ፀሐያዊ ነበልባል፥ የምድር ስጋት? | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 30.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ፀሐያዊ ነበልባል፥ የምድር ስጋት?

የምድራችን ፀሓይን ጨምሮ በሰፊው ኅዋ ላይ ፈሰው የሚርመሰመሱ እልፍ አእላፋት ከዋክብት፥ እውስጣቸው ፍንዳታዎችን ያከናውናሉ፤ በዚያም ፀሐያዊ ነበልባሎችን ያመነጫሉ። ከዋክብቱ አልፎ አልፎ መጠኑ ከተለመደው ላቅ ያለ ነበልባልም ወደ ምድር ይለቃሉ። የነበልባሉ ብርታት እና ግለት ከተለመደው እጅግ ሲልቅ ኃያሉ ነበልባል (superflare) ይከሰታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:44
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:44 ደቂቃ

ፀሓያዊ ነበልባል

ኃያሉ ፀሐያዊ ነበልባል በንጽጽር ሲታይ፦ ከርሰ ምድር እያማቧለቀች ከምትተፋው እሳተ-ገሞራ ዐሥር ሚሊዮን ያኽል መጠን እንደሚደርስ ይጠቀሳል። ለመሆኑ ኃያሉ ፀሓያዊ ነበልባል ምድራችን ላይ መከሰት ይችል ይሆን?

የዛሬ 150 ዓመት ግድም ከፀሐይ የተለቀቀ መጠነኛ ነበልባል ምድር ላይ ደርሶ ነበር። በወቅቱ ይኽ ነበልባል የዩናይትድ ስቴትሷ ግዛት ሐዋዪ እና የካናዳዋ ኩቤክ ድረስ በመዝለቅ የቴሌግራም መልእክት ማስተላለፊያ ሽቦዎችን በግለቱ ለብልቧል። መለብለብ ብቻም አይደል ሽቦዎቹን እሳት ለቆባቸው እንዳነደዳቸው ይነገራል። ነበልባሉ በምድር እና በዙሪያዋ የሚገኙ የመገናኛ አውታሮችን ሁሉ ከጥቅም ውጪ የማድረግ አቅም አለው። በአሜሪካው ብሔራዊ የጠፈር እና ኅዋ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት (NASA) ውስጥ የሚሠሩት ኢትዮጵያዊው ሣይንቲስት ዶር ጥላዬ ታደሰ።

ዶር ጥላዬ ታደሰ ከናሣ ዐሥሩ የምርምር ጣቢያዎች ግዙፍ በሆነው እና ዐሥር ሺህ ሠራተኞች በሚገኙበት ጎዳርድ የኅዋ ማዕከል ውስጥ ፀሓያት ላይ ስለሚከሰቱ ፍንዳታዎች ይመራመራሉ። የኅዋ የአየር ንብረት ቤተ-ሙከራ ውስጥም ከፀሓያት ላይ የሚነሱ ፍንዳታዎች የሚከሰቱበትን ጊዜ የሚተነብዩ ሶፍትዌሮችን ማዘጋጀትም ዋነኛ የሥራ ድርሻቸው ነው። እሳቸው የሚሠሩበት የአሜሪካው ናሣ በኅዋ ላይ ከሚብረቀረቁ ከዋክብት ከግማሽ በላይ ያኽሉ አንዱ በአንዱ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ጥንድ ከዋክብት እንደሆኑ ይገልጣል።

ኬፕለር በተሰኘው እጅግ አግዝፎ መመልከቻ ማጉያ መነጽር ከምድር በ1500 የብርሃን ዓመት ርቀት ላይ ጥንድ ከዋክብቱ የሚያደርጉት የእርስ በእርስ ሽክርክሪት በናሣ ምርምር ተኪያሂዶበታል።
ጥንድ ከዋክብት ላይ ጥናት የሚያደርጉት ተመራማሪው አቶ ጌትነት ፈለቀ ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ፤ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በቅርቡ የፒ ኤች ዲ ዲግሪያቸውን ይይዛሉ። የመመረቂያ ጥናታቸው የሚያተኩረው እርስ በእርስ የሚሽከረከሩ ጥንድ ከዋክብት (binary stars)የሽክርክሪት ባሕሪያትን መቃኘቱ ላይ ነው። ስለ ጸሓያዊ ነበልባል ባሕሪ እንዲህ ያብራራሉ።

ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ በፕላኔት አዳኙ የኬፕለር ቴሌስኮፕ የተሰባሰበውን መረጃ በጥናታቸው ወቅት ተመልክተዋል። ኬፕለር ከምድር እጅግ በርቀት ኅዋ ላይ የሚንሣፈፉ ከዋክብት በሚፈጥሩት ፍንዳታ የሚከቱ ብልጭታዎች እና ነበልባሎችን የመመልከት አቅም አለው።
በኬፕለር የታየው ነበልባል ከምድራችን ጸሓያዊ ነበልባል ጋር በባሕሪ ተመሳሳይነት እንዳለው ተገልጧል። በመጠናቸው በሦስት ይከፈላሉ።

ፀሐያችን ብርሃን ከሙቀት እያዋዛች ትልክልናለች። በሣይንሱ ዓለም ግን ከዚያም አልፋ መጥፊያችን ልትሆን ትችላለች የሚል እሳቤ አለ። ብርቱ የሆነ ፀሐያዊ ነበልባል የሣተላይት፣ የሬዲዮ ሞገድ በአጠቃላይ የመገናኛ አውታሮች መስተጓጎልን ሊያስከትል ይችላል።ፀሓያዊ ነበልባሎች ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት አደገኛ የሆኑ ጨረሮችን ይዘው ነው የሚጓዙት። ጨረሮቹ ሲፈነጥቁ የኤሌክትሪክ እና መግነጢሳዊ ባሕሪያ ያላቸውን (Electromagnetic radiations) ሞገዶች ተሸክመው ነው። እጅግ አደገኛዎቹን ጋማ ሬይ እና ኤክስ ሬይን ጨምሮ፤ አልትራቪዮሌት፣ ማይክሮዌቭ፣ ከኅዋ አካላት እና ከጋዞች የሚመነጭ ራዲዮ ዌቭ፣ ቪዝብል ላይት እና ኢንፍራሬድ የተሰኙትን ሰባቱን ሞገዶችም ይዘው ይጓዛሉ። በእርግጥ ከፀሓይ የሚፈልቁት ጎጂዎቹ ሞገዶች ወደ ምድራችን እንዳይሠርጉ ምድርን ቀንፍፎ የያዛት መግነጢሳዊ መስክ ይከላከላል።

ተመራማሪዎች ምድራችን ከ775 እስከ 993 ዓመተ ምኅረት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከተለመደው ከ10 እስከ 100 እጥፍ በሚደርስ ፀሐያዊ ነበልባል ተመትታ እንደነበር ደርሰንበታል ብለዋል። ይኽንንም ያወቅነው የተገነደሱ ዛፎች ወገብ ላይ የሚታዩ ክበቦችን በማጤን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ሲያጠቃልሉም መሰል ክስተት በዓመዓት ማለትም በሺህ ዓመት አንዴ የሚከሰት እንደሆነ ከድምዳሜ ደርሰዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic