ጥንቃቄ የሚሻው የአእምሮ ጤንነት | ጤና እና አካባቢ | DW | 15.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ጥንቃቄ የሚሻው የአእምሮ ጤንነት

በየ40 ሰከንዱ  አንድ ሰው ሕይወቱን እንደሚያጠፋ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ራስን የማጥፋቱ ርምጃ ደግሞ በተለይ በወጣቶች ላይ እንደሚጠና ነው የተገለጸው። ይህን ችግር የአእምሮ ጤንነትን በመጠበቅ መከላከል እንደሚገባ የዓለም የጤና ድርጅት አሳስቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:52

«ራስን ማጥፋትን ማስቆም ይቻላል»

 

የዓለም የጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና ቀን በመላው ዓለም ባለፈው ሐሙስ ሲታሰብ ራስን ማጥፋት ወይም ሲውሳይድን ዋና መነጋገሪያ እንዲሆን አቅርቧል። በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሊፈፀም የሚችለውን ይህን ድርጊት ማስቆም እንደሚቻልም ጠቁሟል። ራስ ደህና አለች የምትባል አንዲት ፍጥረት አለች። ይህ ማለት የግልን ደህንነት ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ መላ አካልን የሚዘውረው አእምሮ ጤንነቱ መጠበቅ እንደሚገባም ማመላከቻ ነው። የራስን ሕይወት በራስ እጅ ለመቅጠፍ የመወሰኑ መንስኤ ምንም ይሁን ምን ቅድሚያ ሌሎች አውቀውት ቢሆን ለመከላከል እንደሚቻል የአእምሮ ጤና ሀኪሞች ያምናሉ። እንዲህ ወዳለው ርምጃ የሚያደርሰው ከባድ ድብርት ሀኪሞቹ እንደሚሉት ዲፕረሽን ደግሞ በወጣቶች ላይ መጉላቱ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል። የወጣቶች ምድር በሆነችው ኢትዮጵያ ከድህነቱ ጋር የፍላጎቶች አለሟላት ወደዚህ የሚመራ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

 በየዓመቱ በመላው ዓለም የ800 ሺህ ሰዎች ሕይወት በዚህ መንገድ እንደሚቀጠፍ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። በየ40 ሰከንዱ ደግሞ አንድ ሰው። ድርጅቱ ባለፈው ሐሙስ ይህን ያነሳበት ዋናው ምክንያት ችግሩ እጅግ ስር የሰደደ ሆኖ ሳለ ችላ መባሉን መሠረት በማድረግ ሰዎች ከአእምሮ ጤንነት ጋር በማያያዝ እንዲነጋገሩበት እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

Symbolbild Depression

«በከባድ የድብርት ስሜት የተዋጡ ሰዎችን መርዳት ይቻላል»

ለመሆኑ ራስን የማጥፋት ድርጊት ከአእምሮ ጤንነት ጋር ምን ያገናኘዋል? በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህር እና ሀኪም የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኃይለኛ የአእምሮ ህመም ራስን ለማጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል ነው ያመለከቱት። የድብርት ስሜት ማለትም ዲፕረሽን ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ወደዚህ ድርጊት ሊያመራ እንደሚችል በመጥቀስም በዝርዝር ያስረዳሉ።  

የአእምሮ ሀኪም እና ባለሙያው እንደሚሉት አንዳንድ ሰዎች ድብርቱ የሚፈጥርባቸውን ጫና ለመገላገል ብለው ወደሱስ የሚገቡበት አጋጣሚ አለ። ያ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ አባባሽ ሊሆንባቸው ይችላል። ወጣቶች ምንም እንኳን የመጪው ኃላፊነት ተረካቢ ትውልድ መሆናቸው ቢታወቅም ከ15 እስከ 29 ዓመት በሚሆናቸው ወጣቶች ዘንድ ሕይወታቸውን ሊቀጥፍ ከሚችሉ ዋነኛ ምክንያቶች  በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ራስን ማጥፋት መሆኑ ተደርሶበታል። ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያም ላይ ተመሳሳይ እንደሆነ ነው ከፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ መረዳት የሚቻለው።

ውሎ አድሮ ወደሌላ ሊገፋፋ እንደሚችል በሚታመነው ድብርት ወይም ዲፕረሽን የተጠቁ ወጣቶች ለየት ያለ ባሕሪ  እንደሚያሳዩ ነው የአእምሮ ሀኪም እና መምህሩ የሚያሳስቡት። ወላጆችም ሆኑ መምህራን ልብ ሊሉት እንደሚገባም ያሳስባሉ።

Symbolbild Depression

«በድብት ስሜት የተዋጡ ወገኖች የሚያሳዩዋቸውን ምልክቶች አስተውሎ መርዳት ይቻላል»

የድብርቱ ስሜት የተባባሰባቸውን ሰዎች ጠጋ ብሎ መጠየቅ ማወያየቱ በሀገራችን እጅግም ያልተለመደ እና ሊያባብስ ይችላል የሚል አስተሳሰብ ቢኖርም ያንን አልፎ በችግር ውስጥ ያሉት ወገኖች ማነጋገሩ አደጋውን ለመቀነስ እንደሚረዳም ነው ባለሙያው ያስገነዘቡት። የድብርት ስሜት ያጋጠማቸው ሰዎች ሊያደርጉት ይገባል ያሉትን ዋና መፍትሄም እንዲህ ይመክራሉ.

ራስን የማጥፋቱ ጠላፊ ፈተና ማንንም ሰው የትም ቦታ ሊያጋጥመው እንደሚችል ነው የስነልቡና እና የአእምሮ ህክምና ባለሙያዎች የሚናገሩት። ግን ደግሞ ለመከላከል እንደሚቻልም አስረግጠው ይገልጻሉ።  የዓለም የጤና ድርጅት መንግሥታት ራስን የማጥፋት ድርጊት እንዳይፈፀም በብሔራዊ ደረጃ መከላከል የሚያስችል ስልት እንዲኖራቸውም ይመክራል። ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው ከምንም በላይ ደግሞ በወጣቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ አካላት የወጣቱ ችግር ምንድነው የሚለውን በትኩረት ሊሠሩበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። እያንዳንዱ ሰውም በቤተሰብ ደረጃ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታም ሆነ በጓደኝነት በሚቀራረብባቸው  መንገዶች  ሁሉ  የበኩላችንን  በማድረግ  እንዲህ ያለውን  ጸጸት  የሚያስከትል  የሰዎች  ውሳኔ  ሊያስቀር  እንደሚችል  ይታመናል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ከፍተኛ የአእምሮ ህክምና ባለሙያውን በማመስገን ለዕለቱ ያልነውን በዚሁ አበቃን።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ 

 

 

Audios and videos on the topic