1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ኃይለ ማርያም ሥልጣን ሊለቁ ነው

ሐሙስ፣ የካቲት 8 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እና ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመነሳት መጠየቃቸውን አስታወቁ። አቶ ኃይለ ማርያም ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመነሳት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገብተዋል።

https://p.dw.com/p/2slIA
Äthiopien kündigt Freilassung politischer Gefangenen an | Hailemariam Desalegn
Desalegn
ምስል Getty Images/AFP/A. Shazl

 ከሃላፊነታቸው የሚነሱትም በሀገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ችግር ለማስወገድ የሚወሰደው መፍትሄ አካል ለመሆን በማሰብ መሆኑን በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ለመነሳት ለግንባሩ ምክር ቤት የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውንም የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም በቅርቡ የኢህአዴግ ምክር ቤት በሚያካሂደው ስብሰባ ለጥያቄአቸው የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ዲኢህዴን ሊቀመንበርነት ለመነሳት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ጥያቄአቸውን ይቀበላል ብለው እንደሚጠብቁም አስታውቀዋል። ያስገቧቸው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤዎች ውሳኔ እስከሚያገኙ በሃላፊነታቸው እንደሚቆዩም ተናግረዋል። አቶ ኃይለ ማርያም በዛሬ መግለጫቸው ለወቅታዊዎቹ የሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ፍለጋ ህዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል። የ52 ዓመቱ አቶ ኃይለማርያም የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜና በሞት ከተለዩ በኋላ ከመስከረም 2005 ዓም አንስቶ በጠቅላይ ሚኒስርነት ከዚያ ቀደም ሲልም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ