ጥቃትን በቴክዋንዶ መከላከል ይቻል ይሆን?  | ወጣቶች | DW | 01.06.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ጥቃትን በቴክዋንዶ መከላከል ይቻል ይሆን? 

 #77ከመቶው በተሰኘው የወጣቶች ዓለም መሰናዶ በጾታዊ ጥቃት ላይ እናተኩራለን። የጾታ ጥቃት በመኖሪያ ቤት በባልና ሚስት መካከል ብቻ የሚፈጸም አይደለም። ጉልበት የሌላቸው በተለይ ታዳጊ ልጃገረዶች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ጥቃቱ ሊደርስባቸው ይችላል። በኬንያ ተፈፅመዋል የተባሉ ጥቃቶች ባለሥልጣናት ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ እንዲጀምሩ አስገድዷቸዋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:16

በኬንያ ወጣቶች ራሳቸውን ለመከላከል ቴክዋንዶ እየሰለጠኑ ነው

በኬንያዋ የወደብ ከተማ ሞምባሳ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ነው። ዕድሜያቸው ከ8 እስከ 15 የሚደርስ ወደ 200 ገደማ ልጆች ሊኮኒ በተባለው አዳራሽ የቴክዋንዶ ሥልጠና ላይ ናቸው።  
መርኃ-ግብሩ በከተማዋ የተስፋፋውን የወሮበሎች ጥቃት፣ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት እንዲሁም ለከፋ እና ትንኮሳ ለመከላከል በወጣቶች የተጀመረ ነው። ሚርየም ሙቶኒ ሥልጠና ከጀመረች አራት አመታት አለፉ። ሊገጥማት ከሚችለው መሰል ጥቃት ራሷን ማዳን ቀዳሚ ዓላማዋ ነበር።

 
"ይኸን ሥልጠና የጀመርኩት በቡድን ሆነው ሊደፍሩኝ የሚሞክሩ ካሉ እንዴት ራሴን መከላከል እንዳለብኝ ለማወቅ ነው። መልሼ በመደባደብ ራሴን እጠብቃለሁ። ጥቃት ከተሰነዘረብኝ ራሴን ለመከላከል የተማርኳቸውን ክኅሎቶች መጠቀም ስለምችል በራሴ እተማመናለሁ።" 
በነጭ የስፖርት ልብስ ላይ ጥቁር ቀበቶ የታጠቀው ዳንኤል ኦዊኖ የአስራ አንድ አመት ታዳጊ ነው። ታዳጊው እንደ ሚርየም ሁሉ ቴክዋንዶ መሰልጠን ከጀመረ ሰነባበተ። ሥልጠናውን በመከታተሉ በራስ የመተማመን መንፈሱ ማደጉን ጤናውም መጠበቁን ይናገራል። 

"ቀድሞም ስፖርቱን እወደው ስለነበር ነው ሥልጠናውን ለመውሰድ የወሰንኩት። በሥነ-ሥርዓት የታነጽኩ እንድሆን ረድቶኛል። ሕመም የሚያጠቃው እና በተደጋጋሚ ራሴን የምስት አይነትም ነበርኩ። ነገር ግን የቴክዋንዶ ሥልጠና ከጀመርኩ በኋላ ሁሉም ነገር ተለውጧል። ጤናዬ ተሻሽሏል፤ በቴክዋንዶ የነበረኝ ደረጃም ከፍ ብሏል።"
ይኸ ሥልጠና ከስድስት አመታት በፊት ሲጀመር ተሳታፊዎቹ ወደ 50 ልጆች እና ክሪስፒን ምዋዲሜ ብቻ ነበሩ። ከሥልጠናው ጀማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ክሪስፒን እንደሚለው ይኸ ሥልጠና ልጆች በተለይ በገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ልጃገረዶች ጠንካራ ተክለ-ስብዕና እንዲገነቡ ያግዛቸዋል። 

«እኛ ሁሉም ሰው ቴክዋንዶን በመሳሰሉ የስፖርት አይነቶች እንዲሰለጥን እናበረታታለን። ጉዳዩ የሰውነት እንቅስቃሴ የማድረግ ብቻ አይደለም። ልጆች በራስ የመተማመን መንፈሳቸው ከፍ እንዲል ይረዳቸዋል፤ ተጨማሪ ክኅሎትም ይሰጣቸዋል።  አንዳንድ  ጊዜ ልጆቹን ከጥቃት የሚታደጋቸው ይኸ ነው። ልጆቹ አስቸጋሪ ከሆነ ሁኔታ እንዴት መሸሽ እንዳለባቸው እናሰለጥናቸዋለን። ሊጎዳቸው የሚችል ሰውን እንዴት ማጥቃት እንዳለባቸውም ይማራሉ።»

ማኅበሩ ሥልጠናውን ከ400 በላይ ለሚሆኑ ልጆች በመስጠት ላይ ይገኛል። ከ30 በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶችም የማስፋፊያ መርኃ-ግብሮች አሉት። ክሪስፒን እንደሚለው በርካታ ልጆች ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸው ስልጠና ካገኙ በኋላ ይፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶች ቁጥር ቀንሷል። የሞምባሳ ግዛት መሪዎች የሥልጠና መርኃ-ግብራቸውን በሁሉም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲያስፋፉ ጥያቄ አቅርበዋል። 

«በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና በውይይቶች የማርሻል አርትን ጠቀሜታ ለማኅበረሰቡ አስተምረናል። ማጄንጎ በተባለው አካባቢ አስከፊ ጥቃቶች በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸውን ተመልክተናል። ይኸ ሥልጠና በሁሉም ትምህርት ቤቶች መሰጠት ሲጀመር በአካባቢው የሚፈጸሙ ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ ይቆማሉ የሚል ተስፋ አለን።» 
ጃኔ ዋንጂኩ የሚርየም ሙቶኒ እናት ናቸው። ወደ ሊኮኒ አዳራሽ ብቅ ያሉት በሥልጠናው ጥሩ ብቃት ካላቸው መካከል አንዷ የሆነው ልጃቸው ያሳየችውን መሻሻል ለመታዘብ ነው። 


እናት በልጃቸው አካላዊ እንቅስቃሴ እና ታክቲኮች ተገርመዋል። ሚርየም በቤት አይን-አፋር እና ዝምተኛ እንደነበረች ያስታውሳሉ። አሁን እየወሰደች ያለው የቴክዋንዶ ሥልጠና ዛሬም ሆነ ወደፊት ደኅንነቷን ለመጠበቅ እንደሚጠቅማት እርግጠኛም ሆነዋል። 
«የቴክዋንዶ ሥልጠና በትምህርት ቤታቸው ሲጀመር ተመዘገበች። እንደ እናት ሁልጊዜ አብሪያት ልሆን ስለማልችል ስልጠናውን እንድትወስድ ፈቀድኩላት። አሁን የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነች። ከትምህርት ቤት የምትወጣው ከቀኑ ስምንት ሰዓት ነው። የሰለጠነችው ታክቲክ ሊጎዷት ከሚፈልጉ ሰዎች ራሷን ለመከላከል ይረዳታል። ለሰዎች ልጄ የማርሻል አርት እየሰለጠነች መሆኑን ስነግራቸው ማን ያገባታል ሲሉ ይጠይቁኛል። እኔም ይኸ ከማግባት እንደማያግዳት እነግራቸዋለሁ። ይኸ ከባሏ ጋር እንድትደባደብ የሚሰጥ ስልጠና አይደለም። ሁልጊዜም ለራሷ እንድትቆም፤ የትም ብትሆን ራሷን እንድታስከብር የሚረዳት ስልጠና ነው። ያንን ነው ለእርሷ የምፈልገው።»
ዲያና ዋንዮኒ/እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ 

Audios and videos on the topic