ታጣቂዎች የሰገን ከተማን ለቀው ወጡ ፤ በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ውድመት ደረሰ
ዓርብ፣ ነሐሴ 17 2016
የሰገን ከተማ ከታጣቂዎቹ መውጣት በኋላ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ የአስተዳደር መቀመጫ የሆነውን የሰገን ከተማን ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ተቆጣጥረው የነበሩ ታጣቂዎች አካባቢውን ለቀው መውጣቸው ተነግሯል ፡፡ ታጣቂዎቹ ትናንት ከተማውን ለቀው የወጡት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ከተማው መግባቱን ተከትሎ መሆኑን አንድ የከተማው ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡
ከቀናት ቆይታ በኋላ ትናንት የመከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማው ሲገባ መመልከታቸውን የጠቀሱት ነዋሪው “ በከተማው ሠራዊቱ ሲገባ ታጣቂዎቹ አስቀድመው አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል ፡፡ አሁን ሠራዊቱ በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ አንጻራዊ መረጋጋት እየመጣ ነው ፡፡ በድንጋጤ ከከተማው የሸሹና የተደበቁ ነዋሪዎችም እየወጡ ነው ፡፡ ይህ ምን ያህል ዘላቂ ይሆናል የሚል ሥጋት አለብን “ ብለዋል ፡፡
የታጠቁ ኃይሎች የሰገን ከተማን መቆጣጠራቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገለፁ
የወደሙት የመንግሥት መሥሪያቤቶች
ታጣቂ ሀይሉ በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ መዋቅርን በኃይል ለመናድ ሞክሮ አልተሳካለትም ያለው የኮንሶ ዞን መስተዳድር በበኩሉ በ8 ፖሊስ አባላትና 5 ሲቪል ነዋሪዎች ላይ የግድያ ተግባር መፈጸሙን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም በ23 የመንግሥት መሥሪያቤቶች ላይ ሠፊ የንብረት ዝርፊያና ውድመት በመፈጸም ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ ዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡
ኮንሶ፣የድርቅ መዘዝ
ከመሆኑ በፊት
የሰገን ዙሪያ ወረዳ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት መሆኑን የጠቀሱት አንድ የአካባቢው ተወላጅ “ የዞኑም ሆነ የክልሉ አስተዳደር የከተማውን ህዝብ ደህንነት ለመጠበቅ ትኩረት አልሰጠም “ በማለት ወቅሰዋል ፡፡ ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ ይቻል ነበር ያሉን ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላው የሰገን ከተማ ነዋሪ “ የሽብር ቡድኑ ከተማውን ተቆጣጥሮ የሚፈልገውን ሲገድል ፤ የመንግስት መሥሪያቤቶችን ሲዘርፍና ሲያቃጥል ነበር ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘውና አዲስ ገበሬ በተባለው ቦታ የፀጥታ ሠራዊት አባላት ነበሩ ፡፡ ለመከላከልም ሆነ ተጨማሪ ሀይል እንዲመጣላቸው ጥረት ሲያደርጉ አላየንም ፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች አሁንም ነገ ተመልሰው ሥለመምጣታቸው ዋስትና የለንም “ ብለዋል ፡፡
መፍትሄ ያጡት የኮንሶና አካባቢው ተፈናቃዮች
አካባቢው የፀጥታ ችግር እንዳለበት እየታወቀ ትኩረት አልተሰጠውም በሚለው ቅሬታ ላይ ዶቼ ቬለ የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባን ጠይቋል ፡፡ ጥቃቱ በወረዳው እንዴት ሊከሰት እንደቻለና በታጣቂው ላይ እየተወሰደ በሚገኘው እርምጃ ላይ በቀጣይ በጸጥታ ሃላፊዎች ዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጥ ይሆናል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር