ጠ/ሚ ኃይለማርያም እና የፓርላማ አባላት ጥያቄ | ኢትዮጵያ | DW | 20.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ጠ/ሚ ኃይለማርያም እና የፓርላማ አባላት ጥያቄ

ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን የተከሰተዉ የፖለቲካ ቀዉስ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋትና መቁሰል፣ ለሺህዎች መፈናቀል እና ንብረት መዉደም፣ እንዲሁም ለማኅበራዊ መስተጋብር እና ለመማር ማስተማር ሂደት መሰተጓጎል ምክንያት መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት እየተዘገበ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:33

የፓርላማ አባላት ጥያቄ

በሀገሪቱ ዉስጥ ለሚታየዉ ለዚህና ተያያዥ ጉዳዮች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚፈል መጠየቃቸዉን ይናገራሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሎች እየተጎዱ ያሉትን ሰዎች ወክለዉ በፓርላማ ይገኛሉ፣  ስለዚህ እንደ አባልም ሆነ እንደ ተቋም የአገሪቱ ሕገ መንግስት የሰጣቸዉን ሚና መጫወት እንዳለባቸዉ ይታመናል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ቡሌ ሆራን ወክለዉ ፓርላማ የሚገኙት አቶ ቦነያ ኡዴሳ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ፓርላማ ቀርበዉ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ የጠየቁበትን ምክንያትም እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፣«ባሁኑ ሰዓት እየተሰራ ያለዉ፣ አሁን እየተጣሳ ያለዉን የሰባዓዊ መብት ሊያስቆም የሚችለዉ ወይም ለማስቆምም ግዴታ እንዳለዉ ሕገ መንግስቱ ለኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰጥቷል። የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዉን  የሚመሩት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸዉ። አሁን በአገሪቱ ከሕገመንግስት ዉጭ በሰዉ ልጅ ላይ እየተፈፀመ ያለዉን የሰበዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ስላለባቸዉ  ፓርላማዉ ከእሳቸዉ ጋር ሊወያይ ይፈልጋል። እኛም እንደ ፓርላማ አባላት መጠየቅ የምንፈልገዉ የሰዉ ግድያ ለምን አልቆመም? በመንግስት በኩል ይህን ለማስቆም እስካሁን ምን እየተሰራ ነዉ? ይህን ለማስቆም ምን መደረግ አለበት፣ ለምን አልቆመም፣ ለምን አላስቆማችሁም? የሚሉ ጥያቄዎች በዋናነት የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸዉ።»

Äthiopien | Parlament

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ (ግራ)፣ የቀድሞዉ የፓርላማ አፈ-ጉባኤው አቶ አባዱላ ገመዳ (ቀኝ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥያቄያችሁን ለመመልስ ወደ ፓርላማ መቼ ብቅ እንደሚሉ አሳዉቀዋል? ለሚለዉ ጥያቄ፣ «እሳቸዉ አሁን እየተካሀደ ባለዉ የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ይገኛሉ። እንደ ኢሕአዴግ የተነሳዉን ጥያቄ በስብሰባዉ ላይ ስለሚወያዩበት፣ በዛ ላይ ተወያይተንበት የምንደርስበት ነጥቦች ይዤ እመጣለዉ ብለዋል። ያልተጠናከሩ ነጥቦችን ይዤ ከምመጣ እንደ ኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተወያይተንበት በአጭር ግዜ ዉስጥ መጥቼ መልስ እሰጣችኋለዉ ስላሉ እየጠበቅናቸዉ ነዉ።»

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲቀርቡና በጉዳዩ ላይ እንድንወያይ የጠይቅነበት ምክንያት የወከልነዉን ሕዝብ ድምፅ ለማሰማት ነዉ የሚሉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ናጋሌን በመወከል ምክር ቤት የገቡት አቶ ታሪኩ  ደምሴ ናቸዉ። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤት ቀርበዉ በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ የተወያየን ቢሆንም ያን ጊዜ ሁኔታዎች እንዲህ አልባሱም ነበርም ይላሉ። «ከዝህ በፊትም፣ ይመስለኛል ከአንድ ወር በፊት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበዉ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዉ ነበር። ግን የፖለቲካዉ ሁኔታ ከዚህ ደረጃ አልደረሰም ነበር። ችግር ቢኖርም በግዜዉ እንደ አሁኑ ከበበድ ያለና የከረረ አልነበረም።»

በአገሪቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች ኦሮሚያ ክልል 178 መቀመጫ፣ አማራ ክልል 134፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል 108፣ ትግራይ ክልል 37፣ አዲስ አበባ 23 መቀመጫዎች ሲኖሯቸዉ፤ ቀሪዉ በሌሎች አጋር ድርጅቶች የተያዘ መሆኑን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ 


 

Audios and videos on the topic