ጠ/ሚሩ በጦር ሜዳ፤ የፊልትማን ስጋትና የህወሓት 12 አዛዦች ተገደሉ መባል | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 26.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጠ/ሚሩ በጦር ሜዳ፤ የፊልትማን ስጋትና የህወሓት 12 አዛዦች ተገደሉ መባል

«በዶ/ር ዐቢይ ደም ዉስጥ የነጠረ የኢትዮጵያዊነት፤ የአንድነትና የመደመር ንጹህ ደም አለ» «የአራዳ ልጅ ማንም ወጣት በዐቢይ ሙድ እንዳይሸወድ። ነገም ሌላ ቀን ነው።» «የትግራይ ህዝብን ህልውና እና ምግብ መድሃኒትን እንዳይገባ እኪፈቀድ የሚያሰቁመው ማንም ምድራዊ ኃይል የለም» «አሜሪካ ስለእኛ ምነው እንደዚህ ተጨነቀች ግን?»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:56

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ  ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር የሚዋጋዉን የመንግሥታቸዉን ጦር በግንባር ተገኝተዉ ለመምራት እዘምታለሁ ማለታቸዉን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶችን በመጀመርያ ይዘናል። ጠ/ሚ ዐቢይ እዘምታለሁ ማለታቸዉ ከተሰማ በኋላ በኅብረተሰቡ ዘንድ መነቃቃት በመፍጠሩ እና ኅብረተሰቡ ወደ ግንባር እየዘመተ መሆኑን በዚሁ ሳምንት መጀመርያ ላይ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አስታዉቆ  ነበር። ታዋቂ ስፖርተኞች የመድረክ እና የስነ-ፅሑፍ ሰዎች ወጣት አዛዉንቱ ማለትም በርካታ ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን መከተላቸዉ ተዘግቦአል።

አስናቀች ሜስፊናት የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ አብይ ወታደር ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። ዐብይ ወታደር ነዉ። ጠቅላይ ሚንስትር መሆኑ ብቻ አይደለም አይደለም። በቃ ወታደር ነው። ግዴታውን ይወጣል። ወታደር ደግሞ ግዴታውን ያውቃል። ብቻ ለአሁኑ ዘመን የተለየ መሪያችን ነው ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

መስፍን ማርቆስ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚም ፤ በዶ/ር ዐቢይ ደም ዉስጥ የነጠረ የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የመደመር ንጹህ ደም ስለመኖሩ እና፤ ያለጥርጥር ወደ ጦር ሜዳ ሀገሩን ለመታደግ መዝመቱን ሙሉ ምስክር ነኝ ብለዉ ጽፈዋል።

አማራ ጎንደሬው የሚል ስምን የሰጡት የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ የአራዳ ልጅ እንዳትሸወድ። ማንም ወጣት በዐቢይ ሙድ እንዳትሸወድ። ነገ ሌላ ቀን ነው። ይህ ጨለማ ቀን ያልፋል። የማይነጋ የሚመስለው ቀን ይነጋል ብለዋል።

ደጀኔ ነገራ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ዐብይ ስንዴ ሲታጨድ በሄሊኮፕተር ይበርና እዚያ ይገኛል፣ የደካማ እናቶች መኖሪያ ቤት ሊታደስ ሲታቀድ ዶማና አካፋ ይይዝና እዚያ ይገኛል። እንዲሁም በሱ ውሳኔ መሠረት ሀገሪቷ ለጦርነት ስትገደድ አሁንም በሄሊኮፕተር ይበርና የጦር ሜዳ መነፅር ይይዝና እዚያ ይገኛል። የእነዚህ ሁሉ ነገሮች ውጤታማነት መጨረሻው እንዳለ ሆኖ፤ ሥራዎቹን የሚሠሩት ሌሎች ስለሆኑ፤ የእሱ በዚያ ሥፍራ መገኘት ወይም አለመገኘት በመጨረሻ ውጤቱ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ታደሲ ዲሪባ የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ እውነት ምን ጊዜም አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ሕዝቡ አካባቢውን በተጠንቀቅ መጠበቅ ነው የሚጠበቅበት ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ምስክር ተገኝ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ "ክብር ድል ለጀግናው መሪያችን!ድል ለኢትዮጵያችን! ድል ለህዝቦቿ!ጠላቶቻችን ይውደሙ። ኢትዮጵያ ጀግና ብልህና አሰተዋይ መሪና ልጆች አሏት። እትዮጵያ አትሸነፍም። እግዚአብሔር ከእርሶና ከሰራዊቱ ጋር ይሁን ያሉት ደግሞ አዉዲ አጥናፉ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ።

አፖስትል አያሌ አቡሌ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ እንዲህ ይላሉ። ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ስምና ስልጣን ይጠብቅህ ።በፀሎት ከጎንህ ነኝ ። ብለዉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

አዱኛ ደግፊ ተፈራ የተባሉት የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ ባስቀመጡት አስተያየት ስር ብዙ የይሁንታ መልስ አግኝተዋል። የጅል ለቅሶ መልሶ መላልሶ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። ሁሌም ያው። ከዐቢይ መዝመት ውጭ ሌላ ነገር የለም በቃ። በቃ ሄደ ለሃገሩ ተሰለፈ። ይሄዉ ነዉ ። ሌላ ስንት ነገር አለ የሚሰራ። ወደዚያ ዙሩ እስቲ። ብለዋል። ይደመድማሉ።

በሁለተኛነት አስተያየቶችን የሰበሰብነዉ በዚሁ ሳምንት መጀመርያ፤ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዮ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፊሪ ፊልትማን የኢትዮጵያው ጦርነት መባባሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በሚካሄደው ጥረት ላይ ስጋት መፍጠሩን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል ። ፌልትማን የህወሓት ኃይሎች ወደ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ከተንቀሳቀሱ ተቀባይነት የሌለውና አስከፊ ሲሉ ስጋታቸዉን መግለፃቸዉን በተመለከተ ዘገባ ሥር ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤

አሜሪካ ስለእኛ ምነው እንደዚህ ተጨነቀች ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት የፌስቡክ ተከታታይ አለም መስፍን፤ ኢትዮጵያ የሚጨነቅላት እግዚአብሔር፤ ቅድስት ሃገራችንን የሚጠብቃት አይተኛም። አያንቀለፋም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ጎይቶም ኃይላት የተባሉ የፊስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ የትግራይ ህዝብን ህልውና እና ምግብና መድሃኒትን እንዳይገባ በር የተዘጋበትን ሁሉ መንገድ እሰኪከፈት ድረስ የሚያሰቁመው ማንም ምድራዊ ኃይል የለም ሲሉ ጽፈዋል።

አብድልፈታ ያሲን የተባሉ የፊስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ ወይ ጉድ በምን አቅማቸው ነው የሚመጡት? የኢትዮጵያ ጀግኖች የት ሄደው? በቅርብ ቀን ውጤቱን አብረን የምናየው ይሆናል። የኢትዮጵያ ጠላቶች ጨርሰው ይረግፋሉ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ቢንኪ ቢንኪ ሲሉ መለያ ስማቸዉን የፃፉት የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ አዱ ገነት ከመኝታ ቤት ሳሎን ይመስላቸዋል እንዴ? ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ምልክት ዘግተዋል።

ለዱስ ላቭ የተባሉ የማኅበራዊ ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ አይ ዋና ከተማ አይደለም ከደሴ እና ከኮቦልቻ በህውይት ማምለጥ ከቻለ ጅግንነት ነው። መቀለ መመለስ የለም መውጣትም አይታሳብም ። ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው 12 የህወሓት ከፍተኛ የጦር አዛዦች መገደላቸዉን በያዝነዉ ሳምንት አስታዉቆ ነበር።  የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሠ ቱሉ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦሩ ወደ ከፍተኛ የማጥቃት ርምጃ ውስጥ መግባቱን ገልፀዋል። በሚንስትሩ መግለጫ መሠረት በባቲ ግንባር ስድስት የየሕወሓት ቡድኑ የጦር እና የኮር ከፍተኛ አዛዦች ተደምስሰዋል። በከሚሴ ግንባርም እንዲሁ የህወሓትን ጦር ሲመሩ የነበሩ ስድስት ከፍተኛ አመራሮች መደምሰሳቸውን ሚንስትሩ ገልጸዋል። ተገደሉ የተባሉት የጦር አዛዦች ስምንና ማዕረግ ግን አልጠቀሰም።የኢትዮጵያ መንግስት ሠራዊት እየሸሸ ያለውን የህወሃትን ተዋጊ እግር በእግር እየተከታተለ ርምጃ እየወሰደበት እንደሚገኝም ሚንስትሩ አስታውቀዉ ነበር። ይህን ዘገባ ተከትሎ የተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤

ትግራይ አደዬ የሚባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ የህዉሀት ከፍተኛ አመራር የሚባሉ እነማን ናቸዉ? ሁሉ ከፍተኛ ናቸዉ የህዉሀት አመራሮች ብለዋል።

ሰለሞን ቦጋለ ያለኔ የተባሉ አድማጭ፤ ሀገር ለማፍረስ የመጣን መቅጣትማ እትዮጵያ ታቅበታለች። ኢትዮጵያ በልጅቿ ተክብራ ትቀጥላለች ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ሙባረክ አማን ኢብራሂም ደሞ እርምጃዉ ገና ይቀጥላል። ወደን አይደለም የገባነው እራሳቸው የቀሰቀሱት እሳት ነው፤ ሲሉ ጽፈዋል። አሁ ረጋ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ፤ ግልፅ ያልሆነልኝ ነገር አዋጊዎቹንና መሪዎቹን በአንድ ቦታ ተሰብስበው እንዴት አግኝተው ሊደመስሷቸው እንደቻሉ ነዉ ስማቸዉን ብትነግሩን ሲሉ በአስተያየታቸዉ ጠይቀዋል።

ለምን ግን የተባሉ ሌላዉ የሶሻል ሚዲያ ተጠቃሚ፤ አሁን የድል ዜና የምንሰማበት ይሆናል። ሰሞኑን ለምራባዊያን እና አሜሪካ ከእግራችን ስር ወድቀው ይቅርታ ይጠይቁናል። በቅርብ እናየዋለን። ወደ አፍሪካ መግቢያው ኢትዮጵያ ስለሆነች ታሪካችን ምስክር ነው።

አድማጮች አሁን አሁን ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚገኙ አስተያየቶች በሙሉ ማለት ይቻላል፤ የጋዜጠኝነት አልያም የሰዉነትን መርህ ያልጠበቁ ብቻ ናቸዉ። የስርጭት ክፍላችን እነዚህን አይነት አስተያየቶች ይሰርዛል፤ ፀሐፊዎንም እስከወዲያኛዉ ያግዳል። ጠቃሚ ሂስ እና አስተያየቶችን የምትፅፉትን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች እያመሰገን ሙሉ ጥንቅሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን ተጭነዉ ሙሉ ዝግጅቱን እንዲደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ   

Audios and videos on the topic