ፈረንሳይ ከኒሱ ጥቃት በኋላ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ፈረንሳይ ከኒሱ ጥቃት በኋላ

ደቡባዊ ፈረንሳይ ኒስ ውስጥ ለፈረንሳይ ብሔራዊ በዓል የሚተኮስ ርችት ሲያዩ አንድ ቱኒዝያዊ በፍጥነት ያሽከረክር በነበረው ከባድ የጭነት መኪና ሆነ ብሎየገደላቸው እና የቆሰላቸው ሰዎች ትናንት በመላ ፈረንሳይ በተካሄደ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ታስበዋል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:03

ፈረንሳይ ከኒሱ ጥቃት በኋላ

የኒሱ ስነስርዓቱ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ቫልስ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት አደጋው በደረሰበት ጎዳና ላይ ነበር የተካሄደው። ታዳሚዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የጀቧቸውን ባለሥልጣናት «ወንጀለኞች!» «ከስልጣን ውረዱ!» እያሉ ጮኽውባቸዋል።ከኒሱ አደጋ በኋላ የፈረንሳይ የፀጥታ ጥበቃ እና የስለላ ሥራ እያጠያየቀ ነው ። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ለቅንብሩ ኂሩት መለሰ
የፈረንሳይ በተለይም የኒስ ህዝብ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ማታ ከደረሰው ዘግናኝ የአሸባሪ ጥቃት ገና አላገገመም ።በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነው የ84 ሰዎችን ህይወት ያጠፋውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩትን ያቆሰለው የሽብር ጥቃት የደረሰበት መንገድ እና አደጋውን መከላከል አለመቻሉ ማስቆጨቱ ማጠያየቁ ቀጥሏል ። ባለፉት 19 ወራት ፈረንሳይ የኒሱን አደጋ ጨምሮ ሦስት መጠነ ሰፊ የሽብር ጥቃቶች ደርሰውባታል ። በጥር 2015 በምጸታዊ ምስሎቹ በሚታወቀው በፓሪሱ በሻርሊ ኤብዶ መጽሔት ቢሮዎች እና ፓሪስ ውስጥ በሚገኝ በአይሁዶች መደብር ውስጥ የደረሱት ጥቃቶች የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ 130 ሰዎች የተገደሉበት በህዳር ወር ፓሪስ ውስጥ በስድስት የተለያዩ ስፍራዎች የተጣሉት የተቀነባበሩ የሽብር ጥቃቶች ናቸው ። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ማታ ኒስ ውስጥ የፈረንሳይን ብሔራዊ በዓል ምክንያት በማድረግ የሚተኮስ ርችት ትርኢት ለማየትበተሰበሰቡ \

የከተማዋ ነዋሪዎች እና ቱሪስቶች ላይ ቱኒዝያዊው ሞሀመድ ላሁአይጅ በፍጥነት ሲያሽከረክር በነበረው 19 ቶን በሚመዝን ከባድ የጭነት መኪና ያደረሰው አደጋ ሦስተኛው ጥቃት ነው ። ከዛሬ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ወዲህ ፈረንሳይ ውስጥ በሽብር ጥቃቶች የተገደሉት ሰዎች 238 ደርሷል ። ፈረንሳይ ለምን በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ሰለባ ሆነች ? ከኒሲ አደጋ በኋላ ተደጋግሞ የሚነሳ ጥያቄ ሆኗል ። የፖለቲካ ተንታኝ እና የፈረንሳይ ጉዳዮች አዋቂ ሮንያ ኬምፒን ፈረንሳይን ለሽብር አደጋ ያጋለጧት ምክንያቶች ብዙ እና ርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው ይላሉ ።
«በመጀመሪያ ደረጃ ፈረንሳይ በአሸባሪዎች ላይ በተከፈተው ዓለም ዓቀፍ ዘመቻ ጠንካራ ተሳትፎ የምታደርግ ሃገር ናት ። የፈረንሳይ ጦር ኃይል በሶርያ እና በኢራቅ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው ቡድን በአይሲስ ይዞታዎች ላይ የቦምብ ድብደባ ያካሂዳል ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ፈረንሳይ ቅኝ ከገዛቻቸው ሃገራት የመጡ ሁለት ዜግነት ማለትም የትውልድ ሃገራቸው እና የፈረንሳይ እና ዜግነት ያላቸው በርካታ ሙስሊሞች የሚገኙባት ሃገር ናት ። እነዚህ ዜጎች በፈረንሳይ ፓስፖርት እንደ ልባቸው መውጣት እና መግባት ስለሚችሉ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ጽንፈኛ የሚሆኑበትን ሂደት ለመቆጣጠር እና ለመከታተል አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ሶርያውያን ቱኒዝያውያን ወይም ደግሞ አልጀሪያውያን ከሆኑ ፈረንሳይ ውስጥ ለመቆየት ቪዛ አያስፈልጋቸውም ። »
በኬምፒን አስተያየት ፈረንሳይን የጥቃት ዒላማ ውስጥ ያስገቧት ምክንያቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም ። ርሳቸው እንደሚሉት

Mohamed Lahouaiej-Bouhlel Aufenthaltserlaubnis

ጥቃት አድራሹ ሞሀመድ ላሁአይጅ ቡህሌል

ፈረንሳይ ውስጥ ያሉ ሁኔታዎችም ለዚህ አስተዋጽኦ አድርገዋል ።የፈረንሳይ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም ። መንግሥት በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ሃላፊነት አለብኝ ብሎ አያስብም ። ያም ማለት በሙስሊሙ ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አላደረገም ። ከዚህ ሌላ ፈረንሳይ የአሸባሪዎች የጥቃት ዒላማ ልትሆን የቻለችበት ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ምክንያቶችም አሉ ይላሉ ኬምፒን ።
«በሃገሪቱ ከፍተኛ ስራ አጥነት አለ ለ።ከህዝቡ 10 በመቶው ሥራ የለውም ።ይህ ከባድ ችግር ነው ። በተለይ ከወጣቱ 46 በመቶው መሠረቱ የውጭ ዝርያ ነው ።ከዚህ የህብረተሰብ ክፍልም አብዛኛው ሥራ አጥ እና ተስፋ የቆረጠም ነው ። በዚህ የተነሳም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ፅንፈኛ የመሆን እድላቸው የሰፋ ነው ። በመጨረሻም በፈረንሳይ የስለላ ድርጅቶች መካከል ያለው ትብብር አስቸጋሪ ነው ። የፈረንሳይ የደህንነት መስሪያ ቤቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ በበቂ ሁኔታ ተባብረው አይሰሩም ። በተደጋጋሚ የመረጃ ክፍተት ይከሰታል ። ፖለቲከኞችም በተለያዩ ድርጅቶች መካከል ትብብሩ እንዲሻሻል ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ማግኘት አልቻሉም ።አሁን እንደምናየው እነዚህ ክፍተቶች ሃገሪቱን እና ህዝቧን ብዙ ህይወት ለጠፋበት ድንገተኛ አደጋ ዳርጓል ። »
ከኒሱ ጥቃት ወዲህ መንግሥት ሃገሪቱን እና ዜጎቿን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል በቂ ሥራ አልሠራም የሚል ክስ ከየአቅጣጫው እየተሰነዘረበት ነው ። መንግሥት ግን ይህን ያስተባብላል ። የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቤርናር ካዘነቭ ሽብርን ለመከላከል መንግሥትተጨማሪ የፀጥታ ኃይሎች ማሠማራቱን ፣ ለብሔራዊ የደህንነት አገልግሎት ድጋፉን ማጠናከሩን እና የፅንፈኞችን የኢንተርኔት ድረ ገጾች መከታተል የሚያስችሉ አዳዲስ ህጎችን ማውጣቱን እንደ አብነት ያቀርባሉ ። ይህ የካዘነቭ መግለጫ ግን መንግሥትን ከወቀሳ አላዳነም ።መንግሥት እስካሁን አደጋ አድራሹ የ31 ዓመቱ ቱኒዝያዊ ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም ባይ ነው።ጥቃቱ የተፈፀመበት መንገድ ግን ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው አይሲስ የተባለው ቡድን ከሚያስተላልፉቸው የሽብር ጥሪዎች የተወሰደ መሆኑንን ግን ካዘነቭ ሳይጠቁሙ አላለፉም

። ያም የተባለ ይህ አይሲስ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን ወስዷል ። በIS ላይ በተከፈተው ዓለም ዓቀፍ ዘመቻ የምትሳተፈው ፈረንሳይ ብቻ አይደለችም ። ሌሎች ሃገራትም በዚህ ዘመቻ እየተካፈሉ በተለይ ፈረንሳይ ለተደጋጋሚ ጥቃት የተጋለጠችበት ምክንያት ይኖር ይሆን ? ኬምፒን መልስ አላቸው ።
«ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ በሚካሄደው ዘመቻ ከፍተኛ ተሳትፎ ያለቸውን ሁለት ሃገራት ከፈረንሳይ ጋር እናነፃፅር ። ለምሳሌ ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስን ከፈረንሳይ ጋር ብናነፃጽር ፈረንሳይ ከደሴቲቷ ብሪታንያ ይልቅ በመልክዐ ምድራዊ አቀማመጧ ይበልጥ በቀላሉ ሊደርስባት የሚችል አገር ናት ። በሰሜን አፍሪቃ በሳህል አካባቢ ወይም በሶሪያ እና በኢራቅ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ጽንፈኝነት ለተቀየሩ አሸባሪዎች ከፈረንሳይ ይልቅ ዩናይትድ ስቴትስ መግባት በጣም አስቸጋሪ ነው ።»
በሰላም ተጀምሮ በሰላም እስከ ምሽት የዘለቀው ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተከበረው የፈረንሳይ ብሔራዊ በዓል ፍፃሜ አረመኔያዊ ግድያ ይሆናል ብሎ የጠበቀ ቢኖር ራሱ ድርጊቱን የፈፀመው አሸባሪ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው ። ግን ለምን የዚያን እለት ደረሰ የሚሉ ጥያቄዎችም መነሳታቸው አልቀረም ። ኬምፒን እለቱ ለጥቃቱ ለምን ተመረጠ የሚለውን ሊመልሱ የሚችሉ ሁለት ፍንጮች አሉ ይላሉ ።
«በመጀመሪያ ሐምሌ 14 ተምሳሌታዊ እለት ነው ።«ነፃነት ፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት የተሰኙት የፈረንሳይ እሴቶች የሚከበሩበት ብሔራዊ በዓል ነው ። እነርሱም የጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 14 1789 የፈረንሳይ አብዮት ውጤቶች ናቸው ።በፈረንሳዩ አብዮት መነሻነት ፈረንሳይ ራስዋን የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች እናት አድርጋ ነው የምታየው ።በዚህ ዕለት የሽብር ጥቃት መፈፀሙ የሪፐብሊኩን እሴቶች አንጋራም ፣ እንቃወማቸዋለን፣ ይህንንም በተምሳሌታዊ እንቅስቃሴ እናሳያለን ነው ። ጥቃቱ ፈረንሳይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ሆነ በሃገር ውስጥ ለምትቆምላቸው ዓላማዎች በሙሉ ከባድ ምት ነው ። በሁለተኛ ደረጃ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ በተለመደው የብሔራዊ በዓል ንግግራቸው በሃገሪቱ አሸባሪነት በተሻለ ሁኔታ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለው ነበር ። የኒሱ ጥቃት በፅንፈኛ ሙስሊሞች አነሳሽነት የተፈፀመ ከሆነ ፅንፈኛ ሙስሊም አሸባሪዎች ፣በቁጥጥራችሁ ስር ልታደርጉን አትችሉም የሚል ግልጽ ምልክት ይሆናል »
የባስቲ ቀን ተብሎ በሚጠራው የፈረንሳይ አብዮት ቀን ኒስ ውስጥ የደረሰው አደጋ አስቀድሞ የተጠና እና ልምምድ የተደረገበት

እንደነበር የፖሪስ አቃቤ ህግ ትናንት ይፋ አድርጓል ። እንደ አቃቤ ህግ ጥቃት አድራሹ ሁለት ጊዜ አሸከርካሪውን ይዞ በዚሁ ጎዳና ሲመላለስ እንደነበር ለፀጥታ ጥበቃ በተገጠሙ ካሜራዎች ታይቷል ። እንደ አቃቤ ህግ ግለሰቡ ጥቃቱን ያቀደው ከበዓሉ አስቀድሞ ነው ። የፅንፈኛ ሙስሊም ባህርይ ማሳየት የጀመረውም በቅርቡ ነው ። ለተሽከርካሪው መከራያም ገንዘብ ያሰባስብ ነበር ።በኮምፕዩተሩ ላይም ከIS ጋር የተያያዙ ፍለጋዎች ያካሂድ እንደነበረ ተደርሶበታል ።ግለሰቡ አደጋውን ባደረሰበት ወቅት ከ መኪና ውስጥ ሆኖ ይተኩስ ነበር ። በመኪናው ውስጥም ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎች ተገኝተዋል ። አብዛኛው አደጋ የደረሰው ግን ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል እየተጠማዘዘ በፍጥነት ይሸክረከር በነበረው ከባድ የጭነት መኪና ግጭት ነው ። በዚሁ አደጋ ያለ አበሳቸው ከተገደሉት 84 ሰዎች መካከል 10 ሩ ህጻናት ናቸው ። በአደጋው የቆሰሉት ደግሞ 308 ደርሰዋል ። ከመካከላቸው 58ቱ እስከ ትናንት ድረስ ሆስፒታል ውስጥ ሲሆኑ 29 ኙ ደግሞ በእስትንፋስ ሰጭ መሣሪያ ድጋፍ ነው ያሉት ። እስከ ትናንት ድረስ ከሟቾቹ የ13ቱን አስከሬን መለየት አልተቻለም ። ፈረንሳይ ከጥቃቱ በኋላ በIS ላይ የጀመረችውን ጥቃት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች ። ይሁን እና በኬምፒን አስተያየት ካለፈው ዓመት አንስቶ እስካሁን በቀጠለው የአሸባሪዎች ጥቃት ምክንያት ከ10 ሺህ ወታደሮች በላይ በሃገር ውስጥ ያሰማራችው ፈረንሳይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ዘመቻ ተጨማሪ ወታደሮችን የማሰማራት አቅም ይኖራታል ተብሎ አይታሰብም ።
በኒሱ አደጋ እና በፈረንሳይ የፀጥታ ጥበቃ ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አብቅቷል ። አድማጮች በአውሮፓ እና ጀርመን ዝግጅት እንዲነሱ የምትፈልጓቸውን ሃሳቦች፣ ጥያቄዎች ፣እንዲሁም አስተያየቶቻችሁን በኤስ ኤም ኤስ ፣በኢሜል በፌስቡክ እና በዋትስ አፕ አድራሻዎቻችን እንዲሁም በደብዳቤ ላኩልን እናስተናግዳለን ።በስልክም መልዕክት ብትተዉልን ይደርሰናል ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic