 ዮሮ አፋጣኝ ርዳታ፣ የጀርመን መንግሥት እንዲሁ ግማሽ ሚሊዮን ዮሮ አፋጣኝ ርዳታ ፈቅዷል። የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ቤኒግኖ አቁኖ አደጋው ወደደረሰበት አካባቢ ሄደው የታዘቡትን እንደሚከተለው ነው የገለፁት።

« ብዙ የጠፉ ሰዎች መኖራቸው ያሳዝናል። እስካሁን መሞታቸው የተረጋገጠውም በርካታ ሰዎችም እንዲሁ። አሁን ግን በተለይ በህይወት ለተረፉት ነው ትኩረታችን። በተለይም የቆሰሉት ምግብ እና ውሃ ያስፈልጋቸዋል።» 600 ኪሎ ሜትር ስፋት የነበረው ሃኢያን ከባድ አዉሎነፋስ በሰው እና በንብረት ላይ ያስከተለው ጥፋት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic