ፈተና ያጀበው የሱዳን ዲሞክራሲዊ ሽግግር  | አፍሪቃ | DW | 08.01.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ፈተና ያጀበው የሱዳን ዲሞክራሲዊ ሽግግር 

ሱዳን ውስጥ ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት የመቃወሙ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጥሏል። የአብደላ ሃምዶክ ከሥልጣናቸው መልቀቅ ለአንዳንዶች ስጋት ለሌሎች የተስፋ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:08

ትኩረት በአፍሪቃ

ሱዳን ውስጥ ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት የመቃወሙ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላም የሕዝቡ የተቃውሞ ድምጽ በመላ ሀገሪቱ እያስተጋባ ነው። ሐሙስ ዕለት በተካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ሀኪሞች እና ተቃውሞውን የሚያስተባብሩ ወገኖች ተናግረዋል። የሐሙስ ዕለቱ የተቃውሞ ሰልፍ ሀምዶክ በቅርቡ ከሥልጣን ከለቀቁ ወዲህ የተለያዩ የሱዳንን ከተሞች ያካለለ በርካቶች የተሳፉበት ሰልፍ መሆኑን ዘገባዎች ያሳያሉ። ሲቪሉ የፖለቲካ ወገን እና ወታደራዊው ኃይል የበላይነቱን ለመያዝ በሚያደርገው ሽኩቻ የሀምዶክ ከሽግግር መንግሥቱ የኃላፊነት ስፍራ መልቀቅ የሱዳንን ቀጣይ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ እንዳደረገው የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም።

በዚህ ምክንያትም አብደላ ሀምዶክ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየቶች ድብልቅ ናቸው። ለአንዳንዶቹ ሀምዶክ በዚህ አሳሳቢ ጊዜ የወሰዱት እርምጃ እንደውም ሱዳን ወደ ዴሞክራሲያው አስተዳደር ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት ግብአተ መሬት አድርገው በማሰብ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። እሳቸው የከፈቱለትን በር ተጠቅሞ ወታደራዊው ኃይል ሙሉ በሙሉ የሀገሪቱን ሥልጣን እጁ በማስገባት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሰይም ይችላል የሚል ግምትም ይሰነዝራሉ። ሌሎቹ ደግሞ እንደውም የሀምዶክ ሥልጣናቸውን መልቀቅ ውዝግብ ውስጥ የገባውን ዴሞክራሲያዊ ኃይል ወደ አንድነት ማምጣት የሚያስችል አዎንታዊ እርምጃ እንደሆነ እና የሱዳንን ጦር ኃይል ሚና አደባባይ ያወጣዋል ብለው ያስባሉ። ብሪታኒያ የሚገኙት የሱዳን ጉዳይ አጥኚው ጂሀድ ማሻሙን በአዎንታዊ ከሚመለከቱት አንዱ ናቸው። 
«ሀምዶክ ሥልጣን በመልቀቅ ጠቅመውናል፤ ምክንያቱም የጦር ኃይሉን ሚና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አጋልጠዋል። የሚፈልጉትን ሕጋዊነት አሳጥተዋቸዋል።»

ነው የሚሉት። ሀምዶክ ቀደም ሲል በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ዓ,ም የፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር መንግሥት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የተቋቋመው የሲቪል እና ወታደራዊው ኃይል ጥምር የሽግግር መንግሥት አካል ናቸው። ይኽ ጥምር የሽሽር መንግሥት ሱዳን ውስጥ የሲቪል አስተዳደርን እና ዴሞክራሲያን ለማምጣት የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል ተብሎ ሲገለጽ ነበር። ሀገሪቱ በጎርጎሪዮሳዊው 2023 ዓ.ም ምርጫ ታካሂዳለች ተብሎ በመታቀዱ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ድጋፍም ማግኘቱ ይታወሳል። ሆኖም ይኸው የሽግግር መንግሥት ዳግም ባለፈው ጥቅምት ወር መንግሥት ተካሄደበት። የድርጊቱ ፈጻሚ የሽግግር መንግሥቱ አካል የሆነው ወታደራዊው ኃይል ሲሆን ሲቪሉን ፖለቲከኛ ሃምዶክን ገለል አድርጎ ሥልጣኑን ተቆጣጠረ። ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ሃምዶክ ዳግም ወደ ቦታቸው ተመለሱ። ከዚያ አስቀድሞ በቁም እስር ላይ በነበሩበት ጊዜ ከሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታህ አልቡርሃን ጋር ባለሰ 14 ነጥብ ውል ተፈራርመዋል። ሆኖም ከዚህም በኋላ የጦር ኃይሉን በመንግሥት አስተዳደር ጣልቃ መግባት የሚቃወሙት የሀገሪቱ ዜጎች ድምጻቸውን ማሰማታቸውን አላቋረጡም። ውሉንም ያልተቀበሉት ጥቂት አይደሉም። በዚህ መሀልም ሕይወት መቀጠፉ ብዙዎችም መጎዳታቸውን ቀጥሏል።

Sudan Khartoum | Premierminister zurückgetreten | Abdalla Hamdok

አብደላ ሃምዶክ

«የሱዳናውያን ደም ውድ ነው» ያሉት ሀምዶክ ደም መፍሰሱን ማስቆም አለብን ሲሉ ተደምጠዋል። አልፈው ተርፈውም ሲቪሉ የተቃውሞ ሰልፈኛ ላይ ጥይት የተኮሱ የፖሊስ አባላትን ከሥራ እስከማባረር ደርሰዋል። ሆኖም ድርጊቱን ማስቆሙ አልተሳካላቸውም። እሳቸው ከቦታቸው በጦር ኃይሉ ተገድደው ከተነሱ ወዲህ ባሉት ሳምንታት ብቻ 57 ሱዳናውያን መገደላቸው ይፋ ሆኗል። ኻርቱም የሚገኘው የጀርመኑ ፍሪዲሪክ ኤበርት ተቋም ኃላፊ ክርስቲነ ፌሊሲ ሮኸርስ በዚህ ምክንያት አብደላ ሃምዶክ ከወሰዱት እርምጃ የተሻለ ምርጫ አላገኙም ባይ ናቸው።
«ሃምዶክ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም ማለት ይቻላል። ከጦር ኃይሉ ጋር ባለፈው ኅዳር ወር ከተስማሙ በኋላ ወታደሩን በመቃወም በሚካሄዱ ሰልፎች ላይ በየጎዳናው የሚፈሰውን ደም አስቆማለሁ ብለው ነበር። እናም ሥልጣን ለመልቀቃጠው አንዱ ምክንያት ይኽ ነው፤ በዚህ በኩል በእርግጥም አልተሳካላቸውም።» 
አንዳንድ ሱዳናውያንም ሀምዶክ ከሥልጣን መልቀቃቸውን ይደግፉታል። በተለይም ያለመታከት አደባባይ በመውጣት የጦር ኃይሉ እጁን ከመንግሥታዊ አስተዳደር እንዲያወጣ እየጠየቁ የሚሞግቱት የሀገሪቱ ዜጎች ሀምዶክ ከጀነራሉ ጋር ተፈራርመዋል በሚል የሚያወግዙትን ችግር ያለበት ውል የእሳቸው ከሥልጣኑ መነሳት እንዲስተካከል ይረዳል ብለው ያስባሉ። ገሚሶቹ ደግሞ ይኽን እንደሚቃወሙ በዚህ መሀልም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሱዳን ውስጥ እንድሚጣ በሚታገሉት ዜጎች መካከል ልዩነት መፈጠሩን የጦር ኃይሉ ከመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ይውጣ የሚለውን እንቅስቃሴ ከሚደግፉ የኻርቱም ነዋሪዎች አንዷ ፋጡማ ትናገራለች።
«ሲቪሉ ወገን እራሱ በውስጡ የተከፋፈለ ነው። ለምሳሌ ጎዳና ላይ መውጣትችን ትርጉም የለውም፤ ከጀርባ ያደረጉትን አስከፊ ስምምነት ለመለወጥ የምናደርገው አዎንታዊ አስተዋጽኦ አይኖርም የሚሉ በአንድ ወገን አሉ። ሌሎቹ ደግሞ  ልንደግፋቸው ይገባል ምናልባት በውስጥ የተፈጸሙትን ጉዳቶች ለማስተካከል ይችሉ ይሆናል ባይ ናቸው። ይኽ ደግሞ ከፍተኛ ግጭት ፈጥሯል። አሁን እሳቸው ወጥተዋል፤ ቀላል ይሆናል ብዬ አስባለሁ።»
ይኽ የፋጡማ የግል አስተያየት እንጂ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚታገሉት ሱዳናውያን አጠቃላይ አቋም አይደለም። እንዲያም ሆኖ የሀምዶክ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ብቻውን አዎንታዊ ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ተስፋ የማይጋሩት የአውሮጳ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት የአፍሪቃ ጉዳይ መርሃግብር ዳይሬክተር ቴዎዶር መርፊ የታሰበው የጥምር መንግሥት ሱዳን እንዲኖራት ግፊቱ መጠናከር ይኖርበታል ባይ ናቸው።


«ሲቪል እና የጦር ኃይሉን ያካተተ ጥምር መንግሥት ሊኖረን ይገባል ብዬ አስባለሁ። ከወዲሁ ተቃርኖው ይታያል፤ እንደሚታወቀው ተቃውሞው ቀጥሏል ይኽ ደግሞ የሲቪሎቹ የጀርባ አጥንት ማለት ነው፤ ላለፉት ጥቂት ወራትም የጦር ኃይሉ ሥልጣን ይልቀቅ የሚለው ጥያቄ ተባብሷል። ሆኖም ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይኽን እውነታ የተመለከተው አይመስለኝም። ለዚህም ነው የመጀመሪያውን ጉድኝት ሕጋዊነቱን እንዲይዝ ግፊት የሚያደርጉት።»
ብዙዎች ሱዳን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ናት በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ። ይኽን ለመሻገርም ባስቸኳይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሰየም እና ለሕዝቡ ተቃውሞ ምላሽ የሚሆን ወታደራዊ ኃይሉ ያልተካተተበት የባለሙያዎች መንግሥት ማቋቋም ግድ ይሆናል። 

ሸዋዬ ለገሠ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች