ጥቃት በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ጥቃት በጀርመን

በአንድ ሳምንት ውስጥ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የደረሱት አራት ጥቃቶች ዛሬም ማነጋገራቸው ቀጥሏል ። የሰዎች ህይወት ከጠፋባቸው ከነዚህ ጥቃቶች ሦስቱ በተገን ጠያቂዎች መፈጸማቸው ደግሞ በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲ ላይ ሲሰነዘር የቆየው ትችት እንደገና ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጓል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:33

ጥቃት በጀርመን

እነዚህ ጥቃቶች ያስከተሉት ስጋት እና አንድምታቸው የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ። ከአንድ ሳምንት በፊት ፣ የዓለም በተለይም የአውሮጳ ትኩረት ዘግናኙ የኒስ ፈረንሳዩ ጥቃት ነበር ። የኒሱ አደጋ ያስከተለው ሃዘን ሳይወጣ ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የተከታተሉት ጥቃቶች ትኩረቱን ወደ ጀርመን ስበዋል ። ከጥቃቶቹ ለሁለቱ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ISIS ሃላፊነቱን መውሰዱ ደግሞ ስጋቱን አባብሶታል ። የዛሬ ሳምንት ሰኞ ማታ የ17 ዓመት አፍጋኒስታናዊ ስደተኛ በደቡብ ጀርመንዋ በቩርዝቡርግ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ባቡር ጣቢያ በመጥረቢያ ያደረሰው ጥቃት የመጀመሪያው የሽብር አደጋ ነበር ።ለጥቃቱ አይሲስ የተባለው ቡድን ሃላፊነቱን ወስዷል ። 5 ሰዎች የቆሰሉበት ይህ ጥቃት አነጋግሮ ሳያበቃ በዚያው ሳምንት አርብ በሙኒክ የ18 ዓመት ወጣት ሰው በሚያዘወትረው የገበያ ማዕከል ውስጥ እና ማዕከሉ ፊት ለፊት በሚገኝ የማክዶናልድ ምግብ ቤት ደጃፍ ላይ በሽጉጥ 9 ሰዎችን ገደለ ። ራሱን ጨምሮ የ10 ሰው ህይወት ያጠፋው ሙኒክ ተወልዶ ያደገው ይህ ወጣት ያደረሰው ጥቃት ከሽብር ጋር የተገናኘ አይደለም ቢባልም ህዝቡን ክፉኛ ረብሿል ። እሁድ በሌላዋ የደቡብ ጀርመን ከተማ ሮይትሊንገንም አንድ የ21 ዓመት ሶሪያዊ ስደተኛ አብራው የምትሰራ ፖላንዳዊትን በቆንጨራ የገደለበት እና ሁለት ሰዎች የቆሰሉበት አደጋ ሌላው የሰሞኑ አስደንጋጭ ክስተት

ነበረ ። ይህ ጥቃትም ግን ከሽብር ጋር ግንኙነት እንደሌለው ነው የተነገረው ። ጥቃቱ በዚህ ሳያበቃም አንስባህ በተባለችው የደቡብ ጀርመን ከተማ የሙዚቃ ፌስቲቫል በሚካሄድበት ስፍራ አቅራቢያ እሁድ ማታ የ27 ዓመት ሶርያዊ ባፈነዳው ጓዳ ሰራሽ ፈንጂ 15 ሰዎችን ያቆሰለበት አደጋ ነው ። ሶሪያዊው ቲኬት ባለመያዙ ፌስቲቫሉ በሚካሄድበት ስፍራ መግባት ተከለለ እንጂ ሃሳቡ የሙዚቃ ዝግጅቱን በሚከታተሉት ሰዎች ላይ መጠነ ሰፊ አደጋ ማድረስ እንደነበር ተገምቷል። በፍንዳታው ህይወቱ ያለፈው ከሁለት ዓመት በፊት በፊት ጀርመን ተሰዶ የገባው ይኽው ሶሪያዊ ጥገኘነት ተከልክሎ መጀመሪያ ወደ ተመዘገበበት ወደ ቡልጋሪያም እንዲባረር ተወስኖበት ነበር ። ሦስቱ አደጋዎች የተጣሉበት የባየርን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ትናንት እንደተናገሩት ጥቃት አድራሽ ሞባይሉ ላይ በአረብኛ በጀርመኖች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲዝት የሚያሳይ ቪድዮ ተገኝቷል ።
« በዚሁ ቪድዮ ለታዋቂው የIS መሪ ለአቡበከር አል ባግዳዲ በአላህ ስም ታማኝ መሆኑን ቃል ይገባል ።በተለይም ጀርመኖችን እበቀላለሁ ይላል ፤ ምክንያቱም ጀርመኖች እስልምናን ስለሚያደናቅፉ እና ሙስሊሞችም ስለተገደሉ መሆኑን ተናግሯል ። እንደሚመስለኝ ይህ ቪድዮ ያለ ጥርጥር ጥቃቱ ከአክራሪነት ጋር የተያያዘ እና ጥቃት አድራሹም አክራሪ አስተሳሰብ እንዳለው ያሳያል »
ባለፈው ሳምንት በተከታታይ የደረሱት እነዚህ ጥቃቶች የጀርመናውያን የሰሞኑን አብይ የመነጋገሪያ ርዕስ ናቸው ። የአደጋዎቹ መከታተል ብቻ ሳይሆን ከመካከላቸው ሁለቱ የሽብር ጥቃቶች መሆናቸው ፍርሃት እና ስጋት ያሳደረባቸው ጥቂት አይደሉም

።ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አደጋው ከደረሰበት አካባቢ ርቀው የሚገኙ እነዚህ የቦን ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ሌሎች ሃገሮች ውስጥ ሲደርስ ያዩት እና ይሰሙት ሰሙት አደጋ ወደ ሃገራቸው መምጣቱ አስደንግጧቸዋል ።
«እዚህ ጀርመን ውስጥ በመድረሱ አዝኛለሁ እውነቱን ለመናገር ደንግጫለሁ ።ፍርሃት አለ የእለት ተዕለት ኑሮአችንን ግን አይለውጠውም »
«አልተረጋጋሁም ወደ ፍርሃትና መርበትበት ውስጥ መግባት ግን አልፈልግም ፤ ምክንያቱም የሽብር ዓላማ ይህ ነው እና የአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ዘግናኝ ነው ። በቀጥታ የሚያሰራጩት እና በይሆናል የሚናገሯቸው መላምቶች እኔ እንደሚመስለኝ ሁኔታዎችን እያባባሱ ነው »
«በሚቀጥለው ሳምንት እዚህ ቦን ፌስቲቫል ይካሄዳል ትኬት ገዝቻለሁ ። ልሂድ አልሂድ ገና እያሰብኩ ነው ። ፍርሃቱ አለ የልጅ እናት ነኝ ። ባለቤቴ እና እኔ በዚህ ምክንያት ራሳችንን መገደብ እንደሌለብን ተነጋግረናል። ምክንያቱም መኖር አለብን እእንሄዳለን ሆኖም ማሰባችን አይቀርም ።»
ሆኖም አብዛኛዎቹ ተጠያቂዎች ስጋት ቢኖራቸውም አደጋው የትም ሊደርስ ይችላል ፤ ፍጹም የሚባል ፀጥታም ስለሌለ የዕለት ተዕለት ህይወታችን እንደ ቀድሞው ይቀጥላል እንጂ አይለወጥም ነው ያሉት ። ከጥቃቶቹ ሦስቱ በስደተኞች መፈፀማቸው ወትሮም ስደተኞች መግባታቸውን ሲቃወሙ እና ይህን መሰሉ አደጋ ሊያደርሱብን ይችላሉ እያሉ ሲያስጠነቅቁ ለነበሩት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል ። ይህ ሰበብ ሆኖም ጀርመኖች ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር አንስቶ ሃገራቸው ስላስገቧቸው ከ1

Deutschland Ansbach Explosion Pressekonferenz Innenminister von Bayern Joachim Herrmann

የባየርን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዮአሂም ሄርማን

ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ስደተኞች የነበራቸው አመለካከት እንደሚለወጥ ግልጽ ነው ይላሉ እኚህ አስተያየት ሰጭ ።
«አዎ በሚያሳዝን ሁኔታ ይሄ አስተሳሰብ መቀየሩ አይቀርም ።ይህንንም ከሰዎች ጋር ስነጋገር በየቡና ቤቱ በየጎዳናው የሚነሳ ነገር ሆኗል ። ወደ ዚህ በተሰደዱት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማካሄድ እንደሚገባ ነው የምረዳው ። በድንበሩም በኩል ቢሆን »
የአንስባሁ ጥቃት የሽብር ጥቃት መሆኑ ከተደረሰበት በኋላ የጀርመን የፀጥታ ባለሥልጣናት በተገን ጠያቂዎች ላይ ጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር እንደሚደረግ እና ለፀጥታ ጥበቃውም ተጨማሪ ፖሊሶች እንደሚቀጠሩ አስታውቀዋል ።የፌደራል ጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዜር በበኩላቸው ጀርመን ከመጡት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ግድያ እና ክትትል ሸሽተው የመጡ ናቸው፣ ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ጥቂቶቹ በመሆናቸው ሁሉንም በአንድ ዓይን ማየቱ ስህተት ነው ይላሉ ። ሚኒስትሩ ሌሎች መሰል አደጋዎችን ለመከላከል ግን ህዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ጥብቅ የፀጥታ ጥበቃ ተግባራዊ እንዲሆን ማዘዛቸውን ተናግረዋል ።
«በአሁኑ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው ስፍራዎች ተጨማሪ ፖሊሲችን ማሰማራት ነው ። ስለዚህ የፌደራል ፖሊስ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ፣ በባቡር ጣቢያዎች እና በተጨማሪም በድንበር አካባቢ የተጠናከረ ጥበቃ እንዲያደርግ አዝዣለሁ ።»

Thomas de Maiziere PK Bombenexplosion Ansbach

የፌደራል ጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደ ሚዜር

ሦስቱ አደጋዎች የደረሱባት የደቡባዊቷ የባየርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ሃገራችን ውስጥ የገቡትን ሰዎች ማንነት ማወቅ አለብን ሲሉ ሶሪያዊው አንዲት ነፍሰጡር የገደለበት የባየርን አጎራባች የባድን ቩርተምበርግ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ጀርመን በእንግድነት የምታደርግላቸውን አቀባበል ለሌላ ዓላማ የሚያውሉ ወደ መጡበት ሃገር መመለስ አለባቸው ብለዋል ። ጀርመን በIS ላይ በሚካሄደው ዓለም ዓቀፍ ዘመቻ ከሚሳተፉ ሃገራት አንዷ መሆኗ ለዚህ ጥቃት እንዳጋለጣት ይገመታል ። ሆኖም ጀርመን እንደ ብሪታንያ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም ሩስያ የአየር ድብደባዎች አታካሂድም ። ጀርመን በድብደባው በቀጥታ ባትሳተፍም ቃኚ የጦር አውሮፕላኖችን የጦር መርከቦች እና አየር ላይ ቤንዚን የሚሞሉ የጦር አውሮፕላኖችን እንዲሁም ወታደሮችን ግን ልካለች ። የዶቼቬለ የበርሊን ዘጋቢ ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው አሸባሪዎች አሁን ጀርመንን ጨምሮ በሌሎችም የአውሮጳ ሃገራት ጥቃት የሚጥሉባቸው ቦታዎች እና ጥቃት የሚያደርሱበት መንገድ ከከዚህ ቀደሞቹ መለየታቸው ጥቃቱን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተግዳሮት ሆኗል ።
ይሁን እና የአሸባሪዎች ዓላማ የሆነውን ፍርሃትን ማስፈንን መከላከል በጀርመን አሁን ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው እንደ ይልማ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች