ጤና አዋኪዋ ትንሽ ፍጥረት በወሎ | ጤና እና አካባቢ | DW | 22.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ጤና አዋኪዋ ትንሽ ፍጥረት በወሎ

ወሎን አንዲት ትንሽ ፍጥረት እየረበሸች ነው።  ከወራት በፊት ይኸው ጥቆማ ከደቡብ ወሎ ደርሶን መረጃ አለን የሚሉንን ለማነጋገር ሞክረን ነበር። በወቅቱም ጉዳዩ እየተጠና መሆኑ ተገልጾልን ተጨማሪ ጥቆማ ስላልመጣ ችግሩ የተወገደ መስሎን አልተመለስንበትም ነበር። ሆኖም አሁንም ከወደ ሰሜን ወሎ ተመሳሳይ ጥቆማ ለዝግጅት ክፍላችን ደረሰ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:20

አሁንም መፍትሄ አልተገኘላትም?

የሰሜን ወሎ ሐብሩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አድማጭ እሳቸውም የዚችው አነስተኛ ፍጥረት ሰለባ እንደሆኑ እና በቅርቡም በባህላዊ ዘዴ ወደሚያወጧት የአካባቢዉ ሰው ዘንድ ሄደው ትንሿ ጥንዚዛ ያሏት ፍጥረት እንደወጣችላቸው ይናገራሉ። ሕክምናውን ያገኙት በባህላዊ መንገድ ነው። መድኃኒት አዋቂው ቅጠል ጨምቀው ይህች ፍጥረት በገባችበት በኩል ወደሰዉነት ይከታሉ፤ ከዚያም ትወጣለች ይላሉ ይህ ሲደረግ የተመለከቱ ወገኖች።

የሐብሩ ወረዳ ነዋሪዉ እንደሚሉት ትንኝ ሆና ወደሰውነት የምትገባው ፍጥረት ስትወጣ ትንሽ ጥንዚዛ ናት። ፎቶዋ ነው ያሉትንም ልከውልናል። (የፎቶውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ባለመቻላችን ከመጠቀም መቆጠብን መርጠናል።) በነገራችን ላይ እንዲህ አይነቱን አገላለጽ የዛሬ ሁለት ዓመት ባቀረብነው መሰናዶ ከደቡብ ወሎ ነዋሪዎችም ሰምተነው እንዳካፈልናችሁ ይታወስ ይሆናል። የዚች ትንኝ ትሁን ጥንዚዛ በማኅበረሰቡ ያልታወቀች አነስተኛ ፍጥረት ምንነት እስከዛሬ ተደርሶባት እንደሁ ለማጣራት ወደሚመለከተው የክልሉ መሥሪያ ቤት ደወልን። በሰሜን ወሎ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል ባለሙያ አቶ አበበ ሲሳይ ችግሩ እንግዳ እንዳልሆነ ነገሩን።

« እሷ ነገር የቆየች ናት ከእኛ 2008ዓ,ም እንደዚሁ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ከአዲስ አበባም ፤ ከሌላም መጥተው ጉዳዩን ለማየት ሞክረን ነበር። እና ብዙ ተጨባጭ ነገር ያለው የለም። እነሱ ያው እየተጠቀሙ ያሉት ትራዲሽናል የአካባቢ ሰዎች በቅጠል አድርገው የሚጠቀሙ ሰዎች ናቸው እና፤ በእኛ ተብሎ የነበረው ምንድነው። ወደሆስፒታል መጥተው ጎረሯቸውን በደንም ፈልፍሎ በመሳሪያ እንዲታዩ ወጪያቸውም እንዲሸፈን ነበር። ሰዎች ግን መምጣት አልቻሉም ወደ ሆስፒታሉ።»

አቶ አበበ እንደሚሉት የዚህች አዋኪ ፍጥረት ምንነትም በወቅቱ ጥናት ተደርጎበት ውጤቱ ተልኮላቸዋል። እናም በእርግጥም የጥንዚዛ ዘር ናት።

የዚህች የጥንዚዛ ዘር ሰለባ ነኝ የሚሉት የሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳው አድማጫችን በዚህች ፍጥረት ምክንያት የሰው ሕይወት ጠፍቷል ይላሉ። አቶ አበበ ጤናን ማወካ ባይቀርም አትገድልም ነው የሚሉት።

 «በፊት በርከት ያሉ ሰዎች እንደዚሁ ያመናል ብለው አይተናቸው ነበር። ለሞት ለምናምን የሚዳርግ ነገር የለውም። ችግሩ ምንድነው ያው ጉረሮ አካባቢ ላይ የመቁሰል አይነት ነገር እንጂ ያን ያህል የከፋ ነገር የለም። አሁንም ያው ጉዳዩ እንትን እያለ ስለሆነ አልተከታተልነውም ከዚያ ወዲህ። ምክንያቱም ከእኛም ዉጪ ስለሆነ ሌሎችም አካላቶች እንዲያግዙን አድርገን ነበር የተለየ ነገር የለም።  ስለዚህ ከእኛ አቅም ውጪ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ በዚህ ላይ ነው ያለው ነገሩ።»

ተመሳሳይ ችግር የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ያጋጠበመው ደቡብ ወሎ አካባቢ ነበር። ያኔ ይህንኑ ጉዳይ አንስተን ያነጋገርናቸው የደቡብ ወሎ ጤና መምሪያ ባለስልጣን ከሕዝብ የተገኘውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ ጥናት እየተደረገ እንደነበር በወቅቱ ገልጸውልን ነበር። በድጋሚ ትናንት ስደውልላቸው ታዲያ የዚች ትንሽዬ ጥንዚዛ ነገር ችግር መሆኑ በአካባቢያቸው እንደተወገደ ገለጹልን። የተለያዩ የጤና እና የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳይ ባለሙያዎች ከኅብረተሰቡ ጋር በችግሩ ምንነት እና መፍትሄ  ላይ ተወያይተዋል። የዘመናዊ ሕክምና መፍትሄ እንዳለውም ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ተደርጓል ባይ ናቸው።

« እዚያ አካባቢ ላይ ማኅበረሰቡ የሚያነሳው ነገር የለም። እኛም ያው ክሪቲካሊ ለስድስት ወር ተከታታይ በሕክምና ቡድኑ ባቋቋምነው ክትትል ሲደረግበት ነበረ። ከዚያ በቃ ችግሩ መፍትሄ ያገኘበት አግባብ ነው ያለው።»

ደቡብ ወሎ እንዲህ ከዚች አነስተኛ ጥንዚዛ ችግር ሲገላገል ሰሜን ወሎ ቀድሞ ችግሩ መኖሩን ቢያውቅም እስካሁን መፍትሄ  አልተገኘም። የደቡብ ወሎው ተሞክሮ ለሰሜኑም አዎንታዊ ውጤት ለማስገኘት ይረዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የሀብሩ ወረዳው ነዋሪ አድማጫችንም የጥንዚዛዋ ችግር በህክምና መፍትሄ እንዳለው አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ የደቡብ ወሎ ጤና መምሪያ ኃላፊ የሰጡትን ማብራሪያ ልብ ይበሉት። በዚህ አጋጣሚ ግን ጥናት አካሂደዋል የተባሉ አካላትን ለጊዜው ለማግኘት ባለመቻላችን ለዛሬ ከእነሱ ወገን ያለውን ማብራሪያ ማካተት አልቻልንም። እንዳገኘን በድጋሚ ለእናንተ እናደርሳለን።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

 

Audios and videos on the topic