ፈረንሳይና ኔቶ | ዓለም | DW | 17.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ፈረንሳይና ኔቶ

የወግ አጥባቂዉ ፓርቲ አባላት የሆኑ ግን የሳርኮዚን ሐሳብ የሚጠራጠሩ አርባ ያክል እንደራሴዎች አሉ።ድምፅ ሲሰጥ ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ መቃወማቸዉ ግን እንደገና አጠራጣሪ ነዉ

default

የኔቶ ዉጉ ሚንስትሮች ፓሪስ (1966)

የፈረንሳይ ምክር ቤት ፈረንሳይ የሰሜን አትላቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ-ኔቶ) የወታደራዊ ጠቅላይ ዕዝ አባል እንድትሆን የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ባሳለፉት ዉሳኔ ላይ ዛሬ የመታመኛ ድምፅ ይሰጣል።ፈረንሳይ የኔቶ አባል ብትሆንም እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ከ1966 ከድርጅቱ ጠቅላይ ዕዝ አባልነቷ እንደወጣች ነዉ።ፈረሳይ ዳግም የዕዙ አባል ትሁን የሚለዉ ሐሳብ የሐገሪቱን ሕዝብ፥ የምክር ቤት እንደራሴዎችንም አላግባባም።ይሁንና በሥልጣን ላይ ያለዉ UMP ፓርቲ አብላጫ መቀመጫ ሥላለዉ ምክር ቤቱ የፕሬዝዳቱን ሐሳብ ያፀድቀዋል ተብሎ ነዉ-የሚጠበቀዉ።ክላዉዲያ ዴግ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናክሮታል።

ድምፅ

«ፈረንሳይ በዚሕም ብሎ በዚያ የኔቶ አባል ናት።ልዩነቱ የሚሆነዉ እኛ የአመራሩ ተካፋይ መሆን-አለመሆናችን ነዉ።ወትሮም ቢሆን አባል ነን።በዘመቻዉም ተካፍለናል።በመሠረቱ የሚቀየር ነገር የለም።እነዲያ ይመስለኛል።»

ይላሉ-ሰዉዬዉ።እኝሕኛዉ ደግሞ፥-

«በእድሜ የገፋዉ የኔ ትዉልድ ሐሳቡን አይደግፈዉም።ፈረንሳይ ከአመራሩ ከተቀየጠች ምናልባት አሜሪካ ያሻትን እንደፈለገች እንዳታደርግ ያግዳት ይሆናል።እኛ ግን መታቀቡን ነበር-የምንመርጠዉ።»

ሌላኛዉ ሌላ ነዉ-የሚሉት።

«እኔ ለኛ ለፈረንሳዮች ምንም መቀየር የለበትም የሚል እምነት አለኝ።በጣም አስፈላጊዉ ጦራችን ነዉ።ደ ጎል የነበሩት እኔ ካለሁበት በተለየ ጊዜ ነበር።የኔቶን (ዕዝ) ዳግም መየቀጡ ጥሩ-ምርጫ ሥለመሆን አለመሆኑ ግን እኔ ልወሰን አልችልም።»

የምክር ቤቱ አባላት አቋምም እንደ ወከላቸዉ ሕዝብ ሁሉ ስብጥር ነዉ።ይሁንና ከመታመኛ ድምፁ በፊት የተሰባሰበ የሕዝብ አስተያየት እንዳመለከተዉ አብዛኛዉ ሕዝብ ሐገሩ የኔቶ ዕዝ አባል መሆንዋን ይደግፋል።ይሕ ለፈረንሳይ አንድ የታሪክ ምዕራፍ የሚዘጋበት፥ሌላ የሚጀመርበት፥ ታሪካዊ እርምጃ ነዉ።ለፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ ደግሞ ድል።

ሳርኮዚ አላማ ምኞታቸዉ ሐገራቸዉ በአለም አቀፉ መድረክ ጠንከራ ያለ ተፅዕኖ ማድረግ እንድትችል ነዉ ባይ ናቸዉ።በአትላንቲክ ማዶ-ለማዶዉ የጦር ተሻራኪ ድርጅም ላቅ ያለ ሥፍራ ይገባታል ባይ ናቸዉ።

ድምፅ

«ወታደሮቸ እናዘምታለን፥ሕይወታቸዉን ለአደጋ እናጋልጣለን።(የዘመቻዉን) ሥልት እና አለማ የሚበይነዉ አካል፥ አባል ግን አይደለንም።ይሕ የሚያበቃበት ጊዜ ደርሷል።ፈረንሳይ የሚወሰነዉን ከማስፈፀም ወጥታ በዉሳኔዉ መሳተፍ አለባት።»

በኔቶ-ዉሳኔ፥ሥራ-አሰራር የተንሰራፋዉን የአሜሪካኖች ተፅኖ በመቃወም ፈረንሳይ ከድርጅቱ ዕዝ እንድትወጣ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር በ1966 የወሰኑት የቀድሞዉ የሐገሪቱ ፕሬዝዳት የሻርልስ ደጎል ፍልስፍና አቀንቃኞች ግን የሳርኮዚን መከራከሪያ ነጥብ ይጠራጠሩታል።የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትርና የሳርኮዚ ተቀናቃኝ ዶሞኒክ ደ ቪልፐ ከነዚሕ ጎራ አንዱ ናቸዉ።

ድምፅ

«ምዕራቡ ከአለም አማካይ ሥፍራ የሚቆምበት ዘመን አልፏል።ፈረንሳይ በዚሕ ወቅት በምዕራብ ሐገራት ላይ የምታተኩርበት ምክንያት ምድ ነዉ? በመልከ ምድር አቀማመጥ ሲታይ በርግጥ በምዕራቡ አለም እና በአትላንቲክ ማዶ-ለማዶዉ ጉድኝት ዉስጥ እንገኛለን።በዚሕ እንወሰናለን ማለት ግን አይደለም።ከምሥራቁና ከደቡብም ጋር የምትገኛኝ ሐገር ባለቤቶችም ነን።»

እንደ ደ ቪልፐ ሁሉ የወግ አጥባቂዉ ፓርቲ አባላት የሆኑ ግን የሳርኮዚን ሐሳብ የሚጠራጠሩ አርባ ያክል እንደራሴዎች አሉ።ድምፅ ሲሰጥ ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ መቃወማቸዉ ግን እንደገና አጠራጣሪ ነዉ።ሐሳቡ ከግራ እና ከመሐል ፖለቲከኞች የገጠመዉ ተቃዉሞ በጣም ጠንካራ ነዉ።የመሐል ፖለቲካ አቀንቃኙ ፍራንሷ ባይሩ ኔን መቀየጥ ነፃነትን አሳልፎ መስጠት ነዉ-አይነት ባይ ናቸዉ።

ድምፅ

«በኢራቁ ጦርነት ጊዜ እኛ ፈረንሳዮች እንቢኝ ማለት ችለን ነበር።አሁን ግን ይሕንን ነፃነታችንን ለድርድ ማቅረብ ነዉ።»

ፕሬዝዳት ሳርኮዚ-ይሕን ሐሳብ ቅጥፈት ይሉታል።

Autor:-Claudia Deeg/Negash Mohammed

Redaktion:-

Shewaye Legesse

►◄