ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በምክር ቤት የሰጡት ማብራርያ   | ኢትዮጵያ | DW | 22.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በምክር ቤት የሰጡት ማብራርያ  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል በዚህ ዓመት ስለሚካሄደው ምርጫ፣ ስለ ግጭት፣ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ እና የውጭ ዜግነት ስላላቸው የሚዲያ ባለቤቶች ያደረጓቸው ገላጻዎች ይገኙበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:22

"የኢትዮጵያን ከህዳሴ ግድብ ግንባት ማንም አያስቆማትም"

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል በዚህ ዓመት ስለሚካሄደው ምርጫ፣ ስለ ግጭት፣ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ እና የውጭ ዜግነት ስላላቸው የሚዲያ ባለቤቶች ያደረጓቸው ገላጻዎች ይገኙበታል። የኢፊድሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ለህዝብ ተወካዮች እና ለፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ስላደረጉት የመክፈቻ ንግግር የመንግሥትን አቋም ያዳመጠው ምክር ቤቱም ንግግሩን የደገፈበትን የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ተቃውሞ እና በ19 ድምጸ ተአቅቦ አጽድቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ አንዱ ነው። ምርጫው በተለያየ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ይገፋ መባሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው «አሳማኝ አይደለም» ብለዋል። ለዚህም በምክንያትነት ያቀረቡት የምርጫ ቦርድን ዝግጅት ነው።

«የመንግሥት ፍላጎት ዴሞክራሲያዊ እና ነጻ ምርጫ ማካሄድ» መሆኑን ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ዝግጅቱ ከእስካሁኖቹ ምርጫዎች የተሻለ መሆኑን» ጠቁመዋል። ይህም «በበጀት ምድባ በቢሮ እና በቦርድ አባላት አመራረጥ እንደሚታይም» አስረድተዋል። የምርጫ ሕጉም ብዙዎችን በሚያሳትፍ መንገድ መጽደቁንም ተናግረዋል። «ፈተናዎች አሉ ምርጫውን ማድረግ ግን በብዙ መንገድ ይጠቅመናል። ፈተና አልባ ምርጫ ባይሆንም የተሳካ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል» ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ «ምርጫ 97 ካስከፈለው ዋጋ ልምድ ወስዷል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ «ከምርጫ በኋላ ግጭት የሚፈልግ አይደለም» ብለዋል። መገናኛ ብዙሀን ከቀድሞ ለቀቅ ማለታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «የሲቪክ ማህበረሰቡ እና ሚዲያው ሚናቸውንን ከተወጡ ምርጫ የተሻለ ይሆናል» የሚል እምነት አንዳላቸውም ገልጸዋል። ፓርቲዎችን በተመለከተም «ምርጫ፣ አሸንፎ መንግሥት መሆን ብቻ አለመሆኑን» ጠቅሰው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያገኙትን እድል እንዲጠቀሙም ጠይቀዋል።

ፓርቲዎች ለምስረታ ማቅረብ የሚገባቸውን «የአባላት ቁጥርን አንቀበልም» ማለታቸውንም ትክክል አይደለም ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ። ይህን ዓይነት መከራከሪያ የሚያነሳ ፓርቲ «መንግሥት የመሆን ሃሳብ የለውም ማለት ነው» ሲሉ አተያያቸውን ለምክር ቤት አባላት ያካፈሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ይህ ሃሳብ ከሌለው ደግሞ በምርጫው ጊዜ ማባከን አያስፈልግም» ብለዋል።

ዶ/ር ዐቢይ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ቆይታቸው በሊቀመንበርነት ስለሚመሩት ኢህአዴግ የውህደት ጉዳይ ለተጠየቁት ምላሽ ሰጥተዋል። የኢህአዴግ የውህደት ጥያቄ ለ10 ዓመታት ሲጠና መቆየቱን እና በሃዋሳው ጉባኤ ላይ አባላቱ ውህደቱ እንዲፈጸም መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። ሆኖም ውህደቱ ያልተቋጨ ጉዳይ መሆኑን አስረድተው ፈተና እና ችግር ቢኖርም ጥናቱ በጋራ ከታየ በኋላ ምክር ቤቱ ያጸድቀዋል ብለዋል። «ኢህአዴግ ቢኖርም ቢሞትም ኢትዮጵያ ትቀጥላለች» ሲሉ የሀገሪቱ ህልውና ጉዳይ ከገዢው ግንባር ጋር የተያያዘ አለመሆኑንም በአጽንኦት አስረድተዋል።

ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር

አዜብ ታደሰ

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች