ጦርነት፣ረሀብና በሽታ በየመን | ዓለም | DW | 11.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ጦርነት፣ረሀብና በሽታ በየመን

ላለፉት ሁለት አመታት በጦርነት የምትታመሰዉ የመን ከቅርብ ጊዚ ወዲህ ደግሞ የረሃብ አደጋና የኮሌራ በሽታ በሀገሪቱ ክፍተኛ ሰብአዊ ቀዉስ እያደረሰ መሆኑ እየተገለፀ ይገኛል።እንደተባበሩት መንግስታት ዘገባ በሀገሪቱ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰወች ለረሃብ ተጋልጠዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:47

 የ10 ሺህ የመናዉያንን ህይወት ቀጥፏል

 
የ25 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የነበረችዉ ደቡብ አረቢያዊቷ ሀገር የመን ላለፉት ዓመታት በጦርነት እየታመሰች ትገኛለች። በዚሁ ጦርነት ሳቢያ ታዲያ የሀገሪቱ በርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መደበኛ ስራቸዉ ተስተጓጉሏል። በየመን ከተሞች ከበርካታ ወራት ወዲህ የቆሻሻ ማንሳት ስራ ተቋርጧል። በተለይም በከተሞች ዳርቻ ወደር የሌለዉ የቆሻሻ ክምር ይስተዋላል። በዚሁ የከተሞች ንጽህና መጓደል ምክንያት ካለፈዉ ጥቅምት ጀምሮ በሀገሪቱ የኮሌራ በሽታ ምልክት ተመዝግቧል። የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጸዉ በ10 የሀገሪቱ ክፍለ ግዛቶች  በሽታዉ መከሰቱን አረጋግጧል። በበሽታዉ እስካሁን የ108 ሰዎች ሞት ሲመዘገብ 23 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ  በሽታዉ ሊኖርባቸዉ ይችላል የሚል ግምት አለ። አሁን አሁን በበሽታዉ በወረርሽኝ መልክ ሊይስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለም የድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን ቃል አቀባይ ሀሳን አቡ ቻር ለዜና ወክል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል።
ያም ሆኖ ግን በሽታዉ የሚያመጣዉን አደጋ ለመመከት ያስችሉ የነበሩት አብዛኛወቹ የሀገሪቱ የጤና አዉታሮችና ሆስፒታሎች በጦርነቱ በመዉደማቸዉ ችግሩን የከፋ አድርጎታል።
በየመን አሳሳቢ ከሆነዉ ጦርነትና በሽታ ባሻገር 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች  የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚያዚያ ወር ባወጣዉ ዘገባ አመልክቷል። የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽም «የመን ታላቅ የዓለም አቀፍ  የረሀብ መድረክ ናት» በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።


የሀገሪቱን  ዜጎች ለስደት፣ ለሞት፣ ለረሀብና ለበሽታ የዳረገዉ ጦርነትም እስካሁን ድረስ  መቋጫ ባለማግኘቱ በሀገሪቱ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉ ስቃይና መከራ የሚያባራ አይመስልም።
ከ2 ዓመት በፊት የሁቲ አማጽያን የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት አብድራቦ ማንሱርን በመቃወም ነፍጥ ማንሳታቸዉን ተከትሎ በሳዉዲ አረቢያ የሚመራዉ ጥምር ጦር መንግስትን በመደገፍ  የአየር ድብደባ በመጀሩ ግጭቱ እየተካረረ መጥቶ ሀገሪቱ  ራሱን እስላማዊ መንግስት «አይ ኤ ስ» ብሎ ለሚጠራዉና አልቃይዳን ለመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖችም መሸሸጊያ ሆናለች።
በሳዉዲ በሚደገፈዉ በየመን መንግስትና በኢራን በሚደገፉት በሽዓወቹ የሁቲ ሚሊሻዎች መካከል በጎርጎሮሳዊዉ 2015 የተጀመረ  የርስበርስ ጦርነት መልክ ያለዉ ቢሆንም  ከተፋላሚወቹ ጀርባ ባሉት ሀገሮች ምክንያት አሁን አሁን ጦርነቱ የዉክልና  እየሆነ መጥቷል የሚሉት ከጀርመን የዉጭ ጉዳይ የፓለቲካ ማህበረሰብ  የእስልምና የፓለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ስባስቲያን ዞንስ ናቸዉ።
«ይህ ፍጥጫ በመጀመሪያ ደረጃ የፓለቲካና የመልካምድራዊ ስልት  ፍጥጫ ነዉ።በሳዉዲ አረቢያ አመላካከት ግን ከ2003  የሳዳም ሁሴን ሁሴን ዉድቀት በሁዋላ በአካባቢዉ እያደገየመጣዉን የኢራን ተፅዕኖ ለመቋቋም ነዉ»

ተመራማሪዉ ስባስቲያን ዞንስ እንደሚሉት ይህ ግምት በመጨራሻወቹ ዓመታት የበለጠ ጉልህ እየሆነ መጥቷል።
«ሳዉዲ አረቢያ ለኢራን ወዳጅ የሆኑ ሀገሮችን የሷ ተጻራሪ አድርጋ ታያለች።ይህ ደግሞ በኢራቅ ብቻ ሳይሆን በሶርያ፣በባህሬን፣በየመንና በሊባኖስም ጭምር ነዉ።እነዚህ ሀገሮች  በሳዉዲ አረቢያ አመለካከት በኢራን ቁጥጥር ስር እንደሆኑ ነዉ የሚታወቀዉ።በኔ አመለካከት ግን ይህ ጸረ ኢራን የሆነ አመለካከት እንጅ ብዙወቹ ነጥቦች እዉነታነት የላቸዉም።»

ጦርነቱ የርስበርስም ይሁን የዉክልና  እንደ ተባበሩት መንግስታት ዘገባ እስካሁን  የ10 ሺህ የመናዉያንን ህይወት ቀጥፏል። በርካቶች ለስደት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህጻናት ደግሞ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚጠብቁ ናቸዉ። 2.2 ሚሊዮን ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ የማያገኑ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ ገሚሶቹ በከፋ የምግብ እጥረት የሚሰቃዩ መሆናቸዉን የድርጅቱ ዘገባ አመልክቷል።

ፀሐይ ጫኔ /ክኒፕ ክሪስተን

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic