ጥቃት በመቃዲሾ | አፍሪቃ | DW | 02.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ጥቃት በመቃዲሾ

የሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ሚሊሽያዎች ጥቃት አድርሰው ከ 12 ሰዓታት በላይ የተቆጣጠሩትን ሞቃዲሾ የሚገኝ አንድ ሆቴል ሙሉ በሙሉ ማስለቀቁን የሶማሊያ መንግስት ዛሬ አስታወቀ ። ትናንት ቡድኑ ከሆቴሉ ጋር አላትሞ ባፈነዳው ቦምብ እና ፍንዳታውን በተከተለው ተኩስ ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:56

ጥቃት በመቃዲሾ

ከሟቾቹ መካከል የሶማሊያ ምክር ቤት አባላት ይገኙበታል ። ትናንት ማምሻውን ነበር መሃል መቅዲሾ የሚገኘው ባለ ስድስት ፎቁ «አምባሳደር» የተባለው ሆቴል በአሸባብ አጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት የተጣለበት ። አንድ ቦምብ ያጨቀ መኪና ከሆቱሉ ህንፃ ጋር ሲላተም ከባድ ፍንዳታ ተሰማ ፤ አካባቢው በጪስ ተሸፈነ ፤ሁሌም ሰው በማይጠፋበት በአቅራቢያ በሚገኘው የማካ አል ሙካራማ ጎዳና ላይ የነበሩ መኪናዎች ጋዩ መንገዱም በስብርባሪዎች ተሞላ ።በአካቢው የነበረ አንድ የአይን ምስክር እንዳለው ፍንዳታው አካባቢውን በጠቅላላ አውድሟል ። ከፍንዳታው በኋላ ሆቴሉን ጥሰው የገቡ ታጣቂዎች ከመንግሥት ወታደሮች ጋር እስከ ዛሬ ማለዳ ድረስ ሲታኮሱ ነበር ። ለሊቱንም በቀጠለው በዚህ ጥቃት ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል ። 55 ደግሞ ቆስለዋል ። ከሟቾቹ መካከል ሁለት የምክር ቤት አባላት ይገኙበታል ።ሦስት የምክር ቤት አባላት ደግሞ ከአደጋው መትረፋቸውን መቃዲሾ የሚገኘው ጋዜጠኛ ሃሰን ኢስቲላ ተናግሯል ። ሃሰን እንደሚለው አደጋ የተጣለበት ሆቴል በምክር ቤት አባላትና በዓለም ዓቀፍ እንግዶች የሚዘወተር ነው ።
« አምባሳደር ሆቴል የምክር ቤት አባላትና የተለያዩ ባለሥልጣናት ፣ ዓለም ዓቀፍ አምባሳደሮችን በሆቴሉ የሚኖሩ የምክር

ቤት አባላትን ለማግኘት የሚመጡበት ስፍራ ነው። »
ሃሰን እንዳለው የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮችና አሸባብ ሲታኮሱበት በነበረው ሆቴል የሚሆነውን ለማወቅ እስከ ዛሬ ማለዳ ድረስ አስቸጋሪ ነበር ። አሸባብ ሃላፊነቱን በወሰደበት በዚህ ጥቃት ሶስት አጥፍቶ ጠፊዎች ተገድለዋል ። አንደኛው ቦምብ የጫነውን ተሽከርካሪ ከሆቴሉ ጋር ያላተመው ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ሆቴሉን ጥሰው በመግባት ተኩስ የከፈቱት አጥፍቶ ጠፊዎች ናቸው ። የሶማሊያ መንግሥት ፣ ከፍንዳታው በኋላ ለ12 ሰዓታት በሆቴሉ ውስጥ የቀጠለው ጥቃት ማብቃቱን ዛሬ ጠዋት አስታውቋል ። ይሁንና የትናንቱ ጥቃት መቅዲሾን ለማረጋጋት እየጣርን ነው የሚሉት የሶማሊያ መንግሥትና የአፍሪቃ ህብረት ኃይሎች ከባድ ፈተና ውስጥ እንደሚገኙ አመልካች ተደርጎ ተወስዷል ። ጋዜጠኛ ሃሰን እንደሚለው መቅዲሾ ከመረጋጋት ይልቅ ውጊያ የሚካሄድባት ከተማ ሆናለች ።
«የሶማሊያ የደህንነት እና የፖሊስ መሥሪያ ቤት በሞቃዲሾ ሁኔታዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል እያሉ ነው ። ሆኖም በሞቃዲሾ

አሁን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት እየተባባሰ ነው የሄደው ። የሶማሊያ መንግሥትና አሸባብ ማዕከላዊ ሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ሞቃዲሾ ነው ውጊያ የሚያካሂዱት ።»
አሸባብ የትናንቱን ከባድ ጥቃት ያደረሰው ከኬንያው የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ጥቃት ጋር ግንኙነት አለው የተባለው ዳውድ የተባለው የአሸባብ የደህንነት ክንፍ ሃላፊ መገደሉን ለመበቀል ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል ። ዳውድ የተገደለው በደቡብ ሶማሊያ በታችኛው ሸበሌ አካባቢ የሶማሊያ መንግሥት እና ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ መሆኑን ጋዜጠኛ ሃሰን ተናግሯል ። መቅዲሾ ውስጥ ባለፈው የካቲትም አሸባብ በሌላ ሆቴል ላይ በጣለው ጥቃት ቢያንስ 9 ሰዎች ተገድለዋል ።በሚያዚያ ደግሞ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ በፈነዳ ቦምብ የ5 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic