ጣና ሐይቅን የወረረዉ መጤ አረም | ጤና እና አካባቢ | DW | 04.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ጣና ሐይቅን የወረረዉ መጤ አረም

እንግዳ ክስተቶች የዓለማችን ስነምህዳር ያስተናግዳል። ቀደም ሲል በዩጋንዳ ቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ እንዲሁም በግብፁ የአስዋን ግድብ ዉስጥም እንዲሁ የዉኃ ላይ አረም ተከስቶ ሃገራቱን አስጨንቆ ያዉቃል። ካለፉት አምስት እና አራት ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በጣና ሐይቅ ላይ የዉኃ አረም መስፋፋት መጀመሩ አሳሳቢ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:12

አፋጣኝ ርምጃ ካልተወሰደ የጣና ሐይቅን ሊያደቀዉ ይችላል

በአባይ ምንጭነቱ ይታወቃል። ከ20 በላይ ደሴቶችን እና ገዳማትን አቅፏል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ካሉት ሐይቆች ትልቁ፤ ከአፍሪቃ ደግሞ በስፋቱ ሦስተኛዉ መሆኑ ይነገርለታል። ጣና ሐይቅ፤ የአባይ መገኛ ብቻ ሳይሆን መጓጓዣም ሆኖ ያስተናግደዋል። ካለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ታላቅ ሐይቅ ተወሯል፤ በዉስጡ የሚያስተናግደዉ ብዝሐ ሕይወትም እንግዳ ክስተት አደናግሮታል። በአማራ ክልል የሚገኘዉ ጣና ሐይቅ ከላይ ሲያዩት ዉበት መስሎ በሌሎች ሃገራት እንደለመደዉ ሊያደርቀዉ በሚመስል ርምጃ ዉኃዉን አረም ወርሶታል። እንዴት ወደ ሀገር እንደገባ የተለያዩ መላ ምቶች የሚቀርቡበት እምቦጭ የሚል መጠሪያ የተሰጠዉ መጤ የዉኃ አረም በለመደ እግሩ ወደ ሕዳሴዉ ግድብ እንዳይሄድ ስጋት አለ። ምሁራን መፍትሄ ለመፈለግ ምርምርና ጥናት ከጀመሩ መሰንበታቸዉን ይናገራሉ።

በብዝሃ ሕይወት ሀብቱ ስብጥር በዩኒስኮ የተመዘገበዉ የጣና ሐይቅ በዉስጡ ከ67 ያላነሱ የዓሣ ዝርያዎች ይርመሰመሱበታል። ከዓሣዎቹ ሌላ በላዩ የሚንፈላሰሱት አዕዋፍ፣ በዉስጡ የሚንቦራጨቁት ጉማሬዎች የሐይቁ ድንቅ ዉበቶች ናቸዉ። በጣና ሐይቅ ላይ ለመንሳፈፍ የሚረዱት ደንገሎችን ለመሥራት ከሐይቁ ዳር ዳር የሚበቅሉት ሰንበሌጦች ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ የሐይቁም ማስጌጫዎች ናቸዉ።

Wasserhyazinthen Lake Tana Äthiopien

አረሙ ያረፈበት ስፍራ ዉኃዉ ይደርቅ ጀምሯል፤

አረሙ በአካባቢዉ እምቦጭ የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። የመንሰራፋት ዕድል ያገኘዉ እምቦጭ ወትሮ የነበሩ ሁሉ በቀጣይ በሐይቁ ላይ እንዳይገኙ የቆረጠ አስመስሎታል። ሐይቁም ዕድሜ ካገኘ ማለት ነዉ። ዶክተር ዉብዓለም ታደሰ የኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር እንደሚሉት መጤዉ የዉኃ አረም የሐይቁን 50 ሺ ሄክታር የሚሆን አካባቢ በአሁኑ ሰዓት ሸፍኗል። ከዚህ በፊትም በተለያዩ የሀገሪቱ የዉኃ አካላት ማለትም በአዋሽ ወንዝ እና በዝዋይ ሐይቅን በመሳሰሉት ላይ መታየቱንም ጠቁመዋል። እንደእሳቸዉ አገላለጽም እምቦጭ የተባለዉ የዉኃ አረም ጣና ላይ ጠንቷል። በዚህም ምክንያት በአማራ ክልል የሚገኙ የሰባት ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ሐይቁን ከወረረዉ አረም ለማላቀቅ የየበኩላቸዉን ምርምር በማካሄድ ላይ ናቸዉ። የኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ተቋም እና ሌሎች ድርጅቶችም በምርምር ተጠምደዋል። ከሳምንታት በፊት በሰኔ ወር መባቻ ባሉት ቀናት ምርምሮቹን አሰባስቦ የመከረ ጉባኤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተናግዷል።

እምቦጭ የተባለዉ የዉኃ አረም በጣና ሐይቅ ላይ አሁን የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ አምስት ዓመታት ወስዷል። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ምን እየተደረገ ነበር? በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ሳሕሌ በዩኒቨርሲቲዉ በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ መምህር እና ተመራማሪ ናቸዉ። ዩኒቨርሲቲዉ የአካባቢዉን ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ ለማሳወቅ ብዙ እንደሠራ እና ከዚያም አረሙን ለመቀነስ በእጅ ሲነቀል መክረሙን ይዘረዝራሉ።

ይህ የዉኃ አረም ጣና ሐይቅን ብቻ አይደለም የደፈረዉ። ዩጋንዳ ዉስጥ የሚገኘዉን የአፍሪቃን ትልቅ ሐይቅ ቪክቶሪያንም አስቸግሮ ነበር። ግብጽም በአባይ ዉኃ በሚሞላዉ አስዋን ግድብም ላይ እንዲሁ። በእነዚህ ሃገራት የተወሰዱ የመከላከል ርምጃዎች ለኢትዮጵያዉ ደልቃቃ ሐይቅ ጣናም እንዲዉሉ ተሞክሮዎች ተቀስመዋል።

ዶክተር ሳሙኤል እንደሚሉት ይህ የዉኃ አረም ዘር በመሬት ዉስጥ ከ15 እስከ 20 ዓመት መኖር ይችላል። በዚህም ምክንያት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አዳጋች ነዉ። ይህን አሳሳቢ የዉኃ አረም በጣና ሐይቅ ላይ ይበልጥ እንዳይስፋፋም ሆነ ወደሌሎች እንዳይዛመት መፍትሄ ይሆናል ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎቹ እና የተለያዩ ተቋማት የምርምራቸዉን ዉጤት አቅርበዋል። በዚህም መሠረት ከኬሚካሎች አንስቶ፤ ጥንዚዛዎችን መጠቀም፤ የዉኃዉን አረም እያጨደ የሚፈጭ ማሽን እና ሌሎችም ሃሳቦች ምርምሮች ቀርበዋል።

Wasserhyazinthen Lake Tana Äthiopien

ለምርምር የተዘጋጀዉ የእምቦች ዘር

አንዳንዶቹ አድረዉ ሌላ ስጋት እንዳይሆኑ አስቀድሞዉ የሚደረግ ጥንቃቄ ታስቦ እንደሁ ያነሳንላቸዉ ዶክተር ዉብዓለም ሁሉም ትኩረት እንደሚደረግበት ነዉ የገለፁልን። ጣናን የወረረዉ የዉኃ አረም ከወዲሁ ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀለት የሐይቁ ዉኃ ወደሚጓዝባቸዉ ሌሎች አካባቢዎችም መዳረሱ እንደማይቀር ባለሙያዎቹ እያሳሰቡ ነዉ።

ጣና ሐይቅን ለመታደግ ምሁራን ከሚያደርጉት ምርምር እና ጥረት ጎን ለጎን የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ለመረዳት ችለናል። ዶክተር መሐሪ አለባቸዉ የሥርዓተ ምህዳር አያያዝ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የዉኃ እና ዉኃ አዘል መሬቶች ሥርዓተ ምህዳር ዘርፍም በእዚህ በእምቦቻ አረም ላይ የሚከናወኑትን እንቅስቃሴዎች አስተባባሪ  እንገለጹልን ባህር ዳር ከነማ እና ፋሲል ከነማ የእግርኳ ስ ጨዋታ ሲያካሂዱ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ተካሂዷል። በተጨማሪም በአማራ ክልል በትምህርት ቤቶች ለዚሁ የሚሆኑ ጥሩ ጅምሮች እንዳሉም አስረድተዋል። ማብራሪያ ለመስጠት የተባበሩንን ሁሉ እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic