ፀረ ኤቦላ ስርጭት ትግል | አፍሪቃ | DW | 31.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ፀረ ኤቦላ ስርጭት ትግል

የኤቦላ ወረርሽኝ በምዕራብ አፍሪቃ ባለፈው መጋቢት ወር ከተከሰተ በኋላ በወረርሽኙ አስተላላፊ ተኀዋሲ የሚያዘው ሰው ቁጥር ከሰኔ 2014 ዓም ወዲህ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነሱን የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አስታወቀ። ዓለም አቀፉ ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሠረት፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ በተኀዋሲው ይያዝ የነበረው ሰው ብዛት ወደ 100 ወርዶዋል።

WHO Direktorin Margaret Chan zu Ebola Trendwende 25. Jan. 2015

ማርግሬት ቻን

ካለፈው ሳምንት እስካለፈው ሰኞ ድረስ 99 ሰዎች ብቻ ነበሩ በወረርሽኙ መያዛቸውን መመዝገቡን ድርጅቱ አመልክቶዋል። እስካሁን የኤቦላ ወረርሽኝ መስፋፋትን ለማስቆም ሲሰራ የቆየው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁን ትኩረቱን የብዙ ሰው ሕይወት ያጠፋውን በሽታ መቆጣጠር በሚቻልበት ሁለተኛው የትግሉ ሂደት ላይ ማሳረፍ እንደሚያስችለው የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አስታውቋል። የጀርመን መንግሥት ልዩ የኤቦላ ጉዳይ ተጠሪ ቫልተር ሊንድነር ድርጅቱ በተኀዋሲ የሚያዘው ሰው ቁጥርን በመቀነሱ ረገድ መሻሻል ታይቶዋል ባለበት አበረታቺ ዘገባ ቢስማሙም፣ የወረርሽኙ መስፋፋትን በተመለከተ ሰውን ሊያዘናጋ ስለሚችል በኤቦላ አኳያ አሁንም ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

Walter Lindner, Ebola-Beauftragter der Bundesregierung

ቫልተር ሊንድነር

« ባካባቢው ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ ካደረኩት ጉዞ አሁን ነው የተመለስኩት፣ በርግጥም፣ ለውጥ፣ ተስፋ ሰጪ ለውጥ ማየት ችያለሁ። ግን፣ በጣም ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፣ ምክንያቱም በሽታውን በመታገሉ ረገድ የምንጓዘው የመጨረሻው ርቀት በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው፣ ሰዎች በበሽታው አኳያ ያደርጉት የነበረውን ጥንቃቄ ችላ ሊሉ ይችላሉ፣ እና መሻሻል ታይቶዋል ብለን ዘና ማለት ከጀመርን ችግሩ እንደገና ሊባባስ ይችላል። አዎ፣ እውነት ነው፣ ሁኔታው ተሻሽሎዋል፣ የሚያዘው ሰው ቁጥር በሚቀጥሉት ወራት ወደ ዜሮ ዝቅ ሊል ይችል ይሆናል፣ ግን፣ በጀመርነው ጥረታችን መቀጠል ይኖርብናል። »

ወረርሽኙ ባለፈው መጋቢት በምዕራብ አፍሪቃ ከተከሰተ ወዲህ በዓለም በኤቦላ አስተላላፊ ተኀዋሲ እስካሁን 8,700 ሰዎች መሞታቸውን እና ወደ 22,000 የሚጠጉ ደግሞ በተኀዋሲው መያዛቸውን ነው የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዘገባ የሚያሳየው። ወረርሽኙ በተለይ በጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን የግብርና ዘርፍ እና በኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን በዓለም ባንክ የምዕራብ አፍሪቃ ጉዳይ ተከታታይ ክፍል ባልደረባ ቬራ ሶንግዌ አስታውቀዋል።

« ከጠቅላላ ምርታቸው ወደ ሁለት ከመቶ የሚጠጋው ቀንሶዋል። የዋጋ ግሽበቱ እስከ ሶስት፣ አራት ከመቶ ከፍ ብሎዋል። በላይቤሪያ የማዕድን ዘርፍ 20,000 ሰው ስራውን አጥቶዋል። ተቋማት እየዘጉ ነው። በኤቦላ ያልተጎዱ ጋምቢያን የመሳሰሉ ሀገራት እንኳን የቱሪስቱ ቁጥር ከ40 እስከ 60 ከመቶ ቀንሶዋል። ይህ ትልቅ ክስረት ነው። የኤቦላ ተፅዕኖ ደቡብ አፍሪቃን እና ኬንያንም እንደነካ ተመልክተናል።

ዓለም አቀፉ የግብረ ሠናይ ድርጅት፣ ኦክስፋም እነዚህ ሀገራት ከሚገኙበት የኤኮኖሚ ውድቀት ሊላቀቁ የሚችሉበት መርሀግብር እንዲጀመር እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ርዳታ እንዲያደርግ ሀሳብ አቅርቦዋል። አበዳሪ መንግሥታት በኤቦላ የተጠቁ ሶስቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የተሸከሙትን ዕዳ እንዲሽሩላቸው የተመ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን ቀደም ሲል የጠየቁ ሲሆን፣ ይኸው ጥያቄ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መወያያ ርዕስ ሆኖዋል። የተመ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን ኃላፊ ካርሎስ ሎፔስ እንዳስታወሱት፣ ጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን በአሁኑ ጊዜ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት ፣ አይ ኤም ኤፍ የተበደሩ ግነዘብ 372 ሚልዮን ዶላር ነው። ቫልተር ሊንድነር እንደሚሉት፣ በኤፀረ ኤቦላ ትግሉ አኳያ እስካሁን እንደተጠበቀው ርምጃ ያልወሰደው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ በተለይ የሶስቱ ሀገራት የጤና ጥበቃ መዋቅርን በመገንባቱ ረገድ ሰፊ ድርሻ ሊያበረክት ይገባል።

« ካንዳንድ ፣ ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅትን ከመሳሰሉ ጥቂት ድርጅቶች በስተቀር፣ ሁላችንም ርዳታ በማድረጉ ረገድ መዘግየታችንን ሁሉም የሚያውቀው ይመስለኛል። ኤቦላ አሳሳቢ ወረርሽኝ ሊሆን እንደሚችል በጣም ቀደም አድርገው ማስጠንቀቂያ አቅረበው ነበር። ፈጣን ምላሽ አልሰጠንም፤ ግን፣ ቢዘገይም፣ መርዳት ጀምረናል። አሁን ሰብዓዊው ርዳታ በሶስቱም ሀገራት ተንቀሳቅሶዋል። ከዚህ በመቀጠል ግን የሀገራቱን ልማት የሚያራምድ ድጋፍ መቅረብ ይኖርበታል። የኤቦላ ወረርሽኝ ካስከተለው መዘዝ ልንቀስመው የምንችለው ትምህርት፣ ከኤቦላ በፊትም ደካማ የነበረው የሶስቱ ምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የጤና ጥበቃ አውታር እና የትምህርት ሥርዓት፣ ባጠቃላይ ፣ መሠረተ ልማታቸው ሊጠናከር እንደሚገባ ነው። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ብቻ ነው ይህን ዓይነቱን ተመሳሳይ መዘዝ የሚያስከትል ወረርሽኝ ማስወገድ የምንችለው። »

ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተመሳሳይ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ፈጥኖ ርምጃ መውሰድ የሚችልበትን ጉዳይ የሚያጤን አንድ የተመድ ቡድን እንዲያቋቁም የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በአዳጊ ሀገራት ለሚገኙ ሕፃናት ክትባት ለማዳረስ ዘመቻ የጀመረው እና በምሕፃሩ ጋቪ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ህብረት ሰሞኑን በበርሊን ባካሄደው ጉባዔ ወቅት ሀሳብ አቅርበዋል። ይህ ሀገራት፣ በብሔራዊ እና ባካባቢ ደረጃ በመተባበር ብዙ ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ሊያመቻች እንደሚችል ቫልተር ሊንድነር ይገምታሉ።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic