ፀረ ተላላፊ በሽታ የጦር ግብረ ኃይል | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ፀረ ተላላፊ በሽታ የጦር ግብረ ኃይል

በምዕራብ አፍሪቃ ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የኤቦላ ወረርሽኝ ለመታገል ዓ/አቀፉ ማህበረሰብ የወሰደው ርምጃ ንዑስና አዝጋሚ ነበር ሲሉ የርዳታ ድርጅቶች ወቀሳ ሰንዝረዋል። ተላላፊ በሽታ በሚከሰትበት ጊዜ ተመሳሳይ ዝግመት እንዳይታይም፣ የጀርመን መንግሥት አስቸኳይ የህክምና ርዳታ የሚሰጥ ሁሌ ዝግጁ የሚሆን የጦር ግብረ ኃይል ለማቋቋም አቅዷል።

በህክምና ርዳታ አቅርቦቱ ስራ ላይ የጦር ኃይሉ ይሰማራ መባሉ ግን ማከራከሩ አልቀረም። ኤቦላን የመሰለ ተላላፊ በሽታ ሲነሳ ፈጥኖ የሚደርስ የህክምና ርዳታ የሚሰጥ የጦር ግብረ ኃይል ይመሥረት የሚለውን የጀርመናውያኑን ሀሳብ በምዕራብ አፍሪቃ ባለፈው ዓመት ኤቦላ በተከሰተበት ጊዜ በበሽታው አንፃር ከሁሉም አስቀድሞ ርምጃ መውሰድ የጀመረው ድንበር የማይገድበው ድርጅት ያን ያህል አይደግፈውም።

የወታደር ቆብ አጥልቀው የህክምና ርዳታ መስጠት እንደማይፈልጉ የገለጹት የድርጅቱ ሊቀ መንበር ዶክተር ማክሲሚልያን ጌርትለር ተሞክሯቸውን በመጥቀስ እንዳስታወቁት፣ በርዳታ አቅርቦቱ ስራ ላይ የጦር ኃይሉ ተሳትፎ ጥርጣሬ ማስከተሉ አልቀረም።

« እኔ ራሴ ውዝግብ በበዛባቸው፣ ለምሳሌ፣ ቻድ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሰራሁበት ጊዜ አንድ ወታደር ርዳታ አቅራቢ ሆኖ ሲመጣ እንደ ጥሩ ነገር እንደማይታይ ነው የታዘብኩት። »

ኤቦላን የመሰለ ሌላ ተላላፊ በሽታ ሳይከሰት በፊት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ፣ ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት የሚለው ጥያቄ ብዙ ሊያነጋግር ቢችልም፣ አስፈላጊ መሆኑን ነው ጌርትለር በአጽንኦት ያስታውቁት።

« እርግጥ፣ ወደፊት ሌላ ኤቦላን የመሰለ ተላላፊ በሽታ ሲከሰት አስቀድሞ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉ መልካም ቢሆንም፣ አስቸኳዩን ርዳታ ለማቅረብ አዲስ መዋቅር ማዘጋጀት ወይም ሲሰራበት የቆየውን አውታር ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መተው ይበጃል። ያም ሆነ ይህ ግን በግልጽ የተረጋገጠው ነገር የቀድሞው መዋቅር በምዕራብ አፍሪቃ የተከሰተውን የኤቦላን ወረርሽኝ በመታገሉ ረገድ መክሸፉ ነው። »

በኤቦላ አንፃር እየተካሄደ ስላለው ትግል መረጃ ለማግኘት በወቅቱ በምዕራብ አፍሪቃ በመዘዋወር ላይ የሚገኙት የጀርመን የጤና ጥበቃ እና የኤኮኖሚ ልማት ትብብር መስሪያ ቤቶች ሚንስትሮች ኸርማን ግረኸ እና ጌርድ ሚውለርም ለኤቦላ ተጎጂዎች ርዳታው እጅግ አዝግሞ መንቀሳቀሱን ነው ያረጋገጡት። ሚውለር ጉዞ ከመጀራቸው በፊት እንዳስወቁት፣ ወደፊት ፈጥኖ ርዳታ የሚሰጥ አንድ ዓለም አቀፍ ቡድን ማቅረብ መቻል ተገቢ ነው፤ መስሪያ ቤታቸውም ከሶስት እስከ አምስት ቀናት ባለ ጊዜ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ርዳታ ማቅረብ የሚችል አንድ የጦር ግብረ ኃይል ዝግጁ ያደርጋል። ይሁን እንጂ፣ ይህን ዓይነቱ ግብረ ኃይል ማዘጋጀቱ ጊዜ ስለሚወስደ በቅርቡ ስራ እንደሚወስድ ሚንስትሩ ሳያስታውሱ አላለፉም።

Liberia Monrovia DRK & Bundeswehr Ebola-Hilfsstation

በሞንሮቪያ የጀርመናውያኑ የኤቦላ ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል

ኤቦላን የመሰለ ተላላፊ ተላላፊ በሽታ ሲነሳ ፈጣን የህክምና ርዳታ ሰጪ የጦር ግብረ ኃይል እንዲመሠረት እአአ በ2014 ዓም የመፀው ወራት በመጀመሪያ ለሀኪሞች እና የጤና ጥበቃ ባለሙያዎች በመጀመሪያ ሀሳብ ያቀረቡት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ነበሩ፣ ይህን ተከትሎም ሀሳቡን የደገፉት የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈው ጥር ወር፣ ተላላፊ በሽታ በማይኖርበትም ጊዜ ቋሚ ሆኖ የሚቆይ አንድ የጦር ግብረ ኃይል የሚቋቋምበትን ባለስድስት ነጥብ እቅድ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው።

የጀርመን መንግሥት በኤቦላ ለተጎዱት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የሚሰጠውን ርዳታ ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በማጠናከር እስካሁን 200 ሚልዮን ዩሮ ዝግጁ አድርጓል። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም የሲየራ ልዮን፣ ላይቤሪያ እና ጊኒን የጤና ጥበቃ አውታር መልሶ ለመገንባቱ ተግባር የሚውል ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን እንደሚሰጥ አስታውቋል። የጀርመን ብሔራዊ ጦር እና የጀርመን ቀይ መስቀል ድርጅት በላይቤሪያ መዲና ሞንሮቪያ የኤቦላ ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ቢሰሩም፣ ዘግይቶ በመጠናቀቁ ለአንድም የኤቦላ ሕሙም ህክምና አልሰጠም።

የጀርመን መንግሥት የራሱን አስቸኳይ የህክምና ሰጪ የጦር ግብረ ኃይል በሚያቋቁምበት ጊዜ ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅትን በመሳሰሉ የግል ርዳታ ድርጅቶች ተሞክሮ ላይ ጥገኛ እንደሚሆን ማክሲሚልያን ጌርትለር ገልጸዋል።

« ለርዳታ ስራችን የጤና ባለሙያዎችን እና ሀኪሞችን አሠልጥነናል። ተሞክሯችንን ለማካፈል ዝግጁ ነን። ይሁንና፣ የጦር ግብረ ኃይል የሚለውን አባባል ግን መሰረዝ ይኖርበታል። »

ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅት ኤቦላ ከተከሰተ ከመጋቢት 2014 ዓም ወዲህ ከ5,000 ለሚበልጡ ህሙማን የህክምና አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፣ በወቅቱ በሲየራ ልዮን፣ ላይቤሪያ እና ጊኒ ሰባት የህክምና ማዕከላት ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፤ ኤቦላን ለመከላከል የሚያስችለውን ክትባት እና መድሀሀኒት ፍለጋ ምርምርም ላይ እየሰራ ነው።

ፔተር ሂለ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic