ፀረ አይሁዳውያን ርምጃ በፈረንሳይ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 09.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ፀረ አይሁዳውያን ርምጃ በፈረንሳይ

ፈረንሳይ በሚኖሩ አይሁዶች በሚታየው ዘረኝነት እና በሚፈፀምባቸው ጥቃት አንፃር በርካታ ሰዎች ባለፈው እሁድ በፓሪስ አቅራቢያ በምትገኘው ክሬቴይ ሰልፍ ወጥተዋል።አይሁዶች ሀብታሞች ናቸው የሚል የቆየ አነጋገር እንዳለ ይሰማል። ይኸው አነጋገርም ዛሬም ድረስ ብዙ ጠላት አፍርቶባቸዋል።

በዚሁ ሰበብ ከጥቂት ጊዜ በፊት በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ መዳረሻ ላይ በሚገኘው የክሬቴይ ሰፈር በሁለት አይሁዳውያን ላይ የደረሰው በደል ፈረንሳይን ክፉኛ አስደንግጧል። ጥቃቱን አድራሾቹ ግለሰቦች ለጥቃቱ ሆን ብለው አይሁዳውያንን መምረጣቸውን የአይሁዳውያኑን ጥንዶች ቤት በዘረፉበት ጊዜ በግልፅ ተናግረዋል። የባል እና ሚስቱን ንብረት ከዘረፉ በኋላ፤ ባልተቤቲቷን ደፍረው መሰወራቸውም ተሰምቷል። በአሁኑ ወቅት በድርጊቱ የተጠረጠሩ ሶስት ወጣቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

ፈረንሳይ ውስጥ በአይሁዳውያን ላይ የሚደርሰው ዝርፊያ ከሀብት ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም። ከፀረ -ሴማዊነት ጋርም እንደሚገናኝ እስካሁን የደረሱት ጥቃቶች ያመላክታሉ። የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር እስከ አለፈው ክረምት ከ 500 በላይ ከፀረ- ሴማዊነት ጋር የተገናኙ ጥቃቶችን መዝግቧል። ይህ ቁጥር እጎአ በ2013 ዓም በጠቅላላው ዓመት ከደረሱት ጥቃቶች ይበልጣል። ጥቃቶች የተጣሉት ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአይሁዶች ፀሎት ቤቶች እና ሱቆችም ላይ ነው። በተለይ አብዛኞቹ ጥቃቶች የደረሱት ባለፈው ሀምሌ በተካሄደው የጋዛ ጦርነት ወቅት ነው። የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑኤል ቫልስ እየሆነ ያለውን « አዲስ ቅርፅ እየያዘ የመጣ ፀረ-ሴማዊነት » ሲሉ ጠርተውታል። ክሬቴይ ውስጥ ባለፈው ዕሁድ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ የተገኙት የሀገር ውስጥ አስተዳደር ሚኒስትር በርናር ካዜኔቭ በሀገራቸው የሚታየውን ዘረኝነት « የማህበረሰብ በሽታ» ነው ያሉት።

Marie-Christin Lux Historikerin TU Berlin

የታሪክ ምሁር የሆኑት ማሪ - ክሪስቲን ሉክስ

እንደ በርካታ ሀገራት ሁሉ የፈረንሳይ ቀደምት መንግሥታትም አይሁዳውያንን ከሀገራቸው አባረዋል። እንደዛም ሆኖ ግን በርካታ አይሁዳውያን አሁን ድረስ በፈረንሳይ ይገኛሉ።« ከፈረንሳይ አብዬት ጀምሮ ከፍተኛ የአይሁዳውያን ማህበረሰብ ፈረንሳይ ውስጥ ይገኛል። ፈረንሳይ ከጀርመን ወይም ከሌሎች የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት በፊት ለአይሁዳውያን ከፍተኛ መብት የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገርም ናት። »ይላሉ የታሪክ ምሁር የሆኑት ማሪ - ክሪስቲን ሉክስ።ስለሆነም ብዙ አይሁዳውያን ፈረንሳይን እንደ ሀገራቸው እና ራሳቸውን እንደ ፈረንሳውያን ነው የሚመለከቱት። ከዛ በኋላ ነው አይሁዳዊነት እንደሚሰማቸው የሚናገሩት። ይሁንና 40 ከመቶ የሚሆኑት ወደ ቀኝ ያመዘነው የፖለቲካ ፖርቲ፣ ፍሮ(ን) ናስዮናል ተከታዮች አይሁዶችን እንደ ፈረንሳያውያን አይቆጥሯቸውም፣ በፀረ -ሴማዊነት ላይ የተደረገ የአንድ ጥናት ውጤት እንዳሳየው። ጥናቱ እንደሚያመላክተው፤ በብዙዎች ዘንድ ስለ አይሁዶች የተሳሳተ አመለካከት አለ። ከየአምስቱ ፈረንሳዊ አንዱ አይሁዶች ብዙ የፖለቲካ ስልጣን አላቸው ሲል፣ ከየአራቱ ደግሞ አንዱ አይሁዶች በፋይናንሱ ዓለም ትልቅ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ ብሎ ያምናል። ከየአስሩ ደግሞ አንዱ ለአይሁዳዊ ተቀጥሮ መስራት እንደማይፈልግ ይናገራል። የታሪክ ምሁር ሉክስ ፈረንሳይ ውስጥ ፀረ -ሴማዊነት የቀኝ ፓርቲ ደጋፊዎች ዘንድ ብቻ የሚታይ አይደለም ይላሉ።« በኤኮኖሚ ሀብታም አይሁዳውያን የሚያሳርፉት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው የሚለው አስተሳሰብ የሚያሳዝነው አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሎዋል።

Paris Creteil Antisemitischer Überfall

በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ መዳረሻ ላይ በሚገኘው የክሬቴይ ሰፈር

ይኸው አስተሳሰብ በ19ኛው ክፍለ ዘመንም በጣም ይስተዋል ነበር። »አይሁዳውያን በኤኮኖሚ ተጫወቱት በሚባለው ጠንካራ ሚና አንፃር ፈረንሳይ ውስጥ የሚታየው አመለካከት በከፊልም ቢሆን በእስራኤል አኳያ በሚንፀባረቀው ጥሩ ያልሆነ ገፅታ ይበልጡን እየተጠናከረ መጥቷል። በተለይ በፈረንሳይ ወደ ግራ ያዘነበለው ፓርቲ ከጋዛ ሰርጥ ጦርነት በኋላ ርምጃው ያልተመጣጠነ ነበር ሲል ሂስ ይሰነዝራል።

የታሪክ ምሁር ሉክስ ፈረንሳይ ውስጥ በአይሁዶች አንፃር ዘረኝነትን እንዲስፋፋ ያደረጉ በርካታ ምክንያቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። ከምክንያቶቹ የተወሰኑት በታሪክ ተደጋግመው ተጠቅሰዋል። « ታሪክን መለስ ብለን ስንመለከት በዓለም የኤኮኖሚ ቀውስ እጎአ በ1929 ዓም ከታየ በኋላ ፀረ -ሴማዊነት ይበልጥ ተጠናክሯል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን አሁን ድረስ በሚኖሩባት ፈረንሳይ ፤ ሰሞኑን በሴማዊነት አንፃር የተደረገው ተቃውሞ በፈረንሳይ ሕዝብ ዘንድ እንዴት እንደታየ ፓሪስ የምትገኘው ወኪላችን ሀይማኖት ጥሩነህ ተጨማሪ አስተያየት ሰጥታናለች።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች