ፈረንሳይን ማን ይምራት? | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.04.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ፈረንሳይን ማን ይምራት?

እሁድ ማታ ይፋ የሆነው ውጤት እንዳመለከተው ከሆነ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ቀጣዩን ምርጫ ለማሸነፍ ከባድ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ተቀናቃኛቸው ሶሻሊስቱ ፍራንሱዋ ኦሎንድ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ቀንቷቸው ሳርኮዚን አሸንፈዋል። ከአስሩ ተፎካካሪዎች መካከል ለከፍተኛው የሐገሪቱ ስልጣን የሚያበቃው የመራጭ ድምፅ ባለመገኘቱ

default

ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በፈረንሳይ

እሁድ ማታ ይፋ የሆነው ውጤት እንዳመለከተው ከሆነ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ቀጣዩን ምርጫ ለማሸነፍ ከባድ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ተቀናቃኛቸው ሶሻሊስቱ ፍራንሱዋ ኦሎንድ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ቀንቷቸው ሳርኮዚን አሸንፈዋል። ከአስሩ ተፎካካሪዎች መካከል ለከፍተኛው የሐገሪቱ ስልጣን የሚያበቃው የመራጭ ድምፅ ባለመገኘቱ ሁለተኛ ዙር የመለያ ምርጫ ቀጠሮ ተይዞለታል። ከሁለት ሳምንት በኋላ በሁለቱ ዋነኛ ተቀናቃኞች መካከል ለሚካሄደው የማጣሪያ ምርጫ የቀኝ አክራሪዎቹ ድምጽ ወሳኝነት እንደሚኖረው ከወዲሁ እየተነገረ ነው። ቀኝ አክራሪዎቹ በመጀመሪያው ዙር ፉክክር ቀላል የማይባል ውጤት አስመዝግበዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንታዊ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ እሁድ ማታ ሲገለፅ ውጤቱ ለፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ የራስ ምታት፣ ለተቀናቃኛቸው ሶሻሊስቱ ዕጩ ፍራንሱዋ ኦሎንድ ደግሞ ፌሽታ ይዞ ነበር የመጣው። ሳርኮዚ በሁለት ነጥብ ገደማ በኦሎንድ የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ መረታታቸው ተነግሯል። አሸናፊው ኦሎንድ ድሉን ተከትሎ እሁድ ማታ ቱለ ውስጥ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር አሰምተዋል።

«በዚህ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በነቂስ ወጥታችሁ የተሳተፋችሁ ውድ ያገሬ ሰዎች፣ ፈረንሳዊያት እና ፈረንሳውያን፤ 80 በመቶ ያህል መራጮች በተሳተፉበት በእንዲህ አይነቱ ለየት ያለ ምርጫ ዛሬ ማታ ብቻ ያደረግነው የመጀመሪያ ዙር ቆጠራ የሚያሳየው በጀመሪያው ዙር በድል አድራጊነት ብቅ ማለቴን ነው።»

ሶሻሊስቱ ዕጩ ተፎካካሪ ፍራንሱዋ ኦሎንድ

ሶሻሊስቱ ዕጩ ተፎካካሪ ፍራንሱዋ ኦሎንድ

የአምሳ ሰባት ዓመቱ ሶሻሊስት «አንድኛውን ምዕራፍ ዘግተው ሌላኛውን መግለጥ ለሚፈልጉ ሃይላት ሁሉ በዛሬው ምሽት ዕጩ ሆኜ መጥቼያለሁ» ሲሉም አክለውበታል። በመጀመሪያው ዙር የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 10 ዕጩዎች ተሳትፈው ነበር። ይሁንና ግን አንዳቸውም ለፕሬዚዳንትነት የሚያበቃ የመራጭ ድምፅ ባለማግኘታቸው ሁለተኛ ዙር የመለያ ምርጫ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይደረጋል። ውድድሩ በመጀመሪያው ዙር አብላጫ ድምጽ ባገኙት የሶሻሊስቱ መሪ ኦሎንድ እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ሳርኮዚ መካከል ነው የሚካሄደው። ሳርኮዚ ሚያዝያ 28 የሚደረገው ሁለተኛ ዙር ምርጫ ከመድረሱ በፊት ከተቀናቃኛቸው የሶሻሊስቱ መሪ ጋር የሚያደርጉት የክርክር ርዕሰ ጉዳይ ወደ ሶስት ከፍ እንዲል ከወዲሁ ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ዳግም ለመመረጥ

ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ዳግም ለመመረጥ

«የቀሩት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሐገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች እንዲሁም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሶስት ክርክሮችን እንዲያደርጉ ሀሳብ አቀርባለሁ። ፈረንሳዮች እውነቱን በግልጽ የማወቅ መብት አላቸው።»

ሽንፈት የቀመሱት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ለሁለተኛው ዙር ምርጫ ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት ከወዲሁ የቀኝ አክራሪዎችን ትኩረት ለመሳብ እየሞከሩ እንደሆነም ተጠቅሷል። ቀኝ አክራሪዎች ፈረንሳይ ከምንም በፊት ለፈረንሳውያን ተወላጆች መሆን አለባት የሚል መርህ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እነዚህ የውጭ ሀገር ተወላጆች ጥላቻ ያለባቸው ብሔረተኞች በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ማግኘታቸው መላው አውሮጳን ያነጋግር ይዟል። የቀኝ አክራሪው የናሽናል ፍሮንት ፓርቲ መሪ ለ ፔን በሶስተኝነት ደረጃ ነው የእሁዱን ምርጫ ያሸነፉት። እሳቸውም እሁድ ምሽት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲያደርጉ እንዲህ ነበር ያሉት፣

የቀኝ አክራሪዎች መሪ ለ ፔን ማሪን

የቀኝ አክራሪዎች መሪ ለ ፔን ማሪን

«ከፊታችን የተደቀነውን ተግባር ወደፊት ለማራመድ እና አቅጣጫውን ለማስያዝ በእርግጠኝነት ደግሞም የፈረንሳይ ሕዝብ ነፃነቱን፣ ልዕልናውን፣ ክብሩን እና ኩራቱን ወደነበረበት ለመመለስ እናንተ ታስፈልጉኛላችሁ።»

በእሁዱ ምርጫ የብሔራዊ ግንባሩ የቀኝ አክራሪዎች ፓርቲ መሪ ለ ፔን 17 ነጥብ 9 በመቶ የሚደርስ ድምፅ ነው ያገኙት። የወግ አጥባቂዎቹ መሪ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ያገኙት ነጥብ 27 ነጥብ ገደማ ቢደርስ ነው። በዚህም ከፈረንሳይ መራጮች መካከል ከአምስቱ አንዱ ለቀኝ አክራሪዎቹ መሪ ለለ ፔን ማሪን ድምፅ ሰጥቷል ማለት ነው።

ወግ አጥባቂው ሳርኮዚ ለቀኝ አክራሪዎቹ መሪ ለለፔን መራጩ የተሰጠውን ድምፅ በማጣሪያው ምርጫ ለማግኘት ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። ዞሮ ዞሮ በሁለተኛው ዙር ለውድድር የሚቀርቡት ከፍተኛ የመራጭ ድምፅ ያገኙት ኦሎንዶ እና ሳርኮዚ በመሆናቸው ለለፔን የተሰጠው የመራጮች ድምፅ ወደ አንዱ ተፎካካሪ መዞር አለበት። ለ ፔንን ተከትለው የመጀመሪያውን ዙር ፉክክር በአራተኛነት ያጠናቀቁት የግራ ክንፍ ፖለቲካ አራማጁ ዦን ሉክ ሜሎንሾ 11 ነጥብ ግድም ማግኘታቸው ታውቋል። ሜሎንሾ በሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ምርጫ ድጋፋቸውን ለሶሻሊስቱ ኦሎንዶ እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል። ወደግራም ወደ ቀኝም ያላዘነበሉት የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ፍሮንስዋ ባይሩ 9 ነጥብ 1 የመራጭ ድምፅ በማግኘት አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል። የግራ ክንፍ ፖለቲከኛው ሜሎንሾ በፈረንሳይ የቀኝ አክራሪዎች ፓርቲ መሪ የሆኑት ለ ፔን ያገኙትን የመራጭ ድምፅ አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፥

የግራ ክንፍ ፖለቲከኛው ዦን ሉክ ሜሎንሾ

የግራ ክንፍ ፖለቲከኛው ዦን ሉክ ሜሎንሾ

«የምርጫ ዘመቻችንን የቀኝ ፅንፈኞችን መላምት በመተንተን እና ጠንካራ ሂስ በመስጠቱ ላይ አነጣጥረን ማካሄዳችን ልክ ነበርን። ያን ማድረጋችን በእርግጥም ትክክል ነበር። ያ ባይሆን ኖሮ የዛሬው ውጤት ከዚህም የባሰ ያደጋ ደውል ባሰማ ነበር።»

ሜሎንሾ በእሁዱ ንግግራቸው «አሁን የምንመራው የምርጫ ዘመቻ በሰዎች መካከል ያለ ፉክክር አይደለም። በአንዲት ሀገር ውስጥ ብቻም ያለ አይደለም። ይልቁንስ ሜርክል እና ሳርኮዚ በፈጠሩት አመድ ስር ለመሆን የተገደዱትን አውሮጳውያን ሁሉ የሚመለከት ነው። ይህን አመድ ከፈረንሳይ ማስወገድ አለብን» ሲሉ ተደምጠዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ እና የጀርመኗ መራሂተ- መንግስት አንጌላ ሜርክል በአውሮጳ የሚያራምዱትን ፖሊስ ለመንቀፍ ያሰሙት ንግግር ነበር። ሳርኮዚና ሜርክል የሚያራምዱት የፖለቲካ አጋርነት ጠንከር ያለ እንደሆነ ይነገራል። አጋርነቱ የተጠናከረው በተለይ ፕሬዚዳንት ሳርኮዚ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ሆነው ብቅ ያሉ ጊዜ ነበር። ያኔ ሳርኮዚ ጀርመን በርሊን ከተማ ተገኝተው እንዲህ ነበር ያሉት፥

«የጀርመን እና የፈረንሳይ ሕዝብ ወዳጅነታቸውን ለማጠንከር በስንት መከራ ገንብተው ያቆዩትን ግንኙነት ምን ጊዜም ቢሆን መስዋዕት ልናደርግ አይገባም።»

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፈረንሳይ

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፈረንሳይ

ሜርክል ትናንት በቃል አቀባያቸው በኩል አሁንም ድጋፋቸውን ለፕሬዚዳንት ሳርኮዚ እንደሚሰጡ ገልፀዋል። በ17 ቱ የዩሮ ቃጣና ውስጥ በሚገኙ የአውሮጳ ሐገራት መካከል ሳርኮዚና ሜርክል በሚያራምዱት ፖሊሲ እና ወዳጅነት ለየት ያለ ስያሜ ማግኘታቸው ይታወቃል። ከሳርኮዚ ኮዚ የሚለውን ከሜርክል ደግሞ ሜር የሚሉትን ሆሄያት በማዳቀል ሁለቱን መሪዎች በአንድ ቃል ሜርኮዚ እያሉ የሚጠሯቸውም ብዙዎች ናቸው።

ፈረንሳይ ከዓለማችን በምጣኔ ሀብት ቀዳሚ ከሆኑ 10 ሐገራት ተርታ ትሰለፋለች። በዩሮ ቃጣና ውስጥም ያላት ድርሻ ላቅ ያለ ነው። ያም በመሆኑ፤ በፈረንሳይ ማንም ይመረጥ ማን በኅብረቱ የዩሮ ተገበያይ ሀገራት መካከል የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ነው የሚነገረው። ሚያዝያ 28 ዕሑድ ቀን የሚካሄደው ሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ምርጫ ቀጣዩ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ማን እንደሚሆን የሚለይበት ከመሆኑም በላይ በአውሮጳ ይዞት የሚመጣው ለውጥ በብዙዎች ዘንድ ጉጉት ፈጥሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 24.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14kG4

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 24.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14kG4