ጥረት በዱባይ ሲከፍል | ኤኮኖሚ | DW | 05.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ጥረት በዱባይ ሲከፍል

የተሻለ ሥራ እና ገቢ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምሥራቅ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚሰማባቸው በተደጋጋሚ ቢሰማም ጉዞው ግን ዛሬም አላባራም። ዱባይ እና አቡዳቢን በመሳሰሉ ከተሞች ኢትዮጵያውያኑ ቢፈተኑም ስኬታማ የሆኑም አልጠፉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:04

ጥረት በዱባይ ሲከፍል

ወ/ሮ ሳራ አራዲ ከ25 አመታት በፊት ወደ ዱባይ ሲያቀኑ በእጃቸው ያለው ገንዘብ ጥቂት ቢሆንም በልባቸው ትልቅ ሕልም ሰንቀው ነበር። እንደ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቤተሰባቸውን ሰርቶ ማገዝም ትከሻቸው ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነበር። «እኔ እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት አሊያም አፍሪቃዊት ሴት ራዕይ ነበረኝ። ካገሬ ወጥቼ ቤተሰቦቼን ለመርዳት እና ራሴን ለመቀየር አላማ ይዤ ነው የተነሳሁት።» ይላሉ ወይዘሮዋ ወደ ዱባይ ያቀኑበትን ጊዜ ሲያስታውሱ።

እንደ ወ/ሮ ሳራ አራዲ ሁሉ የተሻለ ሥራ እና ገቢ የሚሹ ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቶች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን መዳረሻቸው ካደረጉ አመታት ተቆጠሩ። የአለም የስራ ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፤ ባሕሬን፤ ኦማን እና ኳታር በመሳሰሉ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሥራ ላይ የተሰማሩ አብዛኞቹ ዜጎች ኢትዮጵያን ከመሰሉ አገራት የተጓዙ ናቸው።

ከአመታት መታተር በኋላ አል-ሐበሻ በሚል መጠሪያ ሥም የከፈቱት ምግብ ቤታቸው በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከተሞች ተስፋፍቷል። በሰራተኛ ፈቃድ እጦት ምክንያት የተወሰኑት ቢዘጉም የአል-ሐበሻ ምግብ ቤት ዘጠኝ ቅርንጫፎች ነበሩት። ወ/ራ ሳራ የተዘጉትን መልሰው ለመክፈት በዝግጅት ላይ ናቸው። «እዚህ የደረስኩት ባለቤቴን አገር ቤት ትቼ፤ልጆቼን በሞግዚት እያሳደኩ፤ሰውነቴን አበላሽቼ በቂ እንቅልፍ ሳልተኛ ነው።» ሲሉ ይናገራሉ።

ምግብ ማብሰል የሚወዱት ወ/ሮ የመጀመሪያ የንግድ ሥራቸውን እንዳሰቡት አልሰመረም። በኪራይ የጀመሩት የምግብ ቤት ቢከስርም እንቁላል፤ቅቤ እና ማር ከኢትዮጵያ እያጓዙ መነገድ ጀምረው ነበር። የመንቀሳቀሻ ገንዘባቸው ፈርጠም ሲል ግን ልባቸው ወደ ሸፈተበት የምግብ ማብሰል ተጀመለሱ። የአል-ሐበሻ ምግብ ቤት መጀመሪያ የተከፈተው በዱባይ ከተማ ናኢፍ በተሰኘ አካባቢ ነበር። አነስተኛው ምግብ ቤት በበረሐማዋ የዱባይ ከተማ የኢትዮጵያ ምግብ አዲስ ጣዕም በማስተዋወቁ ረገድ ስኬታማ ሆኗል። በዱባይ ከተማ የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች ከጥብስ፤ቀይ ወጥ እና ክትፎ የዘለለ የምግብ አይነት እንዳልነበራቸው የሚያስታውሱት ወ/ሮ ሳራ እርሳቸው ቁጥሩን ወደ 40 ከፍ እንዳደረጉት ይናገራሉ። «ስጀምር ብቻዬን ነኝ። ሰራተኛም አልነበረኝም። የታዘዝኩትን ምግብ በደንበኞቼ ቤት የማደርሰው እኔ ነኝ። ሥጋ ገዝቼ የምመጣው ራሴ ነኝ። አየር መንገድ እንጀራ የምቀበለው እኔ ነኝ።» ሲሉ ፈታኙን የሥራ ዘመን ያስታውሱታል። «እኔ ራሴ በጥንቃቄ በንፅህና ለራሴ የምበላውን ምግብ ነው የምሰራው።። የሚሉት ወ/ሮ ሳራ በርበሬ እና ቅቤ የመሳሰሉ የምግብ ግብዓቶችን ከኢትዮጵያ አንዴ እንደሚገዙም ተናግረዋል። ፊርጅ ሙራር በተሰኘ የዱባይ ከተማ ክፍል ሁለተኛው ምግብ ቤት ሲከፈት ወ/ሮ ሳራ ትርፋማ መሆን ጀምረው ነበር። የጅቡቲ፤ሶማሊያውያን፤ሱዳናውያን እና የአገሩ ዜጎች ምግቦቻቸውን እንደወደዱላቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ሳራ ከአሜሪካ እና አውሮጳ ወደ ዱባይ ብቅ ያሉ አገር ጎብኚዎችም ምግብ ቤቶቼን ያዘወትራሉ ብለዋል።

እንደ ዱባይ ሁሉ የመካከለኛ ምሥራቅ አገራት የተሻለ ሥራ እና ገቢ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን መዳረሻ ሆነዋል። የኢትዮጵያውያኑ የሥራ ሁኔታ እና አያያዝ ግን ሁሌም መልካም አይደለም። በአሰሪዎቻቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው፤ሞት እና የአካል ጉዳት የገጠማቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ወ/ሮ ሳራ ግን ዱባይን እንደሁለተኛ አገራቸው ይቆጥሯታል።

የአል-ሐበሻ ምግብ ቤት ከዱባይ በተጨማሪ በአቡዳቢ፤ሻርጃሕ፤አጅማን ከተሞች ጭምር ቅርንጫፎች አሉት። ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡትን ምግብ ጥራት ለመጠበቅ ለሰራተኞቻቸው ስልጠና እንደሚሰጡ የሚናገሩት ወ/ሮ ሳራ ጥብቅ አስተዳደር ለስኬታቸው መሰረት እንደሆነ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ሳራ እና ባለቤታቸው ከአመታት በፊት መሐል አዲስ አበባ ፒያሳ ላይ ፊልም የሚያከፋፍሉበት ሱቅ ነበራቸው። በአንድ ወቅት ተወዳጅ የነበሩትን የሕንድ ፊልሞች ያከፋፍሉም ነበር። ሚሊዮነር ስለመሆናቸው ስጠይቃቸው ፈገግ የሚሉት ወ/ሮ ሳራ አዲስ አበባ ላይ ፎቆች እየገነቡም ነው።

ወ/ሮ ሳራ አራዲ ዛሬ ከደረሱበት ስኬታማነት ጀርባ ልፋታቸው እና የከፈሉት ዋጋ እንዳለ አይዘነጉም። በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ስኬታማ ለመሆን ግልጽ አላማ እና ገንዘብን በጥንቃቄ ማስተዳደር ያሻል ባይ ናቸው።

እሸቴ በቀለ

 አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic