1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ከጋዜጠኞች ጋር እንዲወያዩ ጥያቄ ቀረበ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉትን ተከታታይ ውይይት ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ጋርም እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠየቀ። ምክር ቤት የውይይት ጥያቄውን ከሦስት ሳምንት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ማስገባቱን እና ምላሽም እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4et7D
ጠ/ሚ አብይ አህመድ
ጠ/ሚ አብይ አህመድ ምስል Office of Prime minister of Ethiopia

ለጠ/ሚው የቀረበ የውይይት ጥያቄ

በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገውና  ከ80 በላይ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን ፣ የሙያ ማሕበራትን እና የበይነ መረብ እንዲሁም የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃንን ያቀፈው ምክር ቤቱ፤ አሳሳቢነቱ የጎላው የጋዜጠኞች እሥር እና እንግልት፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ያሉባቸው ችግሮች ለውይይት ካቀረባቸው አጀንዳዎች መካከል መሆናቸውን አስታውቋል።

 

የጥያቄው መነሻ

 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትየሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ኃይሉ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ያደረጉትን ውይይት ከጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋርም ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ጥያቄው ቀርቧል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምህዳር መጥበብ፣ መገናኛ ብዙኃን በጎ ሚናቸውን እንዲወጡ የመንግሥት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ እንወያይ የሚለውን ጥያቄ እንዲያነሱ እንዳደረጋቸውም ገልፀዋል።

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተከታታይ ውይይት ሲያደርጉ እየተመለከትን ነው። ነገር ግን ላለፉት ስድስት ዓመታት ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና ከጋዜጠኞች ጋር በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ውይይት አልተደረገም።»

ምክር ቤቱ ያቋቋመው የግልግል ዳኝነት በጎ ሆኖ ሳለ ያንን ትቶ ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ማሰርና ማንገላታት የሚቆምበትን ሀሳብ ለማንፀባረቅ ለጥያቄያቸው የመንግሥትን ይሁንታ እንደሚጠብቁም አቶ ታምራት ነግረውናል። «ጋዜጠኞች ከመንገድ ላይ ይያዛሉ። ይታፈናሉ። ያሉበት የማይታወቅ ሁኔታ አለ። ፍርድ ቤት አይቀርቡም እና ይሄ መቅረት ይኖርበታል።»

ፎቶ ከማኅደር፤ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በቅርቡ ያካሄደው ጉባኤ
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጋር እንዲወያዩ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል።ፎቶ ከማኅደር፤ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በቅርቡ ያካሄደው ጉባኤምስል Solomon Muchie/DW

በሙያ ማሕበራት ቀርቦ የነበረ፣ ውጤት ያላገኘው ጥሪ

 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንባለሙያዎች ማሕበር መንግሥት ለመገናኛ ብዙኃን ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጥ ከሁለት ዓመት በፊት ለጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ ደብዳቤ ልኮ ነበር። ማሕበሩ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ከቤታቸውና ከሥራ ገበታቸው በጸጥታ ኃይሎች መታፈናቸው እንዳሳሰበው በወቅቱ ገልጾ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ሰምተው እንዳልሰሙ መሆናቸው እንዳሳዘነዉ ጠቅሶ አቤት ብሎ ነበር። ነገር ግን ምላሽ አላገኘም። የዚህ ማሕበር አባል የሆነ አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ጋዜጠኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ተጠይቀው ሳይሆን እንደሌሎች ሁሉ የመገናኛ ብዙኃን እና የዘርፉን ተዋናዮች ተጋብዘው ሊወያዩ ይገባ ነበር ነው ያለው።

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለይ የሚዲያ ኢንደስትሪው መጀመርያ አካባቢ የመከፈት እድል ነበረው፣ ከዚያ በኋላ በተለይ አሁን ላይ ብዙ ጋዜጠኞች ታሥረው ፣ እየተዋከቡ እንዲያውም እየተዳከመ ነው ያለው።»

አሁን ባለው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዐውድ ተጽዕኗቸው ጎልቶ የሚታይ የነበሩ የበይነ መረብ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ትንተናዎች እና ዘገባዎች ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችም ይሁን ድርጅቶች በደረሰባቸው ማስፈራራት፣ ቢሮ ተሰብሮ ዘረፋ፣ ዛቻ እና መሰል ጉዳዮች ከሙያው የመራቅ፣ የመታሠር አልያም ሀገር ጥሎ የመሰደድ ፈተና ተጋፍጠዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ