ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ኻርቱም ሊያቀኑ ነው | ኢትዮጵያ | DW | 24.08.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ኻርቱም ሊያቀኑ ነው

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአንድ ቀን ጉብኝት ነገ ወደ ሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም ያመራሉ። የሱዳን ዜና ወኪል (ሱና) ዛሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታሕ አል ቡርሐን ያቀረቡትን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ጠቅሶ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ነገ ወደ ኻርቱም እንደሚያመሩ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአንድ ቀን ጉብኝት ነገ ወደ ሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም ያመራሉ። የሱዳን ዜና ወኪል (ሱና) ዛሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታሕ አል ቡርሐን ያቀረቡትን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ጠቅሶ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ነገ ወደ ኻርቱም እንደሚያመሩ ዘግቧል።

አምባሳደር ይበልጣል ከሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታሕ አል ቡርሐን ተገናኝተው የሹመት ደብዳቤያቸውን እንዳቀረቡ በኻርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፌስቡክ ባሰራጨው መረጃ አረጋግጧል። ይሁንና ስለ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዞ ምንም ያለው ነገር የለም። ዶይቼ ቬለ ኻርቱም ወደ ሚገኘው ኤምባሲ በተደጋጋሚ በመደወል መረጃውን ለማጣራት ያደረገው ጥረት አልሰመረም።

ኢትዮጵያ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ከሱዳን እና ግብጽ የምታደርገው ድርድር እስካሁን ሶስቱንም ወገኖች ከሚያስማማ የመፍትሔ ሐሳብ አልደረሰም። በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት የሚደረገው ድርድር በሱዳን ጥያቄ ከተቋረጠ በኋላ እንደገና ተጀምሯል።

የግብጽ የመስኖ እና የውኃ ሐብቶች ሚኒስቴር ከአምስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ድርድሩ እስከ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር።  

ባለፈው ነሐሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. የግብጹ ጠቅላይ ምኒስትር ሙስጠፋ ማዶብሊ ወደ ኻርቱም አቅንተው ከጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ጋር ከተወያዩ በኋላ ተቋርጦ የነበረው የኅዳሴ ግድብ ድርድር ለቀጠል መስማማቷን ሱዳን አስታውቃለች።  

ማዶብሊ በወቅቱ ወደ ሱዳን ያቀኑት የግብጽ የውኃ እና መስኖ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የጤና፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምኒስትሮች አስከትለው ነበር።  ጠቅላይ ምኒስትሩ በኻርቱም ቆይታቸው ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል-ቡርኻን፤ ከምክትላቸው መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ማይክ ፖምፔዎ ከትናንት ነሐሴ 17 እስከ 22  ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ሱዳንን ጨምሮ አራት አገሮችን እንደሚጎበኙ የመሥሪያ ቤታቸው ቃል አቀባይ ሞርጋን ኦርታጉስ አስታውቀዋል።

ፖምፔዎ የሚጎበኟቸው አገራት እስራኤል፣ ሱዳን፣ ባሕሬን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ናቸው። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ማይክ ፖምፔዎም ነገ ወደ ኻርቱም እንደሚያቀኑ የሱዳን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ዘግቧል። ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ የእስራኤል ጉብኝታቸውን የጀመሩ ሲሆን ወደ ሱዳን ሲያቀኑ ከጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይገናኙ እንደሁ የታወቀ ነገር የለም።  

እሸቴ በቀለ