ጤናና ተፈጥሮ በ2014 | ጤና እና አካባቢ | DW | 30.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ጤናና ተፈጥሮ በ2014

አምና ሊባል አንድ ቀን የቀረዉ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2014ዓ,ም በጤናዉ ረገድ ዓለም ያደናገጡ በሽታዎች የተከሰቱበት ነበር። በዚህ ዓመት ከታዩት በሽታዎች ሳርስ፣ ማርቡርግ እና የወፍ ጉንፋን በየተቀሰቀሱበት አካባቢ ሲወሰኑ፤ ኤቦላ ግን መነሻዉ ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ቢሆንም የተሐዋሲዉ ስርጭት በርካታ ቦታዎችን ነካክቷል።

2014 አዲስ ዓመት ተብሎ ብዙም ሳይሰነብት ነዉ በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጊኒ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ የገጠር መንደሮች ኃይለኛ ትኩሳት የሚያስከትለዉ ኤቦላ መዛመት የጀመረዉ። በሶስት የገጠር መንደሮች መሠራጨት የጀመረዉ የኤቦላ ተሐዋሲ በወቅቱ በአጭር ጊዜ ወደሌሎች ሃገራት ይዛመታል ብሎ የገመተ ባይኖርም ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን በቦታዎቹ ታማሚዎች ተነጥለዉ የህክምና ክትትል የሚያከኙባቸዉ ስፍራዎች ገንብቶ ነበር። ጊኒ ዉስጥ ከሃያ የሚበልጡ የቡድኑ ሃኪሞች ቢኖሩን የህክምና ቁሳቁሶችና መድሃኒት እንዲም ተጨማሪ የሰዉ ኃይል መጋቢት ወር ዉስጥ ወደስፍራዉ መላኩን ቡድኑ አሳዉቆም ነበር። በወቅቱም የመድሃኒት ተስፋ እንደሌለ የተረዳዉ የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ኅብረተሰቡ የግልና የአካባቢዉን ንፅሕና እንዲጠብቅና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ አስተላልፎ ነበር።

ኤቦላን ግን እንደሰደድ እሳት ከመንደር መንደር ከሀገር ሀገር መዛመቱን የገታዉ አልታየም። በሽታዉ ዋል አደር ብሎ ወደጎረቤት ላይቤሪያ ብሎም ሴራሊዮን ገባ። ችግሩን በእነዚህ ሃገራት ይበልጥ ካባባሱት ምክንያቶች በዋነኛነት የሚጠቀሰዉ የሕክምና መስጫ ተቋማት አለመስፋፋት መሆኑ ተነግሯል።

Guinea-Bissau Ebola Vorsichtsmaßnahmen Isolationszelt 10/2014

ጊኒ ዉስጥ በኤቦላ የተያዙ ሰዎች ተገልለዉ የሚቆዩበት ሥፍራ

ኤቦላ በተስፋፋባቸዉ አካባቢዎች በበሽታዉ ሰዎች እንደቅጠል በሚረግፉበት ጊዜ ስለወረርሽኙ ለጤና ባለሙያዎች ያለማሳወቁ ሁኔታም ሌላዉ ዋና ተጨማሪ ምክንያት መሆኑ ነዉ በዓለም የጤና ድርጅት ባለሙያዎች ሲነገር የቆየዉ። ኤቦላ በእነዚህ ሶስት ሃገራት የመስፋፋት ይዞታዉና ያደረሰዉ የጉዳት መጠን ከፍተኛ ይሁን እንጂ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል እንዲሁም ማሊ ላይ በበሽታዉ የተያዙ ሰዎች ነበሩ። ወረርሽኙ ያስከተለዉ ጉዳት ዓለም የግድ ትኩረት እንዲሰጠዉ በማድረጉ ይመስላል በተጠቀሱት ሃገራት የተወሰዱ ፈጣን የቁጥጥር ርምጃዎች ምናልባት ከመዛመት የገቱት ይመስላል። በበሽታዉ መያዛቸዉ የተጠረጠረ ሰዎች በተየያዩ ሃገራት ለጊዜዉ ተገልለዉ እንዲቆዩ ተደርጓል አሁን ይህ ተግባር ቀጥሏል። አንድ ሰዉ በበሽታዉ ከተያዘ ከስምንት እስከአስር ቀናት ዉስጥ የበሽታዉ ምልክቶች ሊታዩበት ይችላሉ። ተሐዋሲዉ በሰዉነት ገብቶ ጥቃት ለመሰንዘር እስኪጠናከር ደግሞ እስከ21 ቀናት ሊቆይ እንደሚችል ተደጋግሞ ተገልጿል።

በሽታዉ መከላከያም ሆነ ማዳኛ መድሃኒት ስለሌለዉ ታማሚዎችን ለመርዳት የተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸዉን መከላከል የሚችሉበት ብቸኛዉ መንገድ በኤቦላ ከተያዘዉ ግለሰብ ሰዉነት የሚወጡ ማናቸዉም ፈሳሾች እንዳይነኳቸዉ ከላይ እስከታችን ጭንብል ማድረግ ነዉ። እንዲያም ሆኖ ግን ከአራት መቶ በላይ የሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ሌሎችን በመርዳት ሂደት በተሐዋሲዉ መያዛቸዉና ከሁለት መቶ የሚበልጡት ደግሞ ህይወታቸዉን ማጣታቸዉ በጥቅምት ወር ላይ ተሰምቷል። እስካሁንም የሟቾቹም ሆነ በኤቦላ የተያዙት ሃኪሞች ቁጥር ሊጨምር ይችላል።

የኤቦላ ታማሚዎችን በሙያቸዉ ሲረዱ ወረርሽኙ የተቀሰቀሰባቸዉ ሃገራትና የሌሎች ሃገራት ዜጎችን ጨምሮ በተሐዋሲዉ የስፔን፣ የአሜሪካ፣ የኖርዌይ፣ የፈረንሳይና የብሪታንያ ዜጎች ተይዘዋል። ወደሀገራቸዉ ተወስደዉ ህክምና የተደረገላቸዉ አብዛኞቹ የምዕራብ ሃገራት ዜጎች ከቀናት በኋላ ከበሽታዉ አገግመዋል። በእርዳታ ተግባር ተሰማርተዉ በኤቦላ ተሐዋሲ የተያዙ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ሠራተኞችም ዩናይትድ ስቴትስ፣ ስፔን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ፣ ጣሊያን፣ ስዊዘርላንድና ብሪታንያ ዉስጥ ታክመዋል። ለሙከራ የተዘጋጁ መድሃኒቶች የብዙዎቹን ነፍስ መታደጋቸዉ ነዉ የተነገረዉ።

የህክምና ባለሙያዎች የሚሉት ደግሞ በኤቦላ የተያዘ ሰዉ የመዳን ተስፋ በሰዉነቱ ዉስጥ ባለዉ በሽታን የመቋቋም የተፈጥሮ አቅም ይወሰናል ነዉ። አንዴ በተሐዋሲዉ ተይዞ መዳን የቻለ ደግሞ ቢያንስ እስከ አስር ዓመታት ሊቆይ የሚችል በሽታን የመከላከል አቅም የመገንባት እድል አለዉ።

ኤቦላ አሁን ድንገት የታየ በሽታ አይደለም 30ዓመታትን አስቆጥሯል። እስካሁን ይህነዉ የሚባል መድሃኒት ያልተገኘለት ምናልባት የቀድሞዉ የተመድ ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን የድሃ በሽታ እንዳሉት ሆኖ ይሆን ያስብላል። የዓለም የጤና ድርጅት በኤቦላ ከተያዙ 90 በመቶዉ እንደማይተርፉ ነዉ ቀደም ሲል የገለፀዉ። በሽታዉ ጊኒ ዉስጥ እንደተቀሰቀሰ በስፍራዉ ተሰማርተዉ ከነበሩት የድንበር የለሽ ሃኪሞች ባልደረባ አንዱ ሚሸል ፋንኸርፕ ይህንኑ አረጋግጠዉ ነበር።

ዓመቱ ከማለቁ አስቀድሞ ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች በኤቦላ ተሐዋሲ ከ20 ሺ የሚልቁ ሰዎች መያዛቸዉን እና የሟቾቹም ቁጥር ሰባት ሺህ ስምንት መቶ መድረሱን ያመለክታሉ። ዓመቱ እንደባተ በወረርሽኝ መልክ ተቀስቅሶ እስካሁንም ስለኤቦላ መነገሩ፤ እሱም ነፍስ መቅጠፍ መበከሉ አላባራም። ምናልባትም ለ2015 ሊያወርሰዉ ይችላል።

ከዚህ ሌላ የጤና ጉዳይ ደግሞ በኩፍኝ ምክንያት በመላዉ ዓለም የሚሞቱ ሕፃናት ቁጥር ከዓመታት በኋላ ዳግም ጨምሮ የተገኘዉ ክትባት በአግባቡ ባለመዳረሱ እንደሆነ የተነገረዉ በ2014ዓ,ም መገባደጃ ወራት ዉስጥ ነዉ። ኩፍን በየዕለቱ የአራት መቶ በሰዓት ደግሞ የ16 ሕፃናትን ነፍስ እንደሚቀጥፍ የዓለም የጤና ድርጅት ይገልጻል። በኩፍኝ ምክንያትም በርካታ የሕጻናት ነፍስ የሚያልፍባቸዉ ሃገራት ናይጀሪያ፣ ፓኪስታን፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ መሆናቸዉም ተነግሯል።

2014ዓ,ም በብዛት ስለኤቦላ መዛመትና ጉዳት ቢነገርበትም የመሬት መንጥቀጥ፣ እና መናድ እንዲሁም ጎርፍና እና ወጀብ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ማድረሳቸዉ አይዘነጋም። አፍጋኒስታን ዉስጥ ሁለት ጊዜ የደረሰዉና የመሬት መናድ በሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ሕይወት የጠፈዉን የተፈጥሮ አደጋ እናስታዉሳለን። ደቡብ ምዕራብ ቻይና ዉስጥ ደግሞ በሬሽተር መለኪያ 6,5 የተመዘገበዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ከስድስት መቶ ሰዎች በላይ ሞተዉበታል።

ሕንድን ጎርፍ ጉዳት አድርሶባታል፣ ፊሊፒንስ እንዳለፈዉ ዓመቱ ሃያን ማዕበል ሳይሆን ዘንድሮ ሀጉፒን የተሰኘዉ ዉሽንፍር ቀድማ በመዘጋጀቷን የማዕበሉም ኃይል ደከም ያለ ስለነበረ በመጠነኛ ጉዳት አልፏታል። እንዲያም ሆኖ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከመኖሪያ ቀየዉ ለመፈናቀል ተገዷል። ዛሬም በጎርፍና እሱ ባስከተለዉ የመሬት መናድ ቢያንስ የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰምቷል። ኔፓልን ደግሞ ገና በጥቅምት ወር መባቻ ነዉ ኃይለኛ የበረዶ ዉሽንፍር የገረፋት። በከተራራዎች አካባቢ ተራራ ወጪ ቱሪስቶች ላይ የወረደዉ የበረዶ ክምርም በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል ቢያንስ የ43ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

በዚህ ዓመት ከሌሎቹ በተለየ ከባቢ አየርን በመበከል ከሚወቀሱ ግንባር ቀደም ሃገራት ሁለቱ ማለትም ቻይናና ዩናይትድ ስቴትስ ከየኢንዱስትሪዎቻቸዉ ወደአየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን እንደሚቀንሱ ፍንጭ መስጠታቸዉ አንድ ነገር ነዉ ተብሏል። ፔሩ ያስተናገደችዉ 20ኛዉ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤም ይህንን ሰናይ ወሬ ይዞ ነዉ በተነቃቃ ስሜት የተጀመረዉ። እንዲያም ሆኖ ዋሽንግተንም ሆነች ቤጂንግ እንቀንሳለን ያሉትን አዲሱን መጠን ሥራ ላይ የሚያዉሉት በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር 2025 ላይ ነዉ ማለታቸዉ ይፋ ያደረጉት ዉሳኔ ከተግባራዊነቱ ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳዉ እንደሚልቅ ነዉ ተቺዎች የተናገሩት። ትችቱ እንዳለ ሆኖ ግን ከሕዳር መገባደጃ ጀምሮ ሊማ ፔሩ ላይ ለሁለት ሳምንት የተካሄደዉ የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤም የባከ ጊዜ የሚባል እንዳልሆነ ነዉ የተነገረለት። ጉባኤ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሁለት ቀን ተራዝሞ ሲያበቃም ለአየር ንብረት ለዉጥ አንዳች መፍትሄ መፈለግ እንዳለበት የሚወተዉቱ ወገኖች ባዶ እጃቸዉን ወደየመጡበት አልተመለሱም። በችኮላም ቢሆን ተሰብሳቢዎቹ በመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ፓሪስ ላይ በሚካሄደዉ ጉባኤ ለድርድር ሊቀርብ የሚችል መንደርደሪያ ሃሳብ ያካተተ ዶሴ አሰናድተዋል።

በዚህ መሠረትም ሃገራት በየበኩላቸዉ ሊያደርጉ ያቀዱትን እስከከ መጋቢት አጋማሽ እስከ ሰኔ ወር እኩሌታ ድረስ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ የበለፀጉት ሃገራት እንደዋና ጉዳይ ያዩት ከባቢ አየርን የሚበክለዉን የአደገኛ ጋዝ የልቀት መጠን የመቀነስን ርምጃ ነዉ። በአየር ንብረት ለዉጥ ላስከተለዉና ለሚያስከትለዉ መዘዝ የተጋለጡ ሆኖም በብከላም እጅግም አስተዋፅኦ የሌላቸዉ አዳጊ ሃገራት ደግሞ በዚህ መዘዝ ለተጎዱ ሃገራት ከለዉጡ ጋ ተላምደዉ እንዲኖሩ ከባለ ኢንዱስትሪዎቹ ሊደረግ የሚገባዉ የገንዘብ ድጎማ ነዉ። ከዚህ በፊት ቃል የተገባዉ በየዓመቱ የአንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር ድጎማ ከአምስት ዓመታት በኋላ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ነዉ የሚነገረዉ። የሊማዉ ጉባኤ በተስፋ ታጅቦ እንደተጀመረ በመልካም ዜና ተጠናቀቀ ቢባልም ተሰብሳቢዎቹን ሁሉ እኩል አላረካም። የኦክስፋም ባልደረባ ያን ኮቫልሲክ ደካማ ሰነድ ብሎታል።

ተመርቆም ተተችቶም 2014 ተግባሩን በዚህ ረገድ አጠናቀቀ። 2015 ምን ደግሶ እንደሁ ሲገባበት የሚታይ ይሆናል። የእኛን አዲስ ዓመት ከአራት ወራት በፊት እንደተቀበልን በጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከሚቀምሩት ጋም ከነገ በስተያ አንድ እንለዋለን። የዚያ ሰዉ ይበለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic