ፀረ ፔጊዳ የሙዚቃ ድግስ በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 27.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ፀረ ፔጊዳ የሙዚቃ ድግስ በጀርመን

ፔጊዳ የተሠኘውን እሥልምናን የሚጠላውን የጀርመን ቡድን የሚያወግዝ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባና የሙዚቃ ድግስ ቡድኑ ንቅናቄውን በጀመረበት በድሬስደን ከተማ ትናንት ምሽት ተካሂዷል ። ታዋቂው ጀርመናዊ የዘመናዊ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኽርበርት ግሮነማየር ባስተባበረውና በርካታ ሙዚቀኞች በተካፈሉበት የአደባባይ ትርዒት ላይ ከ35 ሺህ በላይ ሕዝብተገኝቷል ።

ግሮነማየር ለታዳሚዎቹ ባስተላለፈው መልዕክት ድሬስደን የሁሉም ከተማ መሆኗን አስገንዝቧል ። የትናንቱ የድሬስደን ሕዛባዊ ሥብሠባና የሙዚቃ ድግስ ዓላማ በከተማይቱ መቻቻልንና ልዩነቶችን ማክበርን አጉልቶ ማውጣት ነበር ። ራሱን «በምዕራቡ ዓለም እስልምና መስፋፋቱን የሚቃወሙ አገር ወዳድ አውሮፓውያን»ሲል የሚጠራውን በምህፃሩ ፔጊዳ የሚባለውን ሥብስብትርዒት መሪ መፈክር ለመቃወም የተካሄደው የትናንቱ የሙዚቃ ድግስ መልዕክት «ግልፅና ቅይጧ ድሬስደን ለሁሉም» የሚል ነበር። በድግሱ ላይ የተገኙ በርካታ ድምፃውያንና የሙዚቃ ባንዶች ይህንኑ መልዕክት አስተላልፈዋል ።የሙዚቃ ድግሱ አስተባባሪ ታዋቂው ጀርመናዊ የዘመናዊ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኽርበርት ግሮነማየር በድሬስደን የተጀመረው የፔጊዳ ንቅናቄ ከባድ መዘዝ ማምጣቱ አይቀርም ሲል አስጠንቅቋል ።

«በጀርመን ሰዎች ችላ ተባልን ፣በፖለቲካውም ፍላጎታችን በቁም ነገር አልታየም የሚል ቅሬታ ቢያድርባቸው በሚገባ እገነዘብላችኋለሁ ።ነገር ግን የተወሣሠበ ሥጋትን በሐይማኖት ቡድን አሰባስቦ አንድ የሐይማኖት ቡድንን ዒላማ ማድረግ ብርቱ ጥፋትን የሚያስከትል ይሆናል ።»

በድሬስደኑ ነፃ የሙዚቃ ድግስ ላይ 35 ሺህ ታዳሚዎች መገኘታቸውን አዘጋጆቹ ተናግረዋል ። ትናንት አደባባይ የወጣው ህዝብ ቁጥር ፔጊዳ ከ15 ቀን በፊት ባካሄደውና በርካታ ሰዎች በተካፈሉበት ሰልፍ ላይ ከተገኘው እጅግ የላቀ ነበር ። ጥር ሁለት 2007 ዓም ፔጊዳ በጠራው ሰልፍ 25 ሺህ የሚደርስ ደጋፊ አደባባይ ወጥቶ ነበር ። ፔጊዳ ንቅናቄውን በጀመረባት በምሥራቅ ጀርመንዋ ድሬስደን ከተማ የቀጠለው የፔጊዳ ተቃውሞ ነዋሪዎቹን ማሳሰቡ አልቀረም ። ። ሆኖም ችግሩ ይወገዳል የሚል ተስፋ አላቸው ። ይህን ተስፋ ከሚያደርጉት አንዱ በትናንቱ የድሬስደኑ ፀረ-ፔጊዳ የሙዚቃ ትርዒት ላይ የተገኙት እኚህ ታዳሚ ናቸው

«በአሁኑ ጊዜ ከተማይቱ ያጋጠማትም ሆነ የምትገንበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ። ይሁንና ችግሩን ሁሉ እንደምንወጣው አምናለሁ ። »
ሌላዋ ታዳሚደግሞ በከተማይቱ የነበረው የቀድሞው በጎ መንፈስ እንዲመለስ ነው የሚፈልጉት ።

«እንደቀድሞው እንደ ጥንቱ የድሬስደን ነዋሪነት ስሜት ሲኖር ደስ ያሰኛል ። የቅርብ ጊዜውን አሳፋሪ ሁኔታ ወደ ጎን በመተው ማለት ነው ።አንድ ሰው እንደ ቀድሞዋ ድሬስደን የዛች ከተማ ነዋሪ ነኝ ሲል የሚያኮራ ነው ። »

የድሬስደን ከተማ መስህብ በሆነው FRAUENKIRCHEN በተባለው ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በተካሄደው የሙዚቃ ድግስ ላይ ትናንት ከቀረቡት ሙዚቃዎች አብዛኛዎቹ ፔጊዳን ከመተቸት ይልቅ በመቻቻልና ከውጭ ዜጎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ላይ ያተኮሩ ነበሩ ። ካለፈው ጥቅምት አንስቶ በጀርመን የእስልምና ተፅእኖ አይሏል ሲል በየሳምንቱ ሰኞ በድሬስደን እንዲሁም በሌሎች የጀርመን ከተሞች ተቃውሞውን የሚያሰማው ፔጊዳ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥርም መጨመሩን በጥብቅ ይቃወማል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic