ፅናትና ኢትዮጵያዊነት | ባህል | DW | 08.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ፅናትና ኢትዮጵያዊነት

ፅናትና ኢትዮጵያዊነት

«ፅናትና ኢትዮጵያዊነት በብዙ መልኩ ይገለፃል። ኢትዮጵያዉያን ግጥሞቻቸዉን፤ ቱፊቶቻችዉን፤ ዞር ብለን ብናይ የመጣዉን ሁሉ ነገር ለመቀበል፤ ትልቅ ጽናት አላቸዉ። ታሪካችንን ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ ከዝያ በኋላ የዚአድባሬ ወረራ ብሎም ሌሎች ታሪኮችን ብናያይ ኢትዮጵያዉያን በከፍተኛ ቆራጥነት ችግሮችን የመቋቋም አቅም አላቸዉ።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:20

ፅናታችን በተረቶቻችን፤ በሥነ-ቃሎቻችን ሁሉ ይገኛል

«በጦርነቱ ጊዜ ነጻ እንዲወጡ የሚታገሉላቸዉ ባርያዎች እንኳ አሳዳሪዎቻቸዉን ደግፈዉ ሊንከንን ይወጉ ነበር። ባርያነት ተገቢ ነዉ ብለዉ መሰለኝ። እኛም ጋር ጎጠኝነት ልካችን ነዉ፤ ጠባብነት የኛ ነዉ፤ የሚሉ ብዙ ሰዎች መጥፍያቸዉን ሲስሉ ፤ ጦር ሜዳ አዘጋጅተዉ ራሳቸዉ ላይ ሲተኩሱ ሲታይ ታሪክ በየትም በየትም ብሎ ራሱን ይደግማል ያስብላል። ሃገሪቱ ፈርዶባት ያዙሬት ሃገር ሆነች።» መምህርት እፀገነት ከበደ ትባላለች። የቃልና ዜማ የሥነ ጽሑፍ ምሽት አዘጋጆች መካከል አንድዋ ናት።   ቃል እና ዜማ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ባለፈዉ አርብ «ፅናትና ኢትዮጵያዊነት» በተሰኘዉ የመድረክ ከቀረበዉ ሥነ-ግጥም መነባንብና ወግ በተጨማሪ ጥበባዊ ምሽቱ በዋናነት የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን ስራዎች እያነሳ እዉቁን ታላቅ ባለቅኔ ዘክሮአል። ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ወረሃዊ የሥነ ግጥም የኪነ-ጥበብ ብሎም ግጥም በጃዝ በሚል የተለያዩ ሳምንታዊ ወራሃዊ ጥበባዊ ዝግጅቶች መታየቱ የተለመደ እየሆነ ነዉ። አዘጋጆች እንደሚሉት፤ መድረኩ ተሰባስቦ እዉቀት ግንዛቤ መቅሰምያ ከመሆኑም ባሻገር ታሪክን ማወቅያ ጥሩ የእረፍት ጊዜ ማሳለፍያም እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ አይነቱ መድረክ በመቶዎች ቢበዛ ፤ ይጠቅማል እንጂ ቁጥሩ በዛ ተብሎ ሊናቅ እንደማይገባም ያሉንን ቃል እና ዜማ ወርሃዊ የሥነ-ግጥም ምሽት አዘጋጆችን አነጋግረን ቅንብር ይዘናል።  

አራት መምህራን በመሰባሰብ በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ አበባ ላይ የጀመሩት ቃልና ዜማ የተሰኘዉ ወራሃዊ የሥነ-ጽሑፍ ምሽት፤ በመጀመርያ ዝግጅቱ ታላቁን ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን ዘክሮአል። ወር በገባ የመጨረሻዉ  አርብ ምሽት ላይ የሥነ- ግጥም፤ ኪነ-ጥበብ አፍቃሪን አዲስ አበባ ላይ ቀጠሮ የሚያሲዙት አራቱ ምሁራን በዚህ  አይነት መድረክ ላይ ታድመን ሃሳብ ብቻ ከምንሰጥ፤ ለምን እኛስ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፅ መድረክ አናዘጋጅም በሚል ብዙ ከተነጋገርንበት በኋላ የሥነ-ጽሑፍ መድረኩን በይፋ ጀምረናል ሲሉ ተናግረዋል። በየወሩ በሚታደመዉ በዚህ መድረክም በሃገሪቱ አስተዋጽኦን ያበረከተ ሰዉ እንደሚዘከር እንደሚወደስ ነዉ የገለፁት። ከመስራቾቹ መካከል አንዷመምህርት እፀገነት ከበደ ናት።

« እኔና አራቱ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼ ባለን የወዳጅነት ግንኙነት ጊዜ በአመቸ ጊዜ ስንገናኝ አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ኃሳቦችን እንለዋወጣለን። በዚህም መነሻ አንድ ቀን ለምን የሥነ-ጽሑፍ ምሽት አናዘጋጅም ወደሚል ሃሳብ መጣን። እናም ቃልና ዜማ የሚል ፕሮግራም ለማዘጋጀት ወሰንን። ቃልና ዜማ የሚለዉን ስያሜ የመረጥንበት ዋና ምክንያት ጥበብ በቃል ወይም በዜማ በመገለፁ ነዉ። በርግጥ ጥበብን ስናስብ የሚደረግም ይሆናል። ግን ቃልና ዜማ ሁሉንም ይገልጻል በሚል በስያሜዉ ጸናን። በዚህም መነሻነት፤ ነዉ የምሽቱን ወራሂ መሰናዶ ወደማዘጋጀት የገባነዉ። ያዉ ምሽቱን ሁልጊዜ ስናዘጋጅ እንዳቀድነዉ፤ በየአንዳንዱ ዝግጅት ርዕስ እንዲሰጠዉ ወይም ርዕስ እንዲኖረዉ ነዉ የፈለግነዉ። ምሽት አዘጋጅተን የተጋበዘ እንግዳ አስተያየት እንዲሰጥ ሳይሆን፤ ቅርስ ያለዉ የታሰበበት እንግዶችም ሃሳብ ሲሰነዝሩ አስበዉ አቅደዉ እንዲሆን ተደርጎ የታሰበ ነዉ። በዚህም መሰረት የመጀመርያዉ መሰናዶአችንን ጽናትና ኢትዮጵያዊነት አልነዉ። ጽናት የሚለዉ ነገር ኢትዮጵያዊነት ዉስጥ ይገለፃል ወይም እናገኘዋለን። ይም በተረኮቻችን፤ በተረቶቻችን፤ በሥነ-ቃሎቻችን ዉስጥ ሁሉ ይገኛል። በትክክል ጽናት የሚለዉ ጉዳይ ኢትዮጵያዊነት ዉስጥ እናገኘዋለን። ስለዚህም ለዚህ ድጋፍ መስጠት አለብን። አሁን ባለን የፖለቲካዊ ሁኔታ የጎደለንም ይህ ነዉ። ስለዚህ ይህን እስቲ አጉልተን እናዉጣ ስንል ነዉ የጀመርነዉ። ከዚህ ዉጭ በየዝግጅቱ ሁሉ አንዳንድ የሥነ ጥበብ ሰዎችን እንዲሁም ሃሳብን የመዘከር አላማ ነበረን ፤ የመጀመርያዉን ታላቁን የቅኔ ሰዉ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን አደረግን። »

አዲስ አበባ ከተማ የጥበባዊ ዝግጅቶች በተለያዩ ቦታዎች ይደረጋሉ። ለምሳሌ የሥነ ግጥም ምሽት በብሔራዊ ትያትር በራስ ትያትር በጣይቱ ሆቴል፤ ሥነ-ግጥም በጃዝ የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸዉ። ይህ ዝግጅት እናተ ከምታዘጋጁት ጋር ተመሳሳይ አልሆነባችሁም ወይስ ለየት ለማለት ሞክራችኋል?   

« በመሰረቱ ተመሳሳይ እንኳ ቢሆን ለሕዝቡ በቂ አይደለም። አንደኛ በነዚህ መድረኮች የማንቃት ሥራ ይሰራል። ማለትም የሌሎችም ሃሳብና አላማ ይሄ ነዉ።  ከጥበብ ባሻገር ማንቃት የሚባለዉ ጉዳይ አለ። በሃገራችን እነዚህ እነዚህ ነገሮች ገና አልተሰሩባቸዉም። ሰዉ በሚፈልገዉ ነገር፤ ለማድረግ በደረቁ ምክር ከማድረግ ይልቅ በጥበብ መንገድ ሰዎችን በሚያዝናና መንገድ ሃሳብን ማስተላለፉ ተቀባይነቱ የላቀ ይሆናል። ስለዚህ በቂ ነዉ ብለን አናስብም። ግን እኛ እንደ ፕሮግራም የተለየ ለማድረግ ሞክረናል። አንደኛ ነገር መረሃ ግብራችንን ቅርፅ ሰጥተነዋል። ለምሳሌ ዲስኩር አለዉ፤ የተወሰኑ ግጥሞች አሉት፤ ወግ አለ በቋሚነት፤ እኔም በየጊዜዉ የምጽፋቸዉ ወጎች ነበሩ፤ እና ይሄን ሁሉ አንድ መድረክ ለመስጠት ነዉ። ከዚህ ሌላ የታዳጊዎች መድረክ አለ ታዳጊዎቻችንን ወደ ጥበብ መንገድ የምንጋብዝበት አለ። አንድ ገጽ የሚባል ሌላም ቅርጽ አለን። በአንድ ገጽ ዉስጥ ታዋቂ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ በተለያየ የሞያ ዘርፍ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ከመጽሐፍ አንድ ገጽ እንዲያነቡ የምናደርግበት አለ። ስለዚህ መረሃ ግብራችን ቅርፅ ያለዉና የተዋቀረ፤ በጣም የተዘጋጀንበት መረሃግብር ነዉ የሚቀርበዉ።»              

አዘጋጆቹ እንደገለፁት ከሆነ በመድረኩ ከጠበቁት በላይ ታዳምያን መገኘታቸዉን ፤ ሊተላለፍ የተፈለገዉ መልዕክት በሚገባ መተላለፉን ፤ በተይም የመድረክ አጋፋሪ የነበረዉ አርቲስት ደረጀ ኃይሌ መረሃ-ግብሩን በተሟላ መስተንግዶ እተፈለገበት እንዲደርስ ማድረጉን የገለፀችዉ የቃልና ዜማ ወርሃዊ የሥነጽሑፍ ምሽት መስራቾች አንድዋ  መምህርት መዓዛ ሞሃመድ የዝግጅቱ ርዕስ በነበረዉ «ፅናትና ኢትዮጵያዊነት» በመሆኑ የጽንት እና ኢትዮጵያ ተምሳሌ ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ተዘክሮአል፤ ሌላዉ የጽንት ተምሳሌት ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ታጋይ እስክንድር ነጋ በመድረኩ ተጋብዞ እንደነበር ተናግራለች። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች