ጸረ-ሙባረክ ሰልፈኞችና ፖሊሶች ተጋጩ | አፍሪቃ | DW | 29.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ጸረ-ሙባረክ ሰልፈኞችና ፖሊሶች ተጋጩ

የግብፅ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ መሰናበታቸውን በመቃወም በመዲናይቱ ካይሮ ደም አፋሳሽ ግጭት መቀስቀሱ ተነገረ።ሙባረክን በነፃ ያሰናበተውን የግብፅ ፍርድ ቤት ለመቃወም ታህሪር አደባባይ በወጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጸረ-ሙባረክ ሠልፈኞች እና ፖሊሶች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

ሰዎቹ የሞቱት ፖሊስ አደባባዩ ላይ የተሰበሰቡትን ሰልፈኞች በአስለቃሽ ጢስ እና በውሃ ለመበተን በተንቀሳቀሰበት ወቅት መሆኑም ተገልጿል። ሠልፈኞቹ አደባባይ የወጡት፥ የ86 ዓመቱ የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በሥልጣን ዘመናቸው ተቃውመዋቸው አደባባይ የወጡ 800 ሠልፈኞችን አስገድለዋል በሚል ተከፍቶባቸው ከነበረው ክስ በፍርድ ቤት በነፃ መሰናበታቸውን ለመቃወም ነበር ተብሏል።

Ägypten Mubarak Anklage fallengelassen jubelnde Anhänger

በተቃራኒው የሙባረክ ደጋፊዎች ስለ ሙባረክ ነፃ መሆን ሲሰሙ የተሰማቸው ደስታ

በቀድሞው የግብፅ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ ተክፍቶ የነበረው የፍርድ ችሎት ቅዳሜ ዕለት ሙባረክን ነጻ ቢያሰናብትም የ86 ዓመቱ ሙባረክ ለጊዜው በእስር ቤት እንደሚቆዩ ታውቋል። የቀድሞው መሪ ከ800 በላይ ለሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ተብለው ነበር ክስ የተመሰረተባቸው። ችሎቱ ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ግብፅን ያስተዳደሩት ሙባረክን ጨምሮ፥ የቀድሞው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃቢብ አል- አድሊ፣ ጋማል እና አላ የተባሉትን የሙባረክ ሁለት ወንድ ልጆች እና ሌሎች ተከሳሾችንም ነፃ አድርጓል። አቃቤ-ሕጉ ሙባረክ በሞት እንዲቀጡ በተደጋጋሚ ጠይቆ ነበር። እኤአ በ2011 ዓም ሙባረክን ከሥልጣን መንበራቸው ለማንሳት በተቀሰቀሰዉ ንቅናቄ በጊዜው የነበረው መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ የኃይል ርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፤ ይሁንና ሆስኒ ሙባረክ ከተወነጀሉበት ክስ ነፃ መሆናቸዉን እና «ምንም አይነት ግደሉ የሚል ትዕዛዝ» አለማስተላለፍቸዉን በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸዉ ይታወቃል። ሙባረክ በ2012 ዓም በተካሄደው ችሎት የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው፤ ባቀረቡት ይግባኝ መሰረት፤ በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ ነው የሞት ፍርዱ ተሽሮላቸው አዲስ ችሎት ተክፍቶ የነበረው።

ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ